የአምራች ዘርፉን አፈፃፀም ያሻሻለው ሀገራዊ ንቅናቄ

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እምቅ አቅም ቢኖራትም፣ በዓይነትም ሆነ በብዛት በርካታ የሆኑት የዘርፉ ችግሮች ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል ጥቅም እንዳታገኝና ከረጅም ዓመታት በፊት ሲነገርለት የቆየው መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር እስካሁን እንዳይሳካ እንቅፋት ሆነዋል፡፡

ዘርፉ በግብዓት (ጥሬ ዕቃ)፣ በሰው ኃይል፣ በቦታ፣ በኃይል፣ በፋይናንስና በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግሮች ተተብትቦ የተያዘ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ የውጭ ምንዛሬ እጥረትና የአጠቃቀም ፍትሃዊነት መጓደል፣ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት፣ የሥራ ባህል ደካማነት እንዲሁም ዘርፉን ለማበረታታት የሚወጡ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች በአግባቡ አለመተግበር በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያጋጥሟቸው ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ባለሀብቶች በተለያዩ ጊዜያት ገልጸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ኢንዱስትሪዎች እያመረቱ ያሉት ከአቅማቸው በታች እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ከሰባት በመቶ ያልበለጠ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ በቀጣይ 10 ዓመታት ይህን ድርሻ ወደ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሁን ያለውን 50 በመቶ የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት አቅም ወደ 85 በመቶ የማድረስ እቅድም ተይዟል፡፡

መንግሥት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሔ ርምጃዎች መካከል በሚያዝያ 2014 ዓ.ም፣ ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው፡፡ የሀገራዊ ንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል ፤ እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የሥራ ባህል ማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው፡፡

ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ለመጨመር ብሎም የዘርፉን ልማት ለመደገፍ እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና በቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት የሚከናወኑበት ሲሆን፤ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከተለመደው አሠራር በማሻገር ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ታምኖበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ውስጥ ምርት እድገት እያበረከቱት ያለውን አነስተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያሳድግም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ንቅናቄው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን አምርቶ ለመሸጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ የምታደርገውን ጥረት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሻግር ተግባር ነው፡፡ ሀገሪቷ ያላትን ትልቅ የዘርፉን እምቅ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችን በመቀመር የተጀመረው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ፤ ምሰሶዎች ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ፣ ዘርፉን በጥናትና ምርምር መደገፍ፣ ለዘርፉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ እና የሀገር በቀል ምርቶችንና አመራረትን ማሳደግ ናቸው፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አስቻይ ሁኔታዎችና በመፍጠር የዘርፉን የማምረት አቅም ማሳደግ፣ ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ እና ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማዳን ከ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› መርሃ ግብር የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው፡፡

የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪው ተዋንያን በሆኑ በበርካታ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት የሚተገበር ቢሆንም፣ ንቅናቄውን በዋናነት የሚያስተባብረው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው፡፡ የሚኒስቴሩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በንቅናቄው ትግበራ ለአምራች ዘርፉ ችግሮች መቃለል መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ንቅናቄው በተጀመረበት ዓመት ከ50ሺ በላይ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት በክልሎች፣ በዞኖች፣ በወረዳዎችና በከተማ አስተዳደሮች በንቅናቄዎች በማሳተፍ ግንዛቤ ለመፍጠር እና ባለሀብቱንና አመራሩን ለማቀራረብ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፤ በዚህም ዘርፉ እንዲነቃቃ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል፡፡ ከ352 በላይ ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል፡፡ 635 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማምረት ጀምረዋል፡፡ አራት ሺ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዘርፉ ለመግባት ፈቃድ ወስደዋል፡፡ ባለፈው የበጀት ዓመት በንቅናቄው በተከናወኑ ሥራዎች፣ ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እና የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 55 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ለሚኖረው ውጤታማነት ትልቅ ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉትና ቀልጣፋ አሠራርን ለማስፈን የሚረዱት የአንድ መስኮት አገልግሎት እና የተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር በክልሎችና በየተቋማቱ እየተሻሻሉ መጥተዋል። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከዚህ ቀደም ይይዙት ከነበረው የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ማቅረቢያ በጀት በላይ ተጨማሪ በጀት በመያዝ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የሼድ ግንባታና የመሬት አቅርቦት ድጋፎች ተሻሽለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎች ምን ዓይነት ምርቶችን ያመርቱ እንደነበርና ለሌሎች ፋብሪካዎች ምን ያህል ግብዓት ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚያመለክት መረጃ አልነበረም። ንቅናቄው ይህ መረጃ እንዲታወቅ በማስቻሉ በአምራቾችና በገዢዎች መካከል ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪዎች መካከል የተሻለ ትስስር እንዲፈጠር አግዟል። በሀገሪቱ በአምራች ዘርፍ የተሠማሩ በርካታ ተቋማት በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ሀገራዊ ንቅናቄ እቅዶች ላይ ተመሥርተው ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ ሲሆን፣ ንቅናቄው ቀደም ሲል ጀምሮ የነበሩባቸውን ችግሮች ለመፍታት እገዛ እያደረገላቸው ይገኛል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት በንቅናቄው በኢንዱስትሪ ደረጃ ከተለዩ 2167 ችግሮች (የግብዓት፣ የመሠረተ ልማት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት፣ የመሥሪያና የማስፋፊያ ቦታ ዝግጅት፣ የጉምሩክና የሎጂስቲክስ አገልግሎት… ) መካከል፣ 1034 የሚሆኑት መፍትሔ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በቀሪዎቹ 1133 ላይ ደግሞ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል፤ ችግሮቻቸው ከተፈቱላቸው አምራቾች መካከል አብዛኞቹ የሀገር ውስጥ አምራቾች ናቸው፡፡

የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የተጀመረበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የመጀመሪያው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ኤክስፖ ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት ሁለት ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣ ሚሊኒየም አዳራሽ መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ለአምስት ቀናት የተካሄደው ኤክስፖ ከ450 በላይ ተጋባዥ እንግዶች፣ ከ25 በላይ መገናኛ ብዙኃንና ከ53ሺ በላይ ጎብኚዎች የተሳተፉበት እና ከ125 በላይ የንግድ ስምምቶች የተፈረሙበት እንዲሁም ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት የተፈፀመበት ነበር፡፡

ዘንድሮም ሁለተኛው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ከግንቦት አንድ እስከ አምስት 2016 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡ በኤክስፖው 130 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች፣ 80 መካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች (በድምሩ 210 ኢንዱስትሪዎች) ተሳታፊዎች ሆነዋል። የኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አቅምና ዘርፉ የደረሰበት ደረጃ በተዋወቀበት በዚህ መድረክ፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ምርቶችን ለማስተዋወቅና ዘላቂነት ያላቸውን ትስስሮችን ለመፍጠር እንዲሁም ሸማቹ በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ ያለውን መተማመን ለማሳደግና አማራጭ ገበያ ለመፍጠር ጥረቶች ተደርገዋል፤ ከዚህ በተጨማሪም የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት የሚያግዙ አማራጭ ሃሳቦችን የማሰባሰብና ግንዛቤ የመፍጠር ዓላማ ያላቸው የፓናል ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /ዶክተር/ ኤክስፖውን ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ ሀገሪቱ በብዙ መልኩ ተጠቃሚ እንደሆነች ተናግረዋል። በዚህ ዓመት ብቻ ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ለምርቶቹ ግዢ ይውል የነበረውን የውጭ ምንዛሬን ማዳን እንደተቻለ ጠቁመው፣ ይህም ተስፋ ሰጪ የሆነ ትልቅ ርምጃ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለኢትዮጵያ እድገትና ብልጽግና ወሳኝ የሆነ ዘርፍ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ሲሶ ያህሉን ይሸፍናል፡፡ኢንዱስትሪው የግብርና ግብዓቶችን ይፈልጋል፡፡ በስንዴ፣ በቡናና ሻይ፣ በሩዝና በሌሎች የግብርና ዘርፎች ልማት የተገኙ ውጤቶች የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ አጋዥ ይሆናሉ፡፡ ግብርና ላይ ተሳክቶልናል፤ በኢንዱስትሪውም እንዲሳካልን ተባብረን መሥራት አለብን›› ብለዋል፡፡

