የመልካም አስተዳደር ችግሮች በአመራሩ ብቻ ሊፈቱ አይችሉም

ምንም ይሁን ምን የመልካም አስተዳደር ንቅዘት ባለበት ሁሉ የሕዝብ ጫንቃ መቁሰሉ፤ ሕሊናም መድማቱ የማይቀር ነው:: ባላደጉ ሀገራት ውስጥ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማምጣት ሲታሰብ ፊት ለፊት እንደ ተራራ ተደንቅሮ የማይገፋና የማይናድ የሚሆነው ይሄው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው::

መልካም አስተዳደር ማለት መልካም አስተዳዳሪ ማለት አይደለም:: ምክንያቱም መልካም አስተዳዳሪ ስላለ ብቻ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን አይቻልምና:: የራሱ የጦር ብቃትና ስልት ያለው አንድ የጦር መሪ የግል ብቃት ስላለው ብቻ አሸናፊ ሊሆን አይችልም፤ ስለዚህ ጎበዝ የጦር መሪ፤ ጎበዝ ወታደሮች ሊኖሩት ግድ ነው::

የመልካም አስተዳደር ሥርዓትም እንዲሁ ነው:: አንድ ጠንካራ አመራር ብቻውን መልካም አስተዳደርን ያሰፍናል ተብሎ አይታሰብም:: መልካም አስተዳደርን ማስፈን የብዙዎችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው:: በመልካም አስተዳደር ጉዳይ አመራሩ ብቻውን ሊታገልም ሆነ ሊጠየቅ ይችላል ወይ? በለማ ቁጥር “ጎሽ!”፤ በተበላሸ ቁጥርም “አይንህ ላፈር!” የምንለው መሪውን ብቻ ከሆነ ከምናቃናው ይልቅ የምናጣምመው ይበልጣል::

ችግሩ የሚደርሰው ሕዝብ ላይ እንደመሆኑ፤ ሕዝብ ይህን አጥርቶ የሚመለከት አይንና የሚታገልበት ወኔ ሊኖረው ይገባል:: አብዛኛዎቹ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፤ መብትና ግዴታን ጠንቅቆ ካለማወቅ የሚፈጠሩ ናቸው:: ሕዝብ መብቱን ተረድቶ የማይጋፈጥ ከሆነ የችግሩ ሰለባ ከመሆን አይድንም:: በመልካም አስተዳደር ችግር ውስጥ፤ ከታች ያለው ሠራተኛና ሕዝቡም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ዐሻራቸው መኖሩ አይቀርም::

በየተቋማቱ መውጫና መግቢያ በር ላይ የተለጠፉት የመልካም አስተዳደር መርሆዎች በአመራሩ ብቻ ሳይሆን በታችኛውም ሠራተኛ ልብ ውስጥ መስረጽ ይኖርባቸዋል፤ ወደ ሕዝቡም መውረድ አለባቸው:: አንድ ሰው አገልግሎት ፍለጋ ወደ አንድ ተቋም ሲሄድ አገልግሎቱን የማግኘት መብት እንዳለው ጠንቅቆ ቢያውቅ ኖሮ የሻይና የሥራ ማስኬጃ እያለ ወደ ኪሱ ባልገባ ነበር::

የመልካም አስተዳደር ችግር “የሕግ የበላይነት” የሚለውን ወሳኝ መርህ ካለመገንዘብ አለበለዚያም ከማናለብኝነት የሚመነጭ ነው:: ሕግ የበላይ አልሆነም ማለት በጭንቅላት ቆሞ ለመጓዝ እንደመሞከር ነው:: ይህ ደግሞ ከመውደቅም በዘለለ ከፍ ያለ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል:: አመራሩ የሕግ የበላይነትን አክብሮ ሲሠራ፤ ሰራተኛውም ሕግን አክብሮ ይሠራል፤ ሕዝብንም በአግባቡ ያገለግላል:: ይህ ሲሆን ችግሮች መግቢያ ቀዳዳ አይኖራቸውም::

የመልካም አስተዳደር ግድፈት ማለት በተዘዋዋሪ የሰብዓዊና ሕጋዊ መብቶች ጥሰት ነው:: ሰብዓዊ መብት፤ ከሀገሪቱ ሕገ መንግሥት አልፎም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጠይቅ ነው:: ሁለቱም ድርጊቶች፤ ወንጀል ስለመሆናቸው በሕገ መንግሥታችን ውስጥ የተደነገጉ ቢሆንም፤ ከመልካም አስተዳደር ጉድለት አንጻር የሚከሰቱ ጥሰቶችን በተመለከተ በቂና ግልጽ በሆነ መንገድ ማብራሪያ ተሰጥቷል ለማለት ያዳግታል::

አሻሚነታቸው ከፍ ያለ ነው:: ምክንያቱም የመልካም አስተዳደር ችግሮች፤ መልካቸውን እየቀያየሩ ከመምጣታቸውም በላይ ውስብስብና አንዳንዴም በሕግ ፊት መረጃና ማስረጃ የማይገኝላቸውም ጭምር በመሆናቸው ነው:: ተበዳዩም ቢሆን እንደሌሎች ወንጀሎች ይህን ይዞ ለሕግ አቤት ለማለት ምቹ ሁኔታን አይፈጥሩለትም:: ቢቀርብም ፍሬቢስ ከሆነ ውንጀላነት ላያልፍ ይችላል::

የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪ የሚሆኑትን ሰዎች እያደኑ ችሎት ከማቆም ይልቅ፤ የሕግ ፊደል ማስቆጠሩ ቀላሉ መፍትሄ ነው:: ካጠፉ በኋላ እየቀጡ ከማስተማሩ፤ ከጥፋቱ በፊት ሁሉን ማስገንዘቡ፤ ለመልካም አስተዳደር መልካምነት ይበጃል:: ሕግ አስፈጻሚው አካልም ከየትኛውም በበለጠ ከሕዝባዊ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት አካባቢ አይኑን ሊነቅል አይገባም:: በሕግ ማዕቀፉ ውስጥ ስለተቀመጡት ጉዳዮች፤ አስተዳደርና ሠራተኛው ምን ያህል ተገንዝቦታል የሚለውን መፈተሽም ሆነ በጋራ መሥራት አለበት::

የመልካም አስተዳደር ችግር፤ ትልቁ እልፍኝ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋም ነው:: ችግሩ በግልም ሆነ በየትኛውም ቦታና ጊዜ ሊፈጠር የሚችል ቢሆንም በመንግሥት ተቋማት ግን ይብሳል:: የመልካም አስተዳደር ችግር ተብሎ ሲነሳም በሙስናና መሰል ነገሮች ውስጥ የምንመለከታቸውን ትላልቆቹን ካልሆነ በቀር ከስር ያሉት ጥቃቅኑ ትዝም አይሉንም::

በከፍተኛ ሁኔታ የሚመዘምዙን ግን፤ ንቀን የምናልፋቸው ትንንሾቹ ናቸው:: አንዳንዴም መብትና ግዴታ አገልጋይና ተገልጋይ፤ የተገላቢጦሽ የሚዘበራረቅባቸውም ጭምር ናቸው:: የምንፈልገውን ላለማጣት ስንል ብቻ መብታችንን አሳልፈን እንሰጣለን:: “ለምን?” ብሎ መጠየቅ ፈጽሞ ክልክል ይመስለናል:: ችግር ፈጣሪዎቹ መብታችንን እንደ ግዴታ ቆጥረው ይነጥቁናል:: የእነርሱም ግዴታ የእነርሱ መብት ብቻ ይሆናል::

የሕዝብና ለሕዝብ በሆኑ ስፍራዎች በጥቂት ጉልበተኞች ምክንያት ብዙዎች መብት አልባና ግዞተኛ ሆነው የሚታዩበት አጋጣሚ ቀላል አይደለም:: ለምሳሌ ወደ መናኸሪያዎች ጎራ ስንል የምንመለከተው ምንድነው? ከሕጉና ከሕዝቡ በላይ መብቱ በባለንብረቱ መዳፍ ስር የሚሆንባቸው ሁኔታዎችን፤ አጋጣሚ ናቸው ብለን ማለፍ አንችልም::

ለምሳሌ አንድ የትራንስፖርት መኪና ላይ የሚሠራ ረዳት ከመንገድ ላይ ሊጠብቁት የሚችሉትን የትራፊክ ፖሊሶችን እያሰበ፤ ገና ጉዞ እንደጀመረ የሃምሳና የመቶ ብር ኖቶችን በተለያየ ኪስ ለብቻው ማስቀመጥ የተለመደ ነው:: ለዚህም ከታሪፉ በላይ እስከ አርባና ሃምሳ በመቶ ድረስ በእያንዳንዱ ምስኪን ተሳፋሪ ጭማሪ በማድረግ የቦተረፈውን ገንዘብ፤ ተባብረን እንዝረፍ ለሚለው ትራፊክ ያጎርሳል:: በዚህ አጋጣሚ መልካምና ለሕዝብ አሳቢ፤ ኃላፊነቱን በአግባቡ የሚወጣ አገልጋይ እንዳለም ታሳቢ ይደረግ::

መንግሥት አምኖ ያቆመው ሕግ አዋቂ ሰው በብልሹ የመልካም አስተዳደር ተግባር አብሮ መዝረፍን ከመረጠ ሾፌርና ረዳት ሕዝብን ቢመነትፍ እንዴትስ ይፈረድበታል? የቁጥጥር መሥሪያ ቤቱ ይህን ማጽዳት የግድ ይለዋል:: አለበለዚያ መልካም አስተዳደር…የሕዝብ አገልጋይነት…. የሚል ዲስኩር ቢሰማ፤ ዋጋም ለዛም የለውም::

የህክምና ተቋማትና ባለሙያዎች፤ የሕዝቡ ነብስ በአደራ የተቀመጠባቸው፤ የፈጣሪ እጆች ናቸው:: “ጤና ይቀድማል” የሚለው ሕዝብ፤ ከምንም በላይ እኚህ ተቋማት አንዳች እክል እንዲገጥማቸው አይፈልግም:: ይህን ያህል በህይወቱ የመጀመሪያና ወሳኝ ስፍራ አድርጎ ከሚቆጥረው ሥፍራ በቂ አገልግሎት ያገኛል ለማለት አይቻልም::

ባደጉት ሀገራት አንድ ዶክተር ለአንድ ሰው በሚመድቡበት በዚህ ዘመን በእኛ ሀገር ሁኔታ አንድ ዶክተር በበርካታ ሰዎች የተከበበ ነው:: ይሁንና እዚህ አካባቢ፤ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚታይ ከሆነ ሕዝቡ አበቃለት እንደማለት ነው:: አሁንም ከጤና ኤክስቴንሽን ሙያተኞች እስከ ዶክተሮቹ ድረስ፤ በመልካም ስነምግባር ማህበረሰቡን የሚያገለግሉ እንዳሉ አንርሳ::

ነገር ግን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የራሱን ሆድና ኪስ ለመሙላት የሚያደፍጥ ምግባረ ብልሹ በየትኛውም ቦታ አይጠፋም:: በጤና ተቋማት ውስጥ መድኃኒት እያለ አልቋል በማለት ታካሚዎች ውጪ ካለ የግል መድኃኒት መደብር እንዲገዙ ጥቅም የሚጋሩበትን ቤት የሚጠቁሙ የጤና ባለሙያዎች አጋጥመውን ይሆናል::

ተምረዋል የምንላቸው አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ውስጣቸው እያወቀው፤ አላስፈላጊ የሆኑ ተጨማሪ ምርመራዎችን እንድናደርግ በወረቀት ማዘዣ ጫር ጫር በማድረግ ወደ አንደኛው የግል የህክምና ተቋም ይልኩናል:: ሁልጊዜም ባይሆን፤ ከግል ሀኪም ቤቶች ጋር በመመሳጠር በዚህ አይነት መልኩ የሚጎራረሱ የህክምና ባለሙያዎችና ተቋማት ስለመኖራቸው የሚካድ አይደለም::

እንዲህ ዓይነቶቹ በባለሙያው ውሳኔና ፈቃድ ላይ የተመሠረቱ ጉዳዮች ከሕግና ደንብ ይልቅ በባለሙያዊ የሞራል ህሊናና ሰብአዊነት ላይ የተደገፉ ናቸው::

የባለሙያውን የኋላ ግድፈት በቅጣት ለማስተካከል ከማድፈጥ ይልቅ፤ አስቀድሞ ውስጣዊ ማንነቶቹን መገንባቱ ብልህነት ነው:: ግለሰባዊ ንቅዘቶች እንዲህ እያሉ ወደ አስተዳደራዊ ንቅዘት ያመራሉና::

መልካም አስተዳደርን አጎልብቶ፤ በአስተማማኝ መሠረት ላይ ለማቆም ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል:: ችግሩ የሚፍጠርባቸው አካባቢዎች ላይ ብቻ ከማተኮር፤ ከታች ገና እየመጡ ያሉት ላይ መሥራት ወሳኙ ነጥብ ነው:: ችግሮቹ የሚፈጠሩት ከማህበረሰባዊና ከሰብአዊ እሴቶች እጦት ነውና መላውን ትውልድ ለመሥራት፤ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ በበቂ ማካተትም ሊታሰብበት ይገባል::

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You