የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርት እና ምርታማነትን አሳድጎ ሀገር እና ሕዝብን ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ የለውጥ ኃይሉ ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ቢሆንም እያስመዘገበ ያለው ስኬት በብዙዎች ዘንድ ከበሬታ የተቸረው ሆኗል።
በምግብ እህል ራስን ለመቻል ለተጀመረው ሀገራዊ መነቃቃት አቅም እንዲሆን፤ የግብርናው ዘርፍ በሀገሪቱ ተግባራዊ እየሆነ ባለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ነው። ዘርፉን በሁለንተናዊ መልኩ ማዘመን ወሳኝ መሆኑ ታምኖበትም ወደ ሥራ ከተገባ ውሎ አድሯል።
ለዚህም የግብርናውን ዘርፍ ሜካናይዝድ ከማድረግ ጀምሮ በጥናት እና በምርምር የታገዘ እንዲሆን በርከት ያሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፤ የበጋ ስንዴን ጨምሮ እንደ ሀገር በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ዓለም አቀፍ እውቅና እስከ ማግኘት መድረሳቸው የዚሁ እውነታ ተጨባጭ ማሣያ ነው።
አዳዲስ የእርሻ መሬቶችን ወደ ሥራ ከማስገባት ጀምሮ ቀደም ሲል ሥራ ላይ የነበሩ የእርሻ መሬቶች በተሻለ ምርታማ የሚሆኑበትን መንገድ በጥናት በማፈላለግ የተሄደበት ረጅም ርቀት፤ አርሶ አደሩን የተሻለ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ሀገርን በክፉ ወቅት መታደግ ያስቻለ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል።
ሀገር ብዙ ፈተናዎችን እያለፈች በነበረው ሁኔታ ውስጥ በዘርፉ የተመዘገበው ስኬት ፤ ዘርፉን በተሻለ መንገድ መመራት ከተቻለ እንደ ሀገር ትልቅ ተስፋ ያለው ፣ ሀገርን ከተመጽዋችነት / ከጠባቂነትለመታደግ ለተጀመረው ሀገራዊ መነቃቃት ትልቅ አቅም እንደሚሆን በተግባር ያመላከተ ነው ።
ይህንን ታሳቢ በማድረግ መንግሥት ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ በጊዜው እንዲደርስ እያደረገ ያለው ጥረት ብዙ ፈተናዎችን አልፎ ዛሬ ላይ የደረሰበት ደረጃ የሚበረታታ እና ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በተጨባጭ ያሳየ ነው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ለ2016/17 የበልግና የመኸር ወቅት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከ19 ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ተገዝቶ ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሚሆነው ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ይገኛል፡፡ በምርት ዘመኑ አገልግሎት ላይ እንዲውል ከተገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 25 በመቶ የሚሆነው ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፤ 20 በመቶ የሚሆነው ለበልግ፤ 55 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለመኸር እርሻ የሚውል ነው።
በ2014/15 የምርት ዘመን የተከሰተው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር በ2016/17 እንዳይከሰት የግዥ ሥርዓቱን የማሻሻል፤ አስቀድሞ የመግዛት፣ ስርጭቱን የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ ተሠርቷል፤ ይህ በመደረጉም በቂ የአፈር ማዳበሪያ ለበልግ እንዲቀርብ አስችሏል፡፡
ከዚህ በፊት ከሚገዛበት በዘንድሮው ዓመት ቀደም ብሎ አፈር ማዳበሪያው እንዲገዛ መደረጉ ጊዜና ጉልበትን ከመቆጠቡ ባለፈ አርሶ አደሩ ተረጋግቶ ግብዓቱን በሚፈልገው ሰዓት በቀላሉ እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡ ስርጭቱ ላይ ሕገ ወጥ አሰራሮች እንዳይኖሩም የሚከታተልና የሚቆጣጠር ግብረ ኃይል ተቋቁሙ ወደ ሥራ መግባቱ፤ ስርጭቱ ላይ የጎላ ችግር እንዳይከሰት አድርጓል፡፡
የግብርና ሜካናይዜሽና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እየተሠራ ባለው ሥራ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፤ በበልግና በመኸር እርሻ ላይ ከ15 ሺህ በላይ ትራክተሮች ጥቅም ላይ ውለዋል፤ ለቀጣይ የመኸር እርሻ ቁጥራቸውን በማሳደግ ጥቅም ላይ የማዋል ተግባር እየተከናወነ ነው ፡፡
በስንዴ፣ ቡና፣ ሩዝና ሻይ ምርቶችና በአረንጓዴ ዐሻራ የተከናወኑ ሥራዎችም በርካቶች አድናቆታቸውን የቸሯቸው ሲሆኑ፤ በኢነርጂና በሰው ኃይል ያሉ አቅሞችም ለኢንዱስትሪ ምርታማነት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መናገራቸው ይታወሳል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል፤ ይህም የአምራች ዘርፉን በማጠናከር የተሻለ ዕድገት ለማምጣት የሚረዳ ውጤት ነው።
የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎችን ማለትም ትራክተሮች፤ ኮምባይነሮችና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ከቀረጥ ነፃ በሆነ መንገድ በማኅበራትና በአርሶ አደሮች እንዲገቡ መደረጉ በዘርፉ ለሚደረገው የቴክኖሎጂ ሽግግር ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ይታመናል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም