ያልታሰበ ፈተና የገጠመው

ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል፣

በማለት ሰለሞን ቀድሞ ተናግሮታል።

ሳትደፈር ኖራ ጨረቃም እርቃ፣

በሰው ተፈተነች ጊዜዋን ጠብቃ።

( ከክቡር ዶክተር መሀሙድ አህመድ የቆየ ዘፈን የተወሰደ )

አዎ፣ አሁን ያለንበት ጊዜ ለአሜሪካዊው ዶላር “ጥሩ የሚባል ጊዜ አይደለም። ወይም፣ የአሁኑ ወቅት እንደ ቀድሞው ሁሉ ዶላር ደረቱን ነፍቶ፣ ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ፤ በአራቱም ማእዘን የሚንጎማለልበት የተደላደለ ጊዜ አይደለም። ይህ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዶላር አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ጊዜ ነው ቢባል ቢያንስ እንጂ አይበዛበትም።

ከአንዳንድ የኢኮኖሚክስ ልሂቃን በስተቀር፣ እስከ ዛሬ ማንም ሰው ዶላር እንዲህ አይነት ፈተና ይገጥመዋል ብሎ ያሰበ፤ እንዲህ ዶላርን ከመሰረቱ የሚነቀንቅ ጊዜ ይመጣል ብሎ ያለመ ሰው አልነበረም። ምናልባትም የጦር መሳሪያው እሽቅድድም እያየለ ይሄድ ይሆናል እንጂ ዶላር እግሩ ድረሰ ጠላት ዘልቆ ይፈትነዋል፤ ጉሮሮውን ያንቀዋል ብሎ የገመተ ስለ መኖሩ አፍ ሞልቶ ለመናገር መረጃ የለም። የሆነና እየሆነ ያለው ግን ይኸው ነው።

መሀሙድ አህመድ የኒል አርምስትሮንግን ጨረቃ ላይ ማረፍ ተከትሎ ያዜመውና ለዚህ ጽሑፍ መግቢያነት የተጠቀምንበት አንጓ እንደሚያመለክተው ዶላርም በብሪክስ እየተፈተነ ይገኛል።

ወቅታዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ በአራት፣ በኋላም በአምስት ሀገራት ኅብረት የተመሰረተው ብሪክስ (BRICS) በአሁኑ ሰአት በሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን እየተመራ ሲሆን፤ በፑቲን አማካኝነት ፈጣንና ቆራጥ የሆኑ እርምጃዎች እየተወሰዱና እምዬ ዶላርን ወደ ጠርዝ የሚገፉ ውሳኔዎች እየተላለፉ፤ ለ55 ዶላርም 1 ብሪክስ ምንዛሪ (ex­change rate) ተቆርጦለት ይገኛል (በዚህ ተመን መሰረት 1 ዶላር = 0∙018181818∙∙∙ መሆኑን ልብ ብለዋል?)

ብሪክስ የራሱን የመገበያያ ገንዘብ (ልክ እንደ ዩሮ ሁሉ ማለት ነው) ለመፍጠር ዱብ ዱብ ማለቱን ካስታወቀ ጀምሮ እነሆ እለት በእለት ፍጥነቱን በመጨመር ባልተጠበቀ ሁኔታ የራሱን የመገበያያ ገንዘብ (ብሪክስ ከረንሲ) ይፋ አድርጓል።

ይፋ ማድረጉን ተከትሎም አባል ሀገራቱ ከመገበያያ ገንዘብነቱ ይልቅ የጦር መሳሪያነቱ ያየለውን ዶላር ገሸሽ አድርገው የብሪክስን ገንዘብ እንዲገለገሉ ጥሪ አስተላልፏል። በጥሪውም መላው አፍሪካ እና ኤዥያ ተካትተዋል።

ፑቲን ከግለሰቦች ጀምሮ ማንኛውም ሀገር ብሪክስን በቀላሉ መጠቀም እንደሚችል ይፋ ያደረጉ ሲሆን፤ በተለይ $34∙4 ትሪሊዮን እዳ የሚጨፍርባቸው በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ፊታቸውን በአስቸኳይ ከዶላር ወደ ብሪክስ እንዲያዞሩ አሳስበዋል። የብሪክስ ባንክም (ኤንዲቢ) ለታዳጊ ሀገራት ልማት የሚውል የ500 ቢሊዮን ዶላር ብድር አዘጋጅቻለሁ ነው የሚለው።

እውን ከሆነ እ.አ.አ1792 ጀምሮ፣ በዶላር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእሱ ውጪ የድንበር ተሻጋሪ ግብይት ይከናወን ዘንድ ስምምነት (trade deal) ላይ የተደረሰ ሲሆን፤ ይህ ስምምነትም በብሪክስ አባል ሀገራት (በሩሲያ እና ቻይና) መካከል የተደረገ፣ ከ$260 ቢሊዮን በላይ ግምት ያለው ስምምነት ነው። በዚህ ስምምነት መሰረት የሁለቱም ሀገራት ገንዘቦች በእኩል የምንዛሪ ዋጋ ሥራ ላይ የሚውሉ ሲሆን 95 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍነው የቻይናው ዩዋን፤ 5 በመቶውን የሩሲያው ሩብል ነው።

ይህ የዓለምን የሚዲያ ምህዳር እያንቀጠቀጠ ያለ የብሪክስ ውሳኔ በወደ አሜሪካና ወዳጆቿ ዘንድ ድንጋጤን የፈጠረ ሲሆን፤ በተለያዩ መንገዶች እሰጥ አገባው እንደ ተጧጧፈ ይገኛል። “BRICS: $260 billion in trade without a single dollar″፤ BRICS makes a $260 bil­lion trade transaction using local currencies እና መሰል ርእሶች ሚዲያዎችን በመናጥ ላይ ናቸው።

