ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት የሚደረግ ጥረት

ለዓመታት በሴቶች እኩል ተጠቃሚነት ዙሪያ በተሠሩ ሥራዎች የተነሳ ጉልህ ለውጦች ቢኖሩም አሁንም ሙሉ በሙሉ የፆታ እኩልነትን ለማስመዝገብ ታላቅ ትግል የሚጠይቅ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል። ሴቶች በተለያዩ የዓለም ሀገራት መድልዎ፣ ጥቃት፣ የትምህርትና የጤና አጠባበቅ ተደራሽነት ውስንነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ልዩነቶች ይደርስባቸዋል።

በሴትነታቸው ምክንያት ብቻ በእውቀት ሳያንሱ ከተለያዩ ኃላፊነቶች ሲገለሉ መመልከትም የተለመደ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ተፈጥሮ በለገሰቻቸው እናትነት ምክንያትም ለልጆቻቸው ሲሉ ጓዳ የቀሩ ከፍ ማለት ሲገባቸው ዝቅ ያሉትን ቤት ይቁጠራቸው። በተለያዩ ምክንያቶች ወደኋላ ከመቀረታቸው በተጨማሪ በተለያየ መልኩ እኩል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ የሚደርሱባቸው ጫናዎች በርካታ ናቸው። የዚህን ችግር መጠን ለማሳየት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጥናቶች የተደገፉ አሀዛዊ መረጃዎች መመልከት ይቻላል።

ዓለማችን በሴቶች እና በወንዶች መካከል ያስቀመጠችውን የኢኮኖሚ ልዩነት ስንመለከት ግርምትን ያጭራል። ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በአማካይ ከወንዶች በሃያ ሶስት በመቶ ያነሰ ገቢ ያገኛሉ። የቤት ውስጥ ሥራ የቤተሰብ ኃላፊነት የእነሱን እጅ የሚጠይቁ ሥራዎች በሙሉ ዋጋ ሳይወጣላቸው ማለት ነው። የሴቶች በአመራር ቦታዎች ላይ ያላቸው ውክልናም ዝቅተኛ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአማካይ የፓርላማ መቀመጫ ማግኘት የቻሉት ሃያ አራት በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ብቻ ናቸው፡፡

በትምህርት ላይም የልጃገረዶች የትምህርት ተደራሽነት የተሻሻለ ቢሆንም አሁንም በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች የተለያዩ ፈተናዎች እየገጠሟቸው ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ልጃገረዶች የተለያዩ የባህል መሰናክሎች፣ ያለአቻ ጋብቻ እና ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ያጋጥማቸዋል፣ ይህም የትምህርት እድላቸውን ላይ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። እነኚህን በመሳሰሉ ችግሮችም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሴቶችን በግምት ከመቶ ሰላሳ ሚሊዮን በላይ ልጃገረዶች ከትምህርት ቤት ውጭ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሶስት ሴቶች አንዷ በሕይወት ዘመኗ አካላዊ ወይም ጾታዊ ጥቃት ደርሶባታል። በሴት ልጅ ግርዛት እና ያለአቻ ጋብቻ ባሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አሁንም በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ልጃገረዶች ይጎዳሉ። ይህም በትምህርት እራሳቸውን ከፍ አድርገው እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ጉዞ በአጭሩ የሚያስቀር ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች ከወንዶች አንጻር ሲታዩ በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊውና በፖለቲካው መስኮች ያላቸው ተሳትፎና የተጠቃሚነት ደረጃ አናሳ እንደሆነ ማሳያዎች በርካታ ናቸው፡፡ ከተሳትፎና ተጠቃሚነት የአናሳነት ድርሻ ባሻገር አሁን ባለንበት በዚሁ ወቅት ሴትነት በራሱ ትልቅ ፈተና እየሆነ እንደመጣ ይነገራል፡፡ እየሰሩ እራስን መቀየርና የተሻለ ሕይወት መኖር ዘበት በሆነበት በዚህ ጊዜ ያለ ገቢ መኖርና የሰው እጅ መመልከት ምንኛ ክፉ እንደሆነ ያየ ያውቀዋል፡፡

ይህንኑ ከግምት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል ከሁሉም ክፍለ ከተማ ለተመለመሉ ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ ለሌላቸው አንድ ሺህ ሀምሳ አንድ ሴቶች ከአስር ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተስማሚ ቴክሎጂና የሥራ ማስጀመሪያ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በድጋፉ የታቀፉ ሴቶችም ከዚህ ቀደም የነበራቸው የኑሮ ሁኔታ ፈታኝ እንደነበር እና አሁን ባገኙት ድጋፍ ሰርተው ሕይወታቸው ለመቀየር ማቀዳቸውን ይገልጻሉ፡፡

ሰርተው ማደር ሲችሉ የሰው እጅ ተመልካች የሆኑት እነዚህ ሴቶች ይህንን ድጋፍ ማድረጋቸው ራስን የመቻል ስሜት እንዲኖራቸው እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። ከዚህም በላይ ከትዳር አጋር ጋር በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ግጭት ተወግዶ ልጆችን በሰላም ለማሳደግ መቻሉ እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ። ልጆች ጤናማ ግንኙነት ባለው ትዳር ውስጥ ማደጋቸው ደግሞ ለማህበረሰቡም ታላቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተጠቃሚዎቹ ሴቶች ይናገራሉ።

የድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ ደግነሽ ከድር አንዷ ናቸው፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ኗሪ ሲሆኑ ባለ ትዳር እና የሶስት ልጆች እናት ናቸው፡፡ ከእለታት በአንዱ የእለት ተዕለት ተግባራቸውን በማከናወን ላይ ሳሉ ባጋጠማቸው የመውደቅ አደጋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኑሮአቸው ከዊልቸር ጋር ተቆራኝቷል፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆንም እስትንፋስ እስካለ ድረስ ሕይወት መቀጠሏ አይቀርም፡፡ ሀዘንም ደስታም የሕይወት ገፅታዎች በመሆናቸው የወይዘሮ ደግነሽ ሕይወትም ቀጥሏል፡፡

የወይዘሮ ደግነሽ ባለቤት ምንም እንኳን የአጋራቸው አደጋ ላይ መውደቅ እጅግ ቢያሳዝናቸውም የሕይወትን ውጣውረድ በመጋፈጥ የጉልበት ሥራን በመሥራት በሚያገኙት ገቢ ሶስት ልጆቻቸውን እና ባለቤታቸውን ለማስተዳደር ሌት ከቀን እንደሚታትሩ ባለቤታቸው ምስክርነት ትሰጣለች፡፡

በራሳቸው መንቀሳቀስ እና ወደ ውጭ ወጥተው ሰርተው መግባት በማይችሉበት በዚህ ወቅት የዚህ ድጋፍ ተጠቃሚ በመሆናቸው እጅጉን ተደስተዋል፡፡ ለሰጭው አካልም ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ባገኙት ዘመናዊ የዳቦ መጋገሪያ ኦቭን በሚኖሩበት አካባቢ ማስታወቂያ በመለጠፍ ድፎ ዳቦ እየጋገሩ በመሸጥ የባለቤታቸውን ሸከም ለመጋራት እንደሚሰሩ የሚናገሩት ወይዘሮ ደግነሽ፤ ከሚያገኙት ገቢ በመቆጠብ ሥራቸውን የማስፋፋት እቅድ እንዳላቸውም ይጠቅሳሉ፡፡ ዳቦ መግዣ ይቸግራቸው የነበሩት ሴት ዳቦ ጋገረው መሸጥ ብሎም በሥራው ሀብት ለማፈራት ማቀዳቸውን ነው የሚናገሩት።

ሌላኛዋ የድጋፉ ተጠቃሚ በጨርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ መዓዛ አክሊሉ ናቸው፡፡ የአራት ልጆች እናት ሲሆኑ ሕይወታቸውን ለመምራት በየሰው ቤቱ በመንቀሳቀስ የምግብ ማዘጋጀት፣ የልብስ ማጠብ፣ የመተኮስ እና ሌሎች የቤት ለቤት ሥራዎችን በመሥራት የልጆቻቸውን እና የእሳቸው ሕይወት ለማቅናት ዘወትር ይታትራሉ፡፡

በሚያገኙት ገቢ ልጆቻቸውን አስተምረው እንደነገሩም ቢሆን ሥራ እንዳሲያዟቸው በመናገር አሁን እኔ መኖር አለብኝ የሚሉት ወይዘሮ መዓዛ፤ በድጋፍ ባገኙት ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ በሚኖሩበት አካባቢ እንጀራ ጋግሮ በመሸጥ ሕይወታቸውን ለመቀየር ውጥን ይዘዋል፡፡

ወይዘሮ መዓዛ ህልማቸው ትልቅ ነው፡፡ እንጀራ ሽጠው ከሚያገኙት ገቢ የእለት ተዕለት ወጪን ከመሸፈን ባሻገር በባንክ በመቆጠብ ሥራቸውን ለማስፋፋትና ለሌሎችም የሥራ እድል ለመፍጠር አቅደዋል፡፡ እንዲሁም የሰው ልጅ ሆኖ የማይቸገር፤ የማያጣ የለም፤ ከውጣ ውረድና ልፋት ቀጥሎ ማጌጥም አይቀርም የሚሉት ወይዘሮዋ፤ ሰርተው ሲለወጡም ከእሳቸው በታች የሚገኙ ሰዎችን የመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡

ልጆች ለማሳደግ ለዓመታት ሲለፉ እንደኖሩ የሚናገሩት ወይዘሮ መአዛ “ልጆች መለስ ብለው እኔን በመደገፍ እንዳይቸገሩ አቅም እስከፈቀደ ጊዜ ድረስ ሰርቼ ማግኘትና ለሌሎች መትረፍ ነው ህልሜ” ይላሉ።

እንደፈለጉ ተንቀሳቅሰው ለመሥራት የእግራቸው ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ በአንድ ስፍራ ላይ ተቀምጦ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የሽንኩርት መፍጫ ማሽን በፍላጎታቸው መርጠው መውሰዳቸውን የሚገልጹት ደግሞ ሌላኛዋ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የድጋፉ ተጠቃሚ ወይዘሮ ማዕረግ ካሱ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ማዕረግ አሁን ባሉበት ሁኔታ ምንም ዓይነት ድጋፍም ሆነ የገቢ ምንጭ የሌላቸው መሆኑ አካል ጉዳተኛ ከመሆናቸው ጋር ተዳምሮ ሕይወታቸው እጅግ አክብዶባቸዋል፡፡

የሰው ልጅ ለመለወጥ የመሥራት ፍላጎትና ተነሳሽነት ካለው ከምንም ተነስቶ ትልቅ ደረጃ ይደርሳል የሚሉት ወይዘሮዋ፤ ባገኙት የሽንኩርት መፍጫ ማሽን በመኖሪያ አካባቢያቸው ሽንኩርት የመፍጨት ሥራን በመሥራት ሕይወታቸውን ለመምራት አስበዋል፡፡ ሃሳባቸው እንደሚሳካ እርግጠኛ የሆኑ ሲሆን ከሚያገኙት ገቢ በመቆጠብ አነስተኛ ምግብ ቤትም ለመክፈት አቅደዋል፡፡

የአካል ጉዳትም ሆኔ ሌላ ከአቅም ማጣት የበለጠ አያስቸግርም፤ የሚሉት የድጋፉ ተጠቃሚዎች በምንም ሁኔታ ውስጥ በመሆን ሰርቶ ማግኘትን መለወጥን ከፍ ማለትን ህልማቸው አድርገው ለእቅዳቸው መሳካት እንደሚጥሩ ነው ያስረዱት።

በአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ሕፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ነፃነት ዳባ እንደሚገልፁት፤ የተደረገው ድጋፍ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ችግር በመፍታት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ያለመ ነው። ድጋፉ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን እስካሁን ባለው ጊዜ ከ5ሺህ በላይ ሴቶች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ነፃነት ገለፃ፤ ሴት እናቶችንና የሚያስተዳድሯቸውን ቤተሰቦች በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም አካል የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡ ይህ ድጋፍም የቤት ውስጥ መገልገያ ቢሆንም የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ገቢ የሚያገኙበትን እድል የሚፈጥር ነው፡፡

ከቁሳዊ ድጋፉ በተጨማሪ ለሥራ ለመጀመር የሚያስችል ገንዘብ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ባለፉት ጊዜያትም የባንክ ደብተር እንዲከፍቱ በማድረግ ለሥራ መነሻ የሚሆን ገንዘብ እንዲቆጥቡ ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው፤ የዚህን ዓመት ድጋፍ ለየት የሚያደረገው በማህበር ተደራጅቶ ለመሥራት አስቸጋሪ የሆነባቸውን ሴቶችን ያቀፈና ከአኗኗራቸው ጋር ተስማሚ መሆኑ ነው ይላሉ።

ቴክኖሎጂዎቹ የሴቶችን ልፋት የሚቀንሱና ወጪ ቆጣቢ ናቸው። በቀጣይም ሴቶቹ በማህበር ተደራጅተው ለመሥራት የሚያስችላቸው መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ነፃነት፤ የተሰጡ ቁሳቁሶች ዜጎቹ በቀላሉ በመኖሪያ ቤታቸው መሥራት የሚያስችላቸው በመሆኑ በያሉበት ሆነው ከልጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ሳይርቁ መሥራት እንደሚችሉ ይጠቁማሉ፡፡

መሥራት እየቻሉ ማጣት እግር ከወርች ያሰራቸው እነዚህ እናቶች አንድም በኢኮኖሚ ራሳቸውን ችለው ከጥገኝነትና ከጠባቂነት መውጣታቸው ሌላ ደግሞ በሥራ በተነቃቃች እናት እጅ የሚያድጉ ልጆችን የሥራ ባሕል ማሳየት ይሆናል። ሰው ሰርቶ ማግኘት ከቻለ ምንም ዓይነት የኑሮ ዳገት የሚገፋ መሆኑን የሚናገሩት የድጋፉ ተጠቃሚዎች መንቀሳቀሻ ያጡ ሰዎችም እንደነሱ ተመልካች አግኝተው አቅም በፈቀደ ሥራ ይሰማሩ ዘንድ ተመኝተዋል። እኛም በእነሱ መልካም ምኞት ጽሑፋችንን ቋጭተናል። ቸር ይግጠመን።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You