“ብልጽግና የየትኛውም ብሔር የዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት አለባቸው ብሎ ያምናል” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡– የየትኛውም ብሔር የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎች በተገቢው መልኩ ምላሽ ማግኘት አለባቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ ሀገሪቱ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ያልተቆራረጠ ዕድገት ማስመዝገቧን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን በጎርጎራ በተካሄደው የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አባላት የዘጠኝ ወር የሥራ አፈፃፀም ግምገማ ላይ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡

የፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ የብሔር ጥያቄ ላለፉት 50ና 60 ዓመታት ዋነኛ የፖለቲካ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ እንደነበር አንስተዋል፡፡ የራስን ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህል መሠረት ያደረጉ ንግግሮችና ክርክሮችም ሰፊ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እኛ እንደብልጽግና የየትኛውም ብሔር የሠብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥያቄዎች በተገቢው መልኩ ምላሽ ማግኘት እንዳለባቸው እናምናለን ብለዋል፡፡

የብሔሮች መብትና ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ በሀገር ጥላ ስር ካልተሰባሰብን በስተቀር ለአንድ ብሔር ብቻ በመታገል ሀገር መገንባት አይቻልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ብልጽግና በጋራ እንዳንሰራ ያደረጉንን እሳቤዎች ያፈረሰ፣ በፕሮግራምና በስትራቴጂ ደረጃ ሁሉንም ባህል፣ እምነትና ብሔር አቅፎ የሚሠራ ፓርቲ ነው። በዚህም በርካታ ሀገራዊ ለውጦችን ማስመዝገብ እንደተቻለ አመላክተዋል።

ዶክተር ዐቢይ እንዳስረዱት፤ ሀገሪቱ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ያለተቆራረጠ ዕድገት ማስመዝገቧን ተናግረው፤ በ2011 ዓ.ም 96 ቢሊዮን ዶላር የነበረውን ጥቅል ሀገራዊ ምርት በ2016 ዓ.ም 205 ቢሊዮን ዶላር ማድረስ ተችሏል። የነፍስወከፍ ገቢንም ከ922 ወደ አንድ ሺህ 822 ማሳደግ ተችሏል።

የዋጋ ንረትና ሥራ አጥነት ዋነኛ የሀገሪቱ ስብራት መሆናቸውን ገልጸው፤ ባለፈው ዓመት 33 ነጥብ አምስት በመቶ የነበረውን የዋጋ ንረት ወደ 23 ነጥብ ሶስት በመቶ ማውረድ የተቻለ ሲሆን፤ እስከ ሰኔ መጨረሻ ወደ 20 በመቶ ለማውረድ ታቅዷል ብለዋል።

ምግብ ነክ የዋጋ ንረትን ከ31 ነጥብ ስምንት በመቶ ወደ 27 በመቶ ምግብ ነክ ያልሆነውን የዋጋ ንረት ደግሞ ከ36 በመቶ ወደ 18 በመቶ ማውረድ የተቻለ ቢሆንም አሁንም ሰፊ ሥራን ይጠይቃል ሲሉ አመላክተዋል።

ከተመዘገበው ዕድገት ውስጥ የግብርናን ለአብነት አንስተው፤ ባለፈው ዓመት 393 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ማምረት የተቻለ ሲሆን፤ በዘንድሮው ዓመት 506 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት መቻሉን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂን በሚመለከት የባለፈው ዓመት በዲጂታል ክፍያ የተፈጸመው ሁለት ነጥብ ስምንት ዘጠኝ ትሪሊዮን እንደነበር አስታውሰው፤ ዘንድሮ በሶስት እጥፍ አድጎ ስድስት ነጥብ ሰባት ትሪሊዮን ደርሷል። በተያዘው ዓመት የጥሬ ገንዘብ ዝውውር በዲጂታል ክፍያ ተፈጽሟል ብለዋል።

የመንግሥት ገቢና ወጪን በሚመለከት ባለፈው ዓመት ዘጠኝ ወራት 324 ቢሊዮን የነበረው የሀገር ውስጥ ገቢና የወጪ ንግድ ገቢ በዘንድሮ ዘጠኝ ወራት 374 ቢሊዮን መግባቱን ጠቁመው፤ ገቢን ማሳደግ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በግብርና የሜካናይዜሽንና የክላስተር ሥራን ማስፋፋትና ምርታማነት በመጨመር፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የግል ሴክተሩ በነጻ የንግድ ቀጣናው እንዲገቡ አስቻይ ሁኔታን በመፍጠር፣ በንግድና አገልግሎት ደግሞ ካፒታል ገበያ፣ በስታርት አፕ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚና መሠረተ ልማት ላይ ከሠራን ይበልጥ ማደግ እንችላለን ሲሉ አብራርተዋል።

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚውን ስብራት መጠገን፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን፣ ምርታማነትንና የመንግሥትን ተቋማዊ አቅም በማሳደግ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚቻል አስታውቀዋል።

ሥራ አጥነት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ያልዘመነ የገበያ ሥርዓት፣ የጥቁር ገበያ መስፋፋት፣ ያልዳበረ መሠረተ ልማት፣ ዝቅተኛ የምርት ጥራትና የዓለም አቀፍ ገበያው መዋዠቅ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተግዳሮት መሆኑን ገልጸው፤ ኢኮኖሚውን ከነዚህ ችግሮች ለማስወጣት በቅንጅት መሥራት ይገባል ብለዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You