ሩሲያ በአመራሩ፣ ቻይና በኢኮኖሚው፣ ሌሎች በአባልና አጋርነታቸው ብሪክስን ከፍጥነቱ በላይ እያፈጠኑት ያሉ ሲሆን፤ አባል ለመሆንም ከዓለም ዙሪያ የማመልከቻ መአት እየተግተለተለ ይገኛል። (በኤፕሪል ብቻ ከ40 በላይ ማመልከቻዎች ቀርበዋል።)

በተለይ ቻይና ዶላርን ለመጣል አስቀድማ ያሰበችበት ለመሆኑ በርካታ ምልክቶች ያሉ ሲሆን፤ ለዚህም 4ሺህ 300 ቶን የወርቅ ወቄት (ounce) ክምችት ያላት መሆኑን የቻይና ሕዝብ ባንክ (PBOC) ያስታወቀ ሲሆን፤ (ይህ ሀሰት ነው፤ ከዚህ በላይ አላት የሚሉ ወገኖች እንዳሉ ሆነው)፣ ይህም በአሁኑ የወርቅ ዋጋ (1 ወቄት $1ሺህ 974 ነው) $338∙5 ቢሊዮን ይሆናል። ይህም (ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው) ዶላርን ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ የራሱ የሆነ አቅም አለው፤ ወይም ቻይና ምንም አይነት ዶላር ሳያስፈልጋት ራሷን ችላ እንድትቆም የማድረግ አቅም አለው እየተባለ ነው።

ይህ የቻይና ዶላርን “ወግድ! የማለት (ዲ-ዶላራይዜሽን) ጉዳይ ከመንግሥቱም አልፎ ሕዝቡ ዘንድ የሰረፀ ሲሆን፤ ፍቃዱ ከተማ የተባሉ ፀሐፊ ሰሞኑን ከቻይና ቆይታቸው በኋላ በጉዞ ማስታወሻቸው (ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም) ላይ ያስነበቡን በራሱ የሚነግረን ነገር አለው።

ፍቃዱ “ዶላር ሞገሱ የተገፈፈባት ቻይና በሚል ርእስ ስር እንዳሰፈሩት᎓- እግረ መንገዳችንን ወይም ጉዳይ ገጥሞን በኢትዮጵያ ሆቴል፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲሱ ሕንፃ ወይም ጋንዲ አካባቢ ስንገኝ “ቼንጅ ፈልገው ነው?፤ “ያ ነገር አለ? ወዘተ የሚሉ በርካታ ጥሪዎች ከዚህም ከዚያም ይጎርፉልናል፤ ከእነዚህ ጥያቄዎች ጀርባ ያሉ ጉዳዮች ዶላር እና የውጭ ምንዛሪ ናቸው።

በወርቃማው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃ የውጭ ምንዛሪ ለመጠየቅና ለማግኘት ያለውን ግፊያና ትርምስ ተመልክቼ ቻይና ስሄድ የገጠመኝ ነገር እጅግ ተቃራኒ ነበር። በብርቱዎች ቻይናውያን ዘንድ ዶላር ለመዘርዘር ጥቁር ገበያን ደፍሮ የሚሞክር የለም። ዶላር መመንዘር የፈለገ በኢቲኤም አንዱን የአሜሪካን ዶላር በ5.25 የቻይና ዩዋን ይመነዝራል። ከዚህ ውጪ ሌላ ምንም ዓይነት አማራጭ የለም።

ከዚህም ባለፈም አነስተኛ ሱቅ ተሄዶ እንኳ ዕቃ ለመግዛት በዶላር ልክፈል ቢባል ፈላጊ የለውም። ቻይናውያኑ ዶላሩን ተመልክተው የሚያሳዩት የንቀት ገጽ ሠርተውና ለፍተው የዶላርን ገናናነት ገደል እንደከተቱት ማሳያ ይመስለኛል።

ይህ የአቶ ፍቃዱ የቻይና ትዝብት አንዳንድ አፍሪካ ሀገራት ውስጥ እንዳለም ሰምተናል።

ለዓመት በዓል የመጣና ኑሮውን በሌሴቶ ያደረገ የቅርብ ሰው እንደ ነገረን ከሆነ፣ በሌሴቶ ዶላር ገንዘብ ስለ መሆኑም እንኳ ልብ የሚለው የለም። ሌሴቶ ዶላር ይዞ መገኘት ትርፉ የምንዛሪ ያለህ ብሎ ሲንከራተቱ ከመዋል ያለፈ ፋይዳ የለውም። ሲንጋፖርም ባለ ዶላር ቱሪስቶችን ከማስተናገድ ከተቆጠበች ቆየች። እንደ አጠቃላይ ሲታይም፣ ከእ.አ.አ 2020 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዶላር በ25 በመቶ ቀንሷል።

በመጨረሻም፣ እ.አ.አ በ2009 የፖለቲካ ስብሰባ በማድረግ በተጀመረው፣ በብሪክስ ጥምረት ውስጥ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር ብሔራዊ ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱም ሆነ፤ ትኩረቱን በግብርናና ቴክኖሎጂ ላይ ያደረገ በብሪክስ ጥምረት ማዕቀፍ ስር የኢትዮጵያና የሩሲያ የምሁራንና የተመራማሪዎች ጉባኤ መካሄዱ፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በቅርበት በመሥራትና በመቀናጀት ሀገርና ሕዝብን የሚጠቅም ሥራ መሥራት እንዳለባቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ማስታወቁና የመሳሰሉት ቁልፍ ጉዳዮች ያለ ምክንያት አይሆኑም እና ሁሉንም ወደ ፊት የምናየው ይሆናል።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You