እንደሳቸው ማብራሪያ፤ መንግሥት በሕግ፣ በፖሊሲና በአሠራር የሚወስዳቸው ርምጃዎችም ወሳኝ ግብዓቶች በመሆናቸው በዚህ ረገድ ከተሠሩት ሰፋፊ ሥራዎች በተጨማሪ ሌሎች ቀሪ ተግባራትም በትኩረት ይከናወናሉ። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኙ ውጤቶችን ለማስፋት እድሎችን መመልከት፣ ፈጠራን ማበረታታት፣ የጥናትና ምርምር ተግባራትን መደገፍ እና የሀገር ውስጥ ምርትን ማበረታታትን የሥራ አካል ማድረግ ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች ለማሟላት የኢንዱስትሪ ማኅበረሰቡ የሚጠበቅበትን ግብር በአግባቡ መክፈል እንደሚኖርበትም አሳስበዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው፣ ኤክስፖው ኢትዮጵያ የአምራች ዘርፉን ተወዳዳሪነት፣ የምርት ጥራትና ብዝሀነት እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን በመጨመር የኢንዱስትሪ ዘርፉ በሀገራዊ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ ያላት ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ይላሉ፡፡ እሳቸው እንደሚገልጹት፤ ከ100ሺ በላይ ጎብኚዎች ኤክስፖውን ጎብኝተዋል፡፡ 157 ዲፕሎማቶች እንዲሁም ከ57 ሀገራት የመጡ ድርጅቶች ተሳትፈዋል። ከ830 በላይ ሰዎች የተሳተፉባቸው የፓናል ውይይቶች ተካሂደዋል፤ በዚህም አምራቾች ከፖሊሲ አውጪዎች ጋር በቀጥታ ተገናኝተው እንዲመካከሩ ተደርጓል፡፡ 5188 ግብይቶችና የግብይት ትስስሮች ተከናውነዋል። 74 አብሮ የመሥራት ስምምነቶች ተደርገዋል፡፡ የሀገር ውስጥ አምራቾች ከሰባት ሀገራት ከመጡ ድርጅቶች የግዢ ትዕዛዞችን ተቀብለዋል፡፡ በኤክስፖው ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ተፈፅሟል፡፡

አቶ መላኩ እንዳብራሩት፣ በኤክስፖው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የተካሄዱ የፓናል ውይይቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ የዘርፉን ማነቆ በቅንጅት በመፍታት የ‹‹እንችላለን›› ስሜት የዳበረበት፣ አማራጭ ሃሳቦችን የተሰበሰቡበት፣ ምርቶችን በማስተዋወቅና ዘላቂ የንግድ ትስስር በመፍጠር እንዲሁም የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ሸማቹ በሀገር ውስጥ ምርት ላይ ያለውን አመኔታ በማሳደግ አማራጭ ገበያዎች የተመቻቹበት ሆኗል፡፡

የሀገር ውስጥ ምርቶች የተሻለ እውቅና እንዲያገኙ እና የሀገር ውስጥ የምርትና የንግድ ሥራዎችን ለመደገፍ አስችሏል፡፡ ሸማቾች አዳዲስ ምርቶችን እንዲያውቁ እና ዋጋዎችንና የግዢ ውሳኔዎችን እንዲያወዳድሩ አግዟቸዋል። በተጨማሪም ለፖሊሲ አውጭዎች መረጃ በመስጠት ያልተፈቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት መንግሥት ለአምራች ዘርፉ እድገት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩና ውጤትም ያስገኙ ርምጃዎች መውሰዱን ያስታወሱት አቶ መላኩ፤ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ እና የተኪ ምርት ስትራቴጂ ዝግጅት፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የገበያ ድርሻ የማሳደግ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆኑ የማድረግ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ አስተባባሪ እና የቢዝነስ ከባቢ ሪፎርም ኮሚቴ (Business Climate Reform Steering Committee) የማቋቋም፣ የፋይናንስ አቅርቦትን የማሳደግ ተግባራት ዋናዎቹ ርምጃዎች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

‹‹እነዚህ ርምጃዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የነበሩ 395 ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም በትግራይ ክልል 217 ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ አስችለዋል፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪ የማምረት አቅም አጠቃቀም በ2013 በጀት ዓመት ከነበረበት 47 በመቶ በ2016 በጀት ዓመት አጋማሽ ወደ 56 በመቶ አድጓል፡፡ የኢንዱስትሪ ምርት በ2013 ከነበረበት 36 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ በዚህ ዓመት አጋማሽ ወደ 39 በመቶ እንዲሁም ዘርፉ በየዓመቱ ይፈጥረው የነበረውን 172ሺ ቋሚ ሥራ እድል ወደ 256ሺ ማሳደግ ተችሏል›› ብለዋል፡፡

ይህን ለአምስት ቀናት ተካሂዶ ባለፈው ሰኞ የተዘጋውን የኢትዮጵያ ታምርት ኢግዚቢሽን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ /ዶ/ር/ን ጨምሮ በከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በክልል ርእሳነ መስተዳድሮች፣ በአምራቾች፣ በሸማቾች፣ በአጠቃላይ በዘርፉ ባለድርሻዎች ተጎብኝቷል። አምራቾች ከአምራቾች እንዲሁም ከሸማቾች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ያስቻለ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2016 ዓ.ም

Recommended For You