የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት 125 ዓመቱን እያከበረ ይገኛል። ሀገራቱ በዚህ ረጅም ዓመታት ባስቆጠረ ግንኙነታቸው ተጠቃሚነታቸውን መሠረት ያደረጉ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተግባራትን አከናውነዋል። በዚህም የሕዝቦቻቸውን ተጠቃሚነት ተጨባጭ ማድረግ ችለዋል።
ከዛሬ 125 ዓመት በፊት ኦፊሻል በሆነ መልኩ የተጀመረው የሀገራቱ ግንኙነት በአሜሪካ በኩል ኢትዮጵያን እንደ አንድ ትልቅ ስትራቴጂክ አጋር አድርጎ የቆጠረ ፣ ግንኙነቱም በአብዛኛው በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ ያተኮረ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያትታሉ።
በወቅቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአሜሪካ የሰላም ልዑካን “ፒስ ኮፕ” ወደ ኢትዮጵያ በስፋት መጥተው በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የነጻ አገልግሎት የሚሰጡበት ፣ ብዛት ያላቸው ኢትዮጵውያንም ወደ አሜሪካ በማቅናት በተለያዩ ሙያዎች ስልጠና የሚያገኙበት ሁኔታ የተስተዋለበት ነው።
በኢኮኖሚው ዘርፍም የአሜሪካ ባለሀብቶች መዋዕለነዋያቸውን በማፍሰስ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ መሳተፍ የጀመሩበት ፣ በሀገራቱ መካከል የተጀመሩ የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ የትብብር ስምምነቶች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ መሬት ወርደው ትርጉም ያለው አቅም የሚሆኑበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር።
ይህ ሁኔታ የደርግ መንግሥት ወደ ስልጣን ሲመጣ እና ሶሻሊዝምን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አድርጎ ሲቀበል መልኩን ቀይሯል። በሀገራቱ መካከል የተጀመረው የትብብር እና ስትራቴጂክ አጋርነት ወደ ያለመጣጣም ተለውጦ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ ለመክፈል የተገደደችባቸው ታሪካዊ ክስተቶች ተፈጥረዋል።
ከደርግ መውደቅ በኋላ በነበሩት 27 ዓመታት የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር የነበረውን የቀደመ ግንኙነት በማደስ ፣ በብዙ መልኩ ሀገሪቱን ተጠቃሚ ያደረጉ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተግባራትን አከናውኗል። በዚህም የሀገር እና የሕዝብ ባለውለታ ሆኗል።
ይህ ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት ያደረገው የሀገራቱ ግንኙነት ከለውጡ ማግስት ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ተመልሶ ፈተናዎች ውስጥ ወድቆ ተስተውሏል። የአሜሪካ መንግሥት ተገቢ ያልሆነ እና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ጫናችን ሲያደርግም ተስተውሏል።
በዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን በታላቁ ህዳሴ ግድብ የተነሳ በሀገራቱ መካከል የነበረው ግንኙነት ቀደም ሲል በግንኙነታቸው ጥላ ያጠለ ቢሆንም፤ የሰሜኑ ጦርነት ግን በብዙ መልኩ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ፈተና ውስጥ ከትቶት ቆይቷል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መስከረም 07/2014 ዓ.ም. “ጦርነቱ እንዲባባስ እና የተለያዩ የመብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል” በተባሉ አካላት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ ፈርመዋል።
ከዚያም ባለፈ ከቀረጥ እና ከታሪፍ ነጻ በሆነ መንገድ የተለያዩ ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ ከሚያስገቡ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያ እንድትወጣ የሚያደርግ ኢፍትሐዊ ውሳኔ አስተላልፈዋል። ይህም በሀገራቱ መካከል በነበረው ግንኙነት ላይ ሌላ ተጨማሪ ታሪካዊ ጠባሳ ጥሎ አልፏል።
ጦርነቱ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረገ የሰላም ስምምነት ከተቋጨ ማግስት ጀምሮ በሀገራቱ መካከል የነበረውን ግንኙነት ለማደስ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። ይህም ሆኖ ግን አሁንም በሀገሪቱ እና መሪዎቿ ላይ የተጣለው ማዕቀብ አለመነሳቱ በዜጎች ላይ ቅሬታ እንዳስከተለ ነው ።
ኢትዮጵያ ከምትከተለው ብሔራዊ ጥቅሟን ታሳቢ ካደረገ አቃፊ የውጪ ፖሊሲ አኳያ ዛሬም ከአሜሪካ ጋር ላላት ግንኙነት ትልቅ ከበሬታ ትሰጣለች። በታሪክ አጋጣሚዎች ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች እና አለመግባባቶቹ የሚፈጥሯቸውን የግንኙነት መቀዛቀዞች ብሔራዊ ጥቅምን ከማስከበር አኳያ የሚከሰቱ አድርጋ ትወስዳለች።
እንደ ሀገር ብዙ ተለዋዋጭ ፍላጎቶች ባሉበት ዓለም አቀፋዊ እውነታ ውስጥ በለውጥ ሂደት ውስጥ እንደመገኘቷ መጠን ፣ መንግሥት ረጅም ዓመታት የዘለቀው የሀገራቱ ግንኙነት በተሻለ የጋራ ሀገራዊ ተጠቃሚነት ላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከፍያለ ፍላጎት አለው። ለዚህም ያለውን ቁርጠኝነት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በተጨባጭ እያሳየ ነው ።
ኢትዮጵያውያን ድህነትን ታሪክ በማድረግ ሀገራዊ ብልጽግናን ለማምጣት ለሚያደርጉት ትግል የአሜሪካንን መንግሥት እና ሕዝብ እንደ አንድ ስትራቴጂክ አጋር አድርገው ይመለከታሉ። በዚህ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ ለሚያደርጉት ድጋፍም ትልቅ ከበሬታ አላቸው።
ቀጣይ የሀገራቱ ግንኙነት እንደ ጅማሮው ስትራቴጂክ አጋርነትን ታሳቢ ያደረገ ፣ ዓለም አቀፋዊና አሁናዊ እውነታን በተጨባጭ ያገናዘበ፣ የሀገራቱን ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ፣ የሀገርን ሉአላዊነት ያከበረ፣ የአዲስ ታሪክ ምዕራፍ ጅማሬ እንዲሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ፍላጎት ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም