የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ወደ ጎን መስፋፋትና ሽቅብ መወርወር ታሳቢ በማድረግ የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፍላጎቷ ለመመለስ ይሰራል:: ለእዚህም የግድቦቹን አቅም በማሳደግ፣ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር መውተርተሩን ተያይዞታል:: በእነዚህ የውሃ አማራጮቹ የሚያገኘውን ንጽህ ውሃም ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለማዳረስ እየሰራ ይገኛል::
የከተማዋ ውሃ ፍሳሽ ባለስልጣን የውሃ ልማቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዲያስችል ተቋማት የራሳቸውን ውሃ ከጥልቅ ውሃ ጉድጓድ እንዲያመርቱ የሚያስችል ሌላ አማራጭ እየተከተለም ነው:: ጥሩ ስራ ነው:: በዚህ አማራጭ ከተማ አስተዳደሩ የሚያመርተውን ውሃ በከፍተኛ ደረጃ ይሻሙ የነበሩ ተቋማት ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ችሏል::
አንድ ተቋም በራሱ ውሃ አገኘ ማለት ከከተማዋ ውሃ አቅርቦት ያገኘው የነበረው ውሃ ለበርካታ መኖሪያ ቤቶች የሚውልበትን ምቹ ሁኔታም ይፈጥራል:: ተቋማቱ በችግር ጊዜ የአካባቢውን ማህበረሰብ ሊታደጉ የሚችሉበት እንዲሁም ለከተማዋ ውሃ አገልግሎት ውሃ የሚያቀርቡበት ሁኔታ ውስጥም ሊገቡ ይችላሉና በመልካም ተግባር ሊታይ የሚገባው ነው::
ከተማ አስተዳደሩ በዚህ ሁሉ መንገድ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ረገድ ብዙ እየሰራ ቢሆንም፣ የውሃ ፍላጎትና አቅርቦቱ ክፍተት ከፍተኛ መሆኑ ቀጥሏል:: የችግሩን ደረጃ ለማሳየት ጥናት ማድረግም የተካሄደ ጥናት መጥቀስም የሚያስፈልግ ባይሆንም፣ ከከተማዋ ጥቂት ወረዳዎች በስተቀር አብዛኞቹ በሳምንት አንዴና ሁለቴ የሚያገኙ መሆናቸውን የባለስልጣኑ መረጃዎችም ይጠቁማሉ:: ይህ ክፍተት በራሱ የፍላጎቱን እየጨመረ መምጣት ያመለክታል::
ከዚህም በጠበቡ ቀናት የሚያገኙ ወረዳዎች እንዳሉም ይገለጻል:: የውሃ ፈረቃ ካልነበረበት፣ ወደ ፈረቃ የተገባበት እንዲሁም የውሃ ፈረቃው ሰፊ ከነበረበት ወደ ጠባቡ እየገባ ያለበት ሁኔታም እጥረቱን ቁልጭ አድርገው ያመለክታሉ:: የህዝብ ቁጥሩ እየጨመረ እንዲሁም ውሃ በስፋት የሚፈልግ አኗኗር እየተስፋፋ መምጣት ፣ የሆቴሎች ፣ ኢንዱስትሪዎች፣ ወዘተ መስፋፋት የውሃ ፍላጎቱ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታሉ::
በከተማዋ የተለያዩ መንደሮች በጀሪካን ውሃ የሚያቀርቡ በርካታ ጋሪዎች የሚታዩ መሆናቸው፣ በቦቴና በሌሎች የተለያዩ አማራጮች/በአይሱዙ/ ውሃ በስፋት ለነዋሪዎች እየቀረበ ያለበት ሁኔታም እንዲሁ የውሃ እጥረቱ ማሳያዎች ናቸው:: አብዛኞቹ የከተማ ነዋሪዎች / በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር የሌላቸው ቤቶች/ በተቀመጠላቸው ፈረቃ መሰረት ውሃ ከሄደበት ቀን አንስቶ እስከሚመለስ ድረስ ያሉትን ቀናት በሙሉ መጠቀም የሚያስችለውን ውሃ በበርሜሎች፣ ጀሪካኖች፣ ወዘተ ሁሉ በመያዝ ከተቀዱ በርካታ አመታት ተቆጥረዋል::
ይህን አለማድረግ ማለት አይደለም ትንሽ እንኳ ሳያደርጉ መገኘት የሚያስከትለውን ችግር ነዋሪው በሚገባ ስለሚያውቅ ቆሞ ያድራታል፤ ይውላታል እንጂ ውሃ መጠራቀም እንዳለበት አምኖ ውሃ ማጠራቀምን የህይወቱ የስራ አካል አርጎ ይዞታል:: የቤቱን የበረንዳውን የግቢውን ጥቂት የማይባል ቦታ የያዙት የውሃ ማጠራቀሚያ ቁሶች ናቸው:: ይህን ካላደረገ ለውሃ አገልግሎት በወር ሊከፍል ከሚችለው ገንዘብ በላይ ለአንድ ጀሪካን ውሃ መግዣ ሊያወጣ ይችላል:: ይህ እንዲሆን አይፈቅደም::
በአንድ ወቅት በእዚሁ ጋዜጣ ላይ አንድ ጋዜጠኛ የውሃ አቅርቦትን አስመልክቶ በጻፈው መጣጥፍ እኛ ቤት ውሃ እንዲቀበሉ፣እንዲያስተላልፉ የተገጠሙ ቁሶች ሁሉ ውሃ ጠምቷቸው ነው የሚሰነብቱት ያለው ታወሰኝ:: ፊት መታጠብ በጆግ፣ ገላ መታጠብ በባልዲ፣ መጸዳጃ ቤት ውሃ የሚለቀቀውም እንዲሁ በባልዲ ነው:: ወደ ማብሰያ ክፍል ሲገባም ያው ነው፤ ውሃ በባልዲና በጆግ ነው የሚንሸራሸረው:: ቁሶቹ በራሳቸው ውሃ ይዘው፣ የሚለቁትና የሚለቀቅባቸው በሳምንት አንዴና ሁለቴ ሆኗል:: እንደ ጠማቸው ይከርማሉ::
በሰለጠነ ዓለም ዘይቤ የተሰሩ የመጸዳጃ እና ማብሰያ ቤቶች ታንከር ከሌለ በስተቀር በሳምንት ከሁለት ቀናት በላይ በወጉ የሚጠቀምባቸው የለም፤ ምክንያቱ የውሃ እጥረት ነው:: በዚህ ላይ የውሃ ቁጠባው አለ:: እዚህ ከተማ ውስጥ ውሃ አይቆጠብም የሚሉ ሰዎች አንዱን ጎን ብቻ የተመለከቱ ናቸው፤ ለመኪና ማጠቢያ መዋሉ፣ ቧንቧ ስብራት ሲገጥመው ቶሎ ካለመጠገኑ ጋር በተያያዘ ውሃ በከንቱ እየፈሰሰ ያለበት ሁኔታ ታይቶ ነው አይቆጠብም የሚባለው::
እኔ ግን ካለው ችግር አኳያ አዲስ አበባ ውሃ በደንብ የሚቆጠብባት ከተማ መሆኗን አስረግጬ እናገራለሁ:: እኛ ውሃ በፈረቃ የምናገኝ ወገኖች ውሃ ቆጣቢዎች ነን:: በስንት መከራ በበርሜል በጀሪካንና በመሳሰለው ያጠራቀመውን ውሃ የሚያባክን ሞኝ የለም:: እንዳውም ችግሩ የውሃ ቁጠባን አስተምሯል ባይ ነኝ:: የእቃ እጣቢ አጠራቅሞ ለመጸዳጃ ቤት አገልግሎት የሚያውል ጥቂት የሚባል አይደለም:: አለበለዚያ የመጸዳጃ ቤት መጥፎ ጠረን ጣጣ ይከተላል::
ከከተማዋ ወረዳዎች በጣም ጥቂት ከሚሆኑት በስተቀር አብዛኞቹ በሳምንት አንዴና ሁለቴ የሚያገኙትን ውሃ ያባክናሉ ብሎ ማለት አያስኬድም:: በመሰረቱ በከተማዋ ከተፈጠረውና በቀጣይም ይፈጠራል በሚል ከተሰጋበት የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት አኳያ ሲታይ አሁን መነጋገር ያለብን በስፋት መልማትና ለከተማ መቅረብ ስላለበት ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንጂ ስለውሃ ቁጠባ ነው ብዬ አላምንም::
ስለውሃ ቁጠባ ማውራት ተገቢ አይደለም እያልኩ አይደለም:: በመሰረቱ ውሃ በተጠማ ከተማ ውስጥ የውሃ ብክነት እንዲኖር ማድረግ ትክክል አይደለም:: ውሃ መቆጠብ ነው የሚያዋጣው:: በውሃ እጥረት ውስጥ ለሚገኝ ማህበረሰብ ስለውሃ ቁጠባ መንገር ለቀባሪው አረዱትም ይሆናል:: ውሃ ሲገኝ እኮ ነው የሚባክነው:: ውሃ በአሳር በሚገኝበት ሁኔታ በተለያዩ የውሃ ማከማቻዎች ውሃ ያጠራቀመ ሰው ውሃ እንዲባክን ያደርጋል ማለት ብዙም አያስኬድም::
በአዲስ አበባ ከተማ የውሃ ልማቱን በስፋት ማካሄድ የግድ የሚል ሌላም አብይ ጉዳይ አለን:: ከተማዋ የሀገሪቱ ዋና ከተማ፤ በሌሎች የሀገሪቱ ሞዴል ሆና የምትታይ ከተማ ፣የአፍሪካም የዓለም አቀፍ ተቋማትም መቀመጫም እንደመሆኗ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉዳይ አንገብጋቢ አጀንዳ ነው:: የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ ከተማዋ እንድትደርስ ከሚጠበቅባት ስፍራም ሲታሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ልማቱም ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ትኩረት መስጠትን ይጠይቃል::
አዲስ አበባን ለምታህል የሀገሪቱ ዋና ከተማ፣ የአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ከተማ አሁን ውሃ እየለማና እየቀረበ ያለበት መንገድ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: ከመውተርተር የዘለለ አይሆንም:: የከተማ አስተዳደሩ የውሃ ፍላጎቱን ለመመለስ የሚያስችል ወሳኝ የውሃ ልማት ሥራ ውስጥ እየገባ አይደለም::
የችግሩ ስፋት የንጹህ መጠጥ ውሃ ልማቱ ከእስከ አሁንም በእጅጉ የሰፋ ሥራ ውስጥ መግባትን የግድ ይላል:: ከአመታት በፊት አንድ ግዙፍ ግድብ/ ሲቪሉ ነው የሚባለው/ ለመገንባት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ወሬውም የለም:: ያንን ግዙፍ ለመገንባት አቅሙም ሁኔታውም ቢፈቅድ፣ በሆነ መልኩ ውሃ ያስገኛል ተብሎ ወደ ግንባታ መገባት ያለበት አይመስለኝም::
የከተማዋ የውሃ ፍላጎት በእጅጉ እየጨመረ መምጣት፣ ከተማዋን እንደ ስሟ የማድረግ፣ ከአህጉሪቱ ትላልቅ ከተሞች ተርታ የማሰለፍ ራእይ ለከተማ የደም ያህል የሚቆጠረውን ውሃ ለማልማቱ ሥራ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፤ ለእዚህም ምንም እንኳ በዘርፉ ባለሙያ ባልሆንም ቀደም ሲል የተካሄዱ ጥናቶች በቅድሚያ መከለስ ይኖርባቸዋል እላለሁ::
ምን ያህል ውሃ ለማግኘት፣ መቼ ለማግኘት ፣ ምን ያህል ወጪ በማድረግ የሚሉትን የሚመለስ ጥናት በድጋሚ መስራት ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ:: ሌላ አዲስ ግድብ የመገንባት ወይም ነባሮቹን በወሳኝ መልኩ የማስፋፋት ጉዳይም ብዙም ሲወራላቸው አይሰማምና ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ሊደርስ ይችላል ብሎ መገመት አይከብድም::
አሁን በዋናነት የተያዘው ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን መቆፈር ነው:: ይህ ሀገሪቱ በከርሰ ምድር ውስጥ ያላትን የውሃ ሀብት ለመጠቀም እያደረገች ያለችው ጥረት ጥሩ ሆኖ ሳለ ከቅርብ ጊዜ የሚወጡ መረጃዎች ይህም የራሱ ችግሮች እንዳሉበት እየጠቆሙ ናቸው::
የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ ቁጥር በጨመረ ቁጥር ሊገኝ የሚችለው የውሃ መጠን እየቀነሰ ይመጣል የሚል መረጃ በዘርፉ ባለሙያዎች እየተጠቆመ ነው:: በአንድ አካባቢ ብዙ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ሲቆፈሩም ምንጩ አንድ ነውና የሚጠበቀውን ማግኘት ሊያዳግት ይችላል:: በቂ ውሃ ለማግኘት በጣም ብዙ ርቀት መቆፈር የግድ እየሆነም ነው::
ይህን ቁፋሮ ማድረግ የሚችሉ ማሸነሪዎችን በማግኘት በኩል ተግዳሮት እንዳለ የሚናገሩ ወገኖች አሉ:: አሁን ባለው የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ የከርሰ ምድር ውሃ ሊሟጠጥ እንደሚችልም የዘርፉ ባለሙያዎች እያስገነዘቡ ናቸው:: ከዚህ ሁሉ መረዳት የሚቻለው ልማቱ በበቂ ጥናት ላይ ተመስርቶ መካሄድ እንዳለበት ነው::
የከተማዋ ንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር መሰረታዊ ነው:: ስለዚህ መሰረታዊ ችግር ማውራት ውስጥ በስፋት መግባት ያስፈልጋል:: ስለውሃ እንነጋገር ከተባለ ማድረግ የሚሻለው እንዴት ተደርጎ ውሃ ይልማ ለሚለው ጥያቄ አንዱ መልስ ተበድሮም ተለቅቶም ጨክኖ ልማቱን ማካሄድ ነው:: ልማቱን ለማካሄድ ደግሞ አሁን ያሉት የልማት አማራጮች ብቻቸውን በቂ አይደሉም::
ከግድብ አኳያ ሲታይ ዱሮም የምናውቃቸው ግድቦች ናቸው አገልግሎት እየሰጡ ያሉት፤ እርግጥ ነው እቅማቸውን የማሳደግ ሥራ ተሰርቶላቸዋል:: በርካታ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ተቆፈረው ወደ ሥራ ገብተዋል:: ይሄ ሁሉ በቂ ስላለመሆኑ በከተማ ያለው የውሃ እጥረት ያመለክታል::
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት ከዘርፉ ባለሙያዎች ሰፊ ምክክር ማድረግ ይኖርበታል:: ባለሙያዎቹ በተለያዩ መድረኮችና የተለያዩ አማራጮች ላይ ሃሳባቸው እያንሸራሸሩ ናቸው:: ሌሎች ግዙፍ ግድቦችን ከአዲስ አበባ ዙሪያ ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች ድረስ በመዝለቅም ቢሆን ገንብቶ ስለመጠቀም ማሰብ ውስጥ መግባት ሲሉ አስተያየት የሚሰጡ ባለሙያዎች አሉ:: የጥልቅ ውሃ ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን በመጠቆም ሌሎች የውሃ ማግኛ አማራጮችን ማሰብ ይገባል ሲሉ አስተያየት የሚሰነዘሩም ይደመጣሉ::
ከዚህ በኋላ የሚካሄዱ ለተለያዩ የመሰረተ ልማትና የመሳሰሉት ሥራዎች የሚካሄዱ የግድብ ልማቶች የንጹህ መጠጥ ውሃን ታሳቢ ማድረግ እንዲችሉ ከወዲሁ ታሰቦ ተደርጎ ሊሰራ ይገባል ሲሉ ሰሞኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደ የኮንትስትራክሽን ኢንዱስትሪ መድረክ ላይ የጠቆሙም ባለሙያዎች ነበሩ:: ይህም ለኤሌክትሪክ ፣ ለመስኖና ለመሳሰሉት ልማቶች የሚገነቡ ግድቦች ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚውሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት የሚል አንድምታ አለውና ይጠቅማል::
ከፍተኛ የዝናብ መጠን ያላት ፣ የገጸ ምድር እንዲሁም የከርሰ ምድር ውሃ ሀብቷ ከፍተኛ የሆነች፣ በአጠቃላይ የውሃ ማማ የምትባል ሀገር ዋና ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ የላጭን ልጅ ቅማል በላው እንዲሉ በንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር መጠቀስ አልነበረባትም:: የዘርፉ ባለሙያዎች አሁን ስለተፈጠረው የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ብቻ አይደለም የሚናገሩት:: በቀጣይ ስላለው ስጋትም ነው እየጠቆሙ ያሉት:: ይህን አዳምጦ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ከወዲሁ መስራት ያስፈልጋል::
የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉዳይ ለአዲስ አበባ ከተማ አጀንዳ ተደርጎ መያዝ አለበት:: የሀገሪቱ ዋና ከተማ፣ የዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ከተማ የውሃ ማማ የምትባል ሀገር ዋና ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት ዜና የሚሰራበትም የሚሰማባትም መሆን የለባትም::
የአህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ሀገሮች ከተሞች፣ ያደጉትና በማደግ ላይ ያሉት ሀገሮች ከተሞች ንጹህ የመጠጥ ውሃ በማልማትና በማቅረብ በኩል የሄዱባቸውን መንገዶች አጥንቶ አቅም የሚፈቅደውን መተግበር መጀመርም ያስፈልጋል:: የውቅያኖስና ባህር ውሃ የጨው መጠንን እያመከኑ፣ ጥቅም ላይ የዋለ ውሃን እያከሙ፣ ወዘተ የውሃ አቅርቦታቸውን የሚያሳድጉ ሀገሮች ጥቂት አይደሉም፤ እኛ ይህን ሁሉ ማድረግ ውስጥ የሚያስገባ ሁኔታ ባይኖረንም፣ ሀይቆቻችንን ግድቦቻችንን ትላልቅ ወንዞቻችን ላይ መስራት ስለመጀመር ቢያንስ ማሰብ ግን ያለብን ይመስለኛል::
ከተማዋን ከአፍሪካ ታላላቅ ከተሞች ተርታ ለማሰለፍ እንዲሁም እንደ ስሟ ለማድረግ ግዙፍ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ነው:: ለዚህ አላማ ለምትገነባው አዲስ አበባ የሚሆነውን ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለማልማትና ለነዋሪዎቿ፣ ለተቋሞቿ፣ ወዘተ ለማቅረብ ሥራው በፍጥነት መጀመር አለበት:: ዝግጅቱን አስቀድሞ በማድረግ ልክ እንደ ኮሪደር ልማቱ ግንባታው በርብርብ የሚፈጸምበትን ሁኔታ መፈልግ ይገባል::
ይህ ሥራ መጀመር ከነበረበት ጊዜ በእጅጉ ዘግይቷል:: ይህን ሊያካክስ የሚችል ሥራ በመሥራት የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረትን የከተማ መገለጫ ከመሆን መውጣት ብቻ ሳይሆን በቂና ዘላቂ አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ የከተማዋ ውበት መገለጫ እንዲሆን ማድረግ ይገባል:: ይህ ሲሆን የላጭን ልጅ ምን በላው የተባለው አባባል ሀገሪቱንም ከተማዋንም የማይገልጻቸው ይሆናል::
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም