ሀገራችን ሰላም ጠል በሆኑና ለማንም በማይበጁ ነጣጣይ ትርክቶች ስር ከወደቀች ሰንበትበት ብላለች:: በለው በሚሉና ወደሌላው ጣት በሚቀስሩ ተረት ተረት ታሪኮች ሰላሟንና አንድነቷን አጥታ በብሔር ቡዳኔ ተተብትባለች:: የትርክቶቹ ምንጭ ሳይታወቅ ሀገርና ሕዝብን ችግር ላይ ሲጥሉ ቆይተዋል:: ማን ፈጠራቸው? እንዴት ተፈጠሩ? የሚሉ ቅድመ ጥያቄዎችን ዘንግተን ለትርክቶቹ አባባሽ ምላሽ በመስጠት በመዳከር ላይ እንገኛለን::
ሰፊ ታሪክ፣ ሰፊ ብዙሀነት፣ እልፍ ባህል፣ እልህ ሥርዓት ያጸናት ሀገር፣ በባህል ውርርስ ፊተኝነትን ያገኘች ምድር በሴረኞች ጠብ በተደረገ ትርክት ውበቷን አጥታ በመንገዳገድ ላይ ትገኛለች:: ብዙሀነት የሚለው ጥንተ ስማችንን በብሔርተኝነት ተለውጦ ካብ ለካብ ተፈራርተን ቆመናል::
የጥላቻ ትርክት እንደሰደድ እሳት ነው:: ሰደድ እሳት ያገኘውን እየበላ ታሪክ የሚያበላሽ መሆኑ እሙን ነው:: የጥላቻ ትርክትም ያገኘውን እየጣለ እና እየገፋ አንድነትን በማላላትና ኢትዮጵያዊነትን በማደብዘዝ እርቃን የሚያስቀር ነው:: በዚህ ዓይነቱ ትርክት እስከዛሬም ብዙ ዋጋዎችን ከፍለናል:: በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የብኩርና ግፊያ ጀምረን እኛ የሚለውን የኃይልና የህብረት ስም ወደእኔ ለውጠን ከገዘፈ ማንነት ወደጠበበ እኔነት ተራምደናል:: በታሪክ ሽሚያ፣ በፖለቲካ ሽኩቻ ደም ተቀባብተን፣ ቂምና ቁርሾ ቋጥረን ለነገ ያስቀመጥናቸው እልፍ ቁርሾዎች አሉን::
በመጥፎ የምናወሳቸው የእርስ በርስ ጦርነቶች፣ የብሔርና የጎጥ ግጭቶች አጉል ትርክት የወለዳቸው ስለመሆናቸው ተጠራጣሪ አይኖርም:: እንዲሁም ደግሞ ለማንም ያልተቻሉ ደማማቅ ታሪኮችን የጻፍነው በበጎ ትርክት መሆኑ እንዳይረሳ:: አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ከአጉል ትርክት ወጥተን ሕዝባዊ ትርክት መተረካችን ዘርፈ ብዙ ዋጋ አለው:: ሰላም ለሚፈልገው ሕዝብና አንድነቱ እንዲመለስ ለሚመኘው ትውልድ ብዙሀነትን ያነገበ የጋራ ትርክት የፈረሰውን የሚገነባ፣ የላላውን የሚያጠብቅ ነው:: ለጀመርናቸው የሰላም መንገዶች፣ ለጀመርናቸው የእርቅና የተግባቦት መድረኮች በጎ ትርክት የማይናቅ ዋጋ አላቸው::
