የዞን 5 የታዳጊና ወጣቶች እጅ ኳስ ውድድር በአዲስ አበባ ተጀመረ

የአፍሪካ ዞን አምስት የታዳጊና ወጣቶች (ከ18 እና 20 ዓመት በታች) እጅ ኳስ ውድድር ትናንት በአዲስ አበባ ተጀምሯል:: ‹‹የምስራቅ አፍሪካን የሕዝብ ለሕዝብ ወዳጅነት እናጠናክራለን›› በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ይህ ውድድር ለተከታታይ 5 ቀናት የሚደረግ ነው:: በአፍሪካ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ስር ባሉ ዞኖች ውስጥ በሚደረገው በዚህ ውድድር አሸናፊ የሚሆኑት ሀገራት በአፍሪካ የእጅ ኳስ ቻምፒዮና ላይ የሚካፈሉ ይሆናል::

በዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን የሚዘጋጀው ይህ ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ ስምንት ሀገራት ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ብሩንዲ፣ ርዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሶማሊያ እና ኡጋንዳ የሚካፈሉ ሲሆን፤ ከ250 በላይ ልዑካንም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እንዲሁም በ4 ኪሎ የስፖርት ትምህርትና ስልጠና ማዕከል በመወዳደር ላይ ይገኛሉ::

ከ18 ዓመት በታች በሚደረገው ውድድር የሚካፈሉት ስድስት ሀገራት በሁለት ምድብ ተከፍለው ሲፎካከሩ፤ በመጀመሪያው ምድብ ጅቡቲ፣ ኬንያ እና ብሩንዲ ይጫወታሉ:: በሁለተኛው ምድብ ደግሞ አዘጋጇ ኢትዮጵያ ከርዋንዳ እና ታንዛኒያ ጋር ተደልድለዋል::

ጠንካራ ፉክክር በሚጠበቅበት ከ20 ዓመት በታች የወጣቶች ቡድንም በተመሳሳይ ሀገራቱ በሁለት ምድብ ለአሸናፊነት የሚፋለሙ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ምድብ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ብሩንዲ እና ርዋንዳ ተደልድለዋል:: ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ሶማሊያ እና ኡጋንዳ ደግሞ በሁለተኛው ምድብ እርስ በእርስ የሚጋጠሙ ቡድኖች ናቸው::

ትናንት ጅማሬውን ባደረገው በዚህ ውድድር ላይ ከሁለቱም ምድብ አንድ አንድ ጨዋታ ሲደረግ በታዳጊዎች ቡድን ቡሩንዲ ከጅቡቲ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከታንዛኒያ ተጫውተዋል::

አምና ታንዛኒያ ዳሬሰላም ላይ ተካሂዶ በነበረው በዚሁ የዞን 5 የምስራቅ አፍሪካ ታዳጊና ወጣቶች ቻምፒዮና ላይ የተካፈሉት ሁለቱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች 2ኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ የብር ሜዳሊያ እና ዋንጫ ይዘው መመለሳቸው ይታወሳል:: ይህም ቡድኑ በቀጣናው ያለውን ጠንካራ ተፎካካሪነት የሚያመላክት ሲሆን፤ በዘንድሮው ውድድር ላይም ቡድኑ በበላይነት ዋንጫውን እዚሁ ለማስቀረት አቅዶ እንደሚወዳደር ተጠቁማል:: ይሁንና በበጀት እጥረት ምክንያት እንደታሰበው ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ እንዳልተቻለ የቡድኑ አባላት ከውድድሩ አስቀድሞ ገልጸው ነበር:: በቂ ዝግጅት ባይደረግም ግን ውድድሩ የሚከናወነው በራሳቸው ሀገር ላይ በመሆኑ በተፎካካሪነት ማጠናቀቅ እንደሚችሉ ይጠበቃል::

ከውድድሩ ጎን ለጎን የዳኝነት እና አሰልጣኝነት ስልጠና ከዓለም አቀፉ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን በተወጣጡ ባለሙያዎች የሚሰጥም ይሆናል:: በዚህም መሠረት ከ20 ቡድኖች የተወጣጡ 40 የሚሆኑ አሰልጣኞች ተሳታፊ ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ አዘጋጅ ሀገር በመሆኗ ተጨማሪ አሰልጣኞችን እና ዳኞችን እንድታካፍል በር ይከፍትላታል። ውድድሩ ቀጣናዊ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ በማዘጋጀቷ ከስፖርታዊ ውድድር ባሻገር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳው የላቀ ነው ተብላል:: በኢትዮጵያ የእጅ ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፍትህ ወልደሰንበት(ዶ/ር) የዞን 5 ምስራቅ አፍሪካ እጅ ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እንደመሆናቸው መጠን መሰል የውድድር አዘጋጅነት እንዲሁም የስልጠና መርሃ ግብሮችን የማግኘት ሰፊ እድል እንደሚኖራት ገልጸዋል::

በዛሬው የሁለተኛ ቀን የውድድር መርሃ ግብር መሠረትም በታዳጊ ቡድን (ከ18 ዓመት በታች) ሁለት ጨዋታዎች የሚከናወኑ ሲሆን፤ ኬንያ ከቡሩንዲ እንዲሁም ርዋንዳ ከታንዛኒያ ይገናኛሉ:: በወጣቶች (ከ20 ዓመት በታች) ውድድር ደግሞ ርዋንዳ ከጅቡቲ፣ ቡሩንዲ ከኬንያ፣ ኡጋንዳ ከታንዛኒያ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ይጫወታሉ:: በውድድሩ የሚያሸንፉ ሀገራት በቀጥታ ለአፍሪካ እጅ ኳስ ሻምፒዮና የሚያልፉም ይሆናል::

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You