የተበላሸውን አስተካክለው በአዲስ ሕዝባዊነት ለመቀጠል ሲያቃቅሩን የነበሩ መሠረት የለሽ ተረት ተረት አሉባልታዎች መስተካከል አለባቸው:: በምትኩ አንድነትና ህብረብሔራዊነት የሚያብቡበት፣ ጥንተ ታሪካችን የሚታደስበት አግባቢና አስማሚ ታሪኮች ግድ ይሉናል:: ለዚህ ደግሞ ከመንግሥት ጀምሮ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት አለበት:: የሰላም ጉዳይ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው አይደለም:: የሀገር ጉዳይ፣ የትውልድ ጥያቄ በመንግሥት ወይም ደግሞ በሆነ አካል ብቻ እልባት የሚሰጠው አይደለም:: ጥምረትና ህብረት ያስፈልገዋል::
የጥላቻ ትርክት ፈጣሪዎች ትርክት ሲፈጥሩና ሕዝብን ከሕዝብ ሲለያዩ ተያይዘውና ተመካክረው ነው:: በአንድ ጊዜ አለያዩንም፣ በአንድ ጊዜ በስጋትና በፍራት እንድንተያይ አላደረጉንም:: አስበውና ተዘጋጅተውበት ነው:: እኛም አንድነታችንን ለመመለስና ኢትዮጵያዊነትን ለማስቀጠል በበጎ ትርክት መዘጋጀት አለብን:: ተያይዘንና ተጠላልፈን እኩይ ትርክት ፈጣሪዎችን የሚያሳፍርና ዳግም ጥፋት መሥራት ወደማይችሉበት ደረጃ እስኪደርሱ ድረስ ስለአብሮነታችን ማውጋት ይኖርብናል::
ለእንዲህ ዓይነቱ ነውር የማያዳግም ምላሽ ለመስጠት ከሀገርና ከሕዝብ ጋር የተነሱ እንደብሔራዊ ምክክር ያሉ በኮሚሽን ደረጃ የተቋቋሙ ተቋሞች ወደሥራ ገብተዋል:: ይሄ ብቻ ግን በቂ አይደለም:: ሌሎች ስለሀገርና ሕዝብ ግድ የሚላቸው ስለሰላም አበክረው የሚሰሩ ድርጅቶች፣ ተቋማት፣ ግለሰቦች የመፍትሔው አንድ አካል በመሆን ድምጻቸውን ማሰማት አለባቸው:: ዛሬ ላይ የምናዋጣት የሰላም መዋጮ ለነገ ነፃነታችንና አብሮነታችን ያላት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው:: እንደዘበት በተወረወሩ ቃላቶችና ንግግሮች ነው ዋጋ እየከፈልን ያለንው:: ለእንግልት የዳረጉን የሆነ ቀን በሆነ ሰው የተነገሩ፣ የተሰራጩ መሠረት የለሽ የራስ አመለካከቶች ናቸው::
እኛም እውነቱን መናገር አለብን:: ተደናግረው ያደናገሩን ትርክት ፈጣሪዎች፣ ተሳስተው ያሳሳቱን ጠላቶቻችን የሚያፍሩትና ከድርጊታቸው የሚቆጠቡት
ስንታረቅ፣ ስንግባባ፣ ስንወያይ፣ በአንድነት ስንቆም፣ ሕዝባዊነት ሲመለስ፣ እኛነት ሲያብብ፣ አብሮነት ሲጎመራ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለጥላቻ ትርክቶቻችን የአብሮነት ትርክት ስንፈጥር ብቻ ነው:: እንዲህ ካልሆነ አናሸንፋቸውም:: የእኛ መለያየት ለእነሱ ኃይል ነው:: የእኛ መራራቅ ለእነሱ ጉልበት ነው:: የምናሸንፋቸው ነውራቸውን የሚገልጥ የአንድነትና የአብሮነት የወንድማማችነትም ህብረት ስናበጅ ነው::
እኛ ኢትዮጵያውያን በማንም የምንከሽፍ አይደለንም:: ማንም የመሰለውን እየተናገረ የሚያቃቅረንና የሚያሰጋን ሕዝቦች አይደለንም:: ማን ምናለ እያልን በወሬና በአሉባልታ ጥንተ ህንደኬነታችንን የምንሰውርም አይደለንም:: በብዙ ፈተና ውስጥ አልፈን አብሮነታችንን ያስመሰከርን እንዳንለያይ ሆነን የጸናን የአንድ መዳፍ ጣቶች ነን:: በወሬ የማይፈርስ፣ በአሉባልታ በማይላላ ጽኑ ወንድማማችነት ውስጥ የቆምን ነን:: በጠበቀና በጠነከረ የአብሮነት ታሪክ ውስጥ ሀገርና ሕዝብ የሆንን ነን:: በተዋረሰና በተዋሃደ ቅይጥ ማንነት ውስጥ ነፃነትን የሠራን፣ ፍትህን ያወጅን፣ ለሰው ልጅ ሁሉ ደጀን የሆንን አስጠላይ ዋርካ ነን::
ማንም ተነስቶ በመካከላችን ልዩነትን እንዲፈጥር መፍቀድ የለብንም:: የሚማረውን ማስተማር የማይማረውን ደግሞ መቅጣት ስለኢትዮጵያዊነት የምንከፍለው ዋጋ መሆን አለበት:: ግፊያ በበዛበት በሻከረና በለዘበ ጉርብትና ውስጥ ወደፊት መራመድ አንችልም:: ከሁሉ አስቀድመን በመንገዳችን ላይ እንቅፋት ለሆኑ መጥፎ ትርክቶች መልስ እንስጥ:: እንቅፋቶቻችን ከመንገዳችን ላይ ገለል ሲሉ ነው ሰላምም ሆነ ልማት የሚመጣው:: ባልጸዳና ባልተስተካከለ ፖለቲካ ውስጥ፣ ባልተማመነና ባልተጎራበተ ማህበረሰብ ውስጥ ምንም ብንደክም ትርፍ አይኖረንም::
እንደእኛ እኮ የተመሳሰለና የተቃቀፈ ታሪክ ያለው ሀገር የለም:: ብዙ ነገራችን የተዋረሰና የተቀየጠ ነው:: እኔ ብለን ራሳችንን እንዳናገል በሆነ ትስስር ውስጥ ያረፍን ነን:: ብንለያይ እንኳን ተዋደንና ተከባብረን ነው:: ከሰማኒያ በላይ ብሔረሰብ፣ ከሰማኒያ በላይ ቋንቋና ከሰማኒያ በላይ ባህል ይዘን ኢትዮጵያዊነትን ማስቀጠል መቻላችን ብርቱነታችንን የሚያሳይ ገሀድ ነው:: ይሄ ጥንካሬ ለዘመናት መለያችን ሆኖ ቆይቷል:: ምክንያት ካስፈለገው እንደምክንያት የሚነሳው የጋራ ትርክታችን ነው::
አሁን ላይ ይሄ ጥንተ ስማችን እየጎደፈ የመጣው የጋራ ትርክት አጥተን የብቻ ትርክት በመጀመራችን ነው:: በሰፊ ሀገር ላይ የብቻ ትርክት ለያይና አራራቂ ነው:: የብቻ ትርክት ብዙሀነት የለውም:: የራስ ፍላጎትና አላማ የሚንጸባረቅበት ተጠጋግቶ የቆመውን ብዙሀነት የሚያቃቅርም ነው:: ከሁሉ በላይ አስከፊ ሆኖ የሚነሳው ኢትዮጵያዊነት የደበዘዘበት፣ ብሔርተኝነትና እኔነት ገኖ የወጣበት መሆኑ ነው:: ይሄ ልምምድ በሂደት ልክ አሁን ላይ በሀገራችን እየሆነ እንዳለው ሀገርን ወደመከፋፈል ሄዶ የእኔ የአንተ የሚል ሰጣ ገባን ያመጣል::
ሰፊ ሀገር የጠበበ ፖለቲካ፣ የጠበበ ፖለቲከኛ ጠንቋ ነው:: ከሰፊው ሕዝብ ውስጥ ራስን ብቻ ማውጣት፣ ከብዙሀነት ውስጥ የራስን ብቻ ማግነን ከእኩይ ትርክቶች በላይ በውንብድና የሚጠቀስ ድርጊት ነው:: በብዙሀነት ውስጥ የራስ ብቻ ታሪክ፣ የራስ ብቻ እውነት የለም:: መንዝረንና በርብረን የምናወጣው የብቻ ልዕልና የለም:: መንሸራተት ስንፈልግ ግን በዚህ እውነት ላይ ዘምተን እኔ፣ የእኔ ማለት እንጀምራለን:: በተዛነፈ ትርክት የታሪክ ሽሚያ፣ የብሔር ግፊያ እናደርጋለን:: መጨረሻችን መንሸራተትና ጸንቶ የቆመውን ማንሸራተት ይሆናል::
በሰፊ ሀገር ላይ የሚያስፈልገው ሰፊና ብዙሀኑን የነካ ትርክት ነው:: ሀገር አጥበን የምናሰፋው ብሔር የለም:: ኢትዮጵያዊነትን አሳንሰን የምናገዝፈው ማንነት አይኖርም:: መነሻችን ለመድረሻችን ወሳኝነት አለው:: ከሀገር ካልጀመርን፣ ከሕዝብ ካልተነሳን መንገዳገዳችን የማይቀር ነው:: የጥላቻ ትርክት ፈጣሪዎች ትርክት ሲፈጥሩ ሀገርን አያስተውሉም:: ከማንነት ነው የሚጀምሩት፣ ከብሔር ነው የሚነሱት:: በሀገርና ሕዝብ በኩል እኩይ አላማ እንደሌለ ስለሚያውቁ ሁልጊዜም መነሻቸውን የሚያደርጉት ብሔር ላይ ነው:: ብሔርን ተንጠላጥለው፣ ማንነትን አንጠልጥለው በአንዱ ላይ የበታችነትን በሌላው ላይ ደግሞ የበላይነትን በመፍጠር የሚያቧድኑ፣ ጎራ የሚያስፈጥሩ ናቸው::
በተቃራኒው የአንድነትና የአብሮነት ትርክት ፈጣሪዎች መነሻቸው ሀገርና ሕዝብ ነው:: ብርቱና ሉዓላዊ የሚሆኑት ሀገር ብለው ሲነሱና ሕዝብ ብለው ሲጀምሩ እንደሆነ ያውቃሉ:: እኚህ ከላይና ከታች የዘረዘርኳቸው የትርክት ፈጣሪዎች አካሄድ ሀገርን ለማፍረስና ሀገርን ለማጽናት የሚመርጧቸው አቅጣጫዎች እንደሆኑ ነው:: የእኩይ ትርክት ፈጣሪዎችን አካሄድ ማወቃችን የክፉዎችን አላማ ተረድተን የአብሮነት ትርክት እንድንፈጥር መንገድ ከመክፈቱም በላይ በብሔርና በማንነት የመጡብን ሁሉ የጋራ ጠላቶቻችን እንደሆኑ እንድንረዳም የሚያደርግ ነው::
መቼም የትም መነሻውን ማንነትና ብሔር ያደረገ ሃሳብ፣ እቅድ፣ አላማ እኩይ ነው:: መቼም የትም መጀመሪያውን ሀገር ያላደረገ ፖለቲካና ፖለቲከኛ እርባና ቢስ ነው:: በጎ ትርክት በመፍጠር ሂደት ውስጥ እንደመነሻ የምንወስዳቸው የታሪክ፣ የሥርዓት ማጣቀሻዎች ሂደቱ ዋጋ ያለው እንዲሆን ሚናቸው የበዛ ነው:: ፖለቲካውና ፖለቲከኞቻችን ራስ ላይ ብቻ ማንጸባረቃቸውን ትተው ብዙሀኑ ላይ የሚያርፍ ብርሃንን ይርጩ:: ትርክት ሲፈጥሩ ከራሳቸው ባይጀምሩና ኢትዮጵያን መሠረት አድርገው ቢጀምሩ፣ ሀገርና ሕዝብን ተንተርሰው ቢንጠራሩ፣ ትውልዱን ሳይዘነጉ ነገን እያሰቡ ቢናገሩ ብዙ ለውጦችን ማምጣት እንችላለን::
በብዙ አንድ ዓይነትና በጥቂት ልዩነት ውስጥ በኢትዮጵያ የምንጠራ ነን:: አንድነታችን ለኃይል ምንጭ ልዩነታችንን ደግሞ ውበት ሆኖን ብዙ ዘመን ተጉዘናል:: ቀጣይ እጣ ፈንታችንም ሊሆን የሚገባው ይሄ ነው:: ተለያይቶ የበረታ ሀገር የለም:: እንደሀገር የወደቀብንን የሰላም ጥያቄ፣ የማደግና ራስን የመቻል ፍልሚያ ከዳር ለማድረስ በጎ ትርክት ዋጋ አላቸው::
እንደ እውነቱ ከሆነ የጥላቻ ትርክቶች ሁላችንንም እንደነኩ ሁሉ በሁላችንም ተሳትፎ ነው የሚጠፉት:: ተናጋሪና አድማጭ ሆነን የራሳችንን የመፍትሔ ሃሳብ ሳናቀርብ ችግራችንን ማርገብ አንችልም:: ብሔራዊ ምክክር ሕዝባዊ መድረክን በማዘጋጀት ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል:: እኛም በመነጋገርና በመግባባት ኃላፊነታችንን መወጣት ቀዳሚ የቤት ሥራችን ሊሆን ይገባል:: በተዘጋጀው ነፃና ፍትሃዊ መድረክ ላይ ሃሳብ በመስጠትና ሃሳብ በመቀበል አብሮነታችንን የምናስቀጥለው እኛ ነን::
ብሔራዊ ምክክር በኮሚሽን ደረጃ ሲቋቋም የጥላቻ ትርክቶችን አስወግዶ ኢትዮጵያዊ ቀለሞችን ለማጉላት ነው:: ማን፣ መቼና እንዴት እንደፈበረካቸው በማናውቃቸው ድራማዊ አሉባልታዎች ዋጋ ከፍለናል:: እኚህ አፈ ታሪኮች በእውነትና በሀቅ ሕዝባዊነትንም በተዋሃዱ ትርክቶች ተቀይረው ራሳችንን ከእስራት ነፃ የምናወጣባቸው እንዲሆኑ ኃላፊነት እንውሰድ::
የጥላቻ ትርክቶች ወደሞት ካልሆነ ማንንም ወደ ሕይወት አይወስዱም:: ሰላም የሌለባቸው፣ የወንድማማች መገፋፋቶች የበረከተባቸው ታሪኮች ሥረ መሠረታቸው ቢፈተሽ ሆን ተብሎ የተበጀ፣ ወደአንድ ወገን ያደላ የጥላቻ ትርክቶች ይገኝበታል:: የናዚው መሪ አዶልፍ ሂትለር በአይሁዶች ላይ ሲነሳ መጀመሪያ ያደረገው በጀርመናውያን ልብ ውስጥ ስለአይሁዳውያን እኩይ ትርክቶችን መፍጠር ነበር:: እንዳሰበውም ስለአይሁዳውያን ረጅም ጊዜ በወሰደ የፈጠራና የአሉባልታ ታሪክ መጥፎ ትርክት ፈጥሮ በጀርመናውያን ልብ ውስጥ ነዛ::
ይሄ እኩይ ታሪክ በአራጋቢዎች ተራግቦ ነዶ በመቀጣጠል ብዙዎችን በላ:: በታሪክ አስከፊ የሆነውን ከስድስት ሚሊዮን በላይ ንጹሃን ያለቁበትን የሁለተኛውን የዓለም ጦርነትም ወለደ:: በሩዋንዳ የሆነውም ተመሳሳይ ነው፣ እንደዘበት በተነገረች አንዲት ትርክት ነው ሩዋንዳውያን መቼም ከማይረሱትና ከስምንት መቶ ሺ በላይ ዜጎቻቸውን ላጡበት ታሪካዊ ቀውስ የተዳረጉት:: ከራሳችንም ሆነ ከሌሎች ተምረን በአንድነት የምንራመድበትን የፍቅር ሰርጥ እናብጅ ማብቂያ መልዕክቴ ነው::
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም