የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ጥሪ ባለ ታሪክ የሆነን ሕዝብ ለሌላ የታሪክ ከፍታ የሚያበቃ ነው !

የአንድ መንግሥት ሆነ ቡድን ሕዝባዊነት የሚገለጸው ለሕዝብ ካለው እውነተኛ ተቆርቋሪነት እና ከዚህ ተቆርቋሪነት የሚመነጭ የሕዝብ ተጠቃሚነት ለማስፈን ከሚደረግ ጥረት ነው። ከዚህ ውጪ ስለ ሕዝብ ሆነ ሕዝባዊነት የሚደረጉ ትርክቶች ሕዝብን ያልተገባ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ ምንም ፋይዳ እንደሌላቸው ይታመናል።

በተለይም ሕዝባዊነትን ፣ የጥቅም መሸቀጫ ሸቀጥ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ፣ በሕዝብ ስም የሚያደርጉት የትኛውም እንቅስቃሴ የሚኖሩበትን ማህበረሰብ ያልተገባ ዋጋ የሚያስከፍል እና ማህበራዊ ጉዞውን የኋልዮሽ የሚጎትት ነው።

በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በትውልዶች መሰላሰል መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ተፈጥሯዊ ተስፈኝነት ፈተና ውስጥ በመክተት ትውልዶቹ በነገዎቻቸው ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ ፈተና ይሆናል፤ ስለራሳቸው እና ስለማህበረሰባቸው ያላቸውን አመለካከት ያጠለሻል።

ይህ እውነታ ለእኛ ኢትዮጵውያን እንደ አዲስ የሚተረክ አይደለም። እንደ ሀገር በመጣንባቸው ረጅም የሀገረ መንግሥት ታሪካችን ውስጥ ሲፈታተነን የቆየ ፣ ብዙ ያልተገባ ዋጋ ያስከፈለን ፣ ዛሬም ላለንበት ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች በዋነኛነት እንደ ምክንያት የሚጠቀስ ነው።

በሀገሪቱ በቅርብ ያሉትን ስድስት አስርት ዓመታት ብንወስድ እንኳን፤ በሕዝብ እና በሕዝባዊነት ስም የተነሱ ግለሰቦች እና ቡድኖች ሀገሪቱን እንደ ሀገር የህልውና ስጋት እስክትወድቅ ድረስ ዋጋ ያስከፈሉ ፈተናዎች ውስጥ ከተዋታል። በዚህም ብዙ ተስፈኛ ትውልድ እስከነ ብሩህ ተስፋው ለህልፈት ተዳርጓል።

እንደሀገር በየዘመኑ የተሞከሩ የለውጥ ንቅናቄዎችም የታሰበውን ያህል ፍሬ አፍርተው ትውልዱ በብዙ የናፈቀውን ሀገራዊ ብልጽግና ማምጣት ሳይቻል ቀርቷል። ከዚያ ይልቅ የተለያዩ ሀገራዊ የለውጥ መነሳሳቶች በተለያዩ ስሞች በሚጠሩ ነጻ አውጪዎች ተጠልፈው ሀገር እና ሕዝብ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል ሆኗል።

ከዚህ ጥላ ሆኖ ከሚከተለን ሀገራዊ ችግር ባለመማራችን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በሕዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች፤ በብዙ ተስፋ እና በብዙ ዋጋ ለውጡን አምጦ የወለደውን ሕዝብ ተጨማሪ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍል አድርገውታል። ለውጡን በሕዝብ ስም በማንገጫገጭ ተፈጥሯዊ የጉዞ ፍጥነቱን እንዳይጓዝ ተግዳሮት ሆነውታል።

እነዚህ በሕዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች እንቆረቆርለታለን የሚሉትን ሕዝብ ለውጥ ለማዘግየት ብዙ ለፍተዋል፣ ነፍጥ አንግበው በማሳደድ ፣ በማፈን፣ በመዝረፍ እና በመግደል ለችግር ዳርገውታል፤ ዛሬም በስሙ በተመሳሳይ መንገድ ሰላማዊ ኑሮውን እየተገዳደሩት ነው።

እነዚህ ቡድኖች ስለ ሕዝብ እና ሕዝባዊነት እያወሩ የሕዝቡን የልማት ሥራዎች ከማደናቀፍ ጀምሮ የሕዝቡን የልማት መሻት የሚገዳደሩ ተግባራትን በአደባባይ እያከናወኑ ነው። ይህን የጥፋት ተግባራቸው ለእኩይ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ አቅም አድርገው ሲንቀሳቀሱም ማየት የተለመደ ሆኗል።

ይህ አይነቱ በሕዝብ ስም የሚደረግ ወንጀል ፤ በዚህ ትውልድ ማብቂያ ሊበጅለት ይገባል፤ በተለይም በእነዚህ ቡድኖች የጥፋት ትርክት አውቆም ይሁን ሳያውቅ ነፍጥ አንስቶ በገዛ ወገኑ ተስፋ ላይ እየተኮሰ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል እያደረገ ያለው ምን እንደሆነ ቆም ብሎ ሊያስብ ይገባል።

የአንድን ሕዝብ ሰላማዊ የለውጥ መነቃቃት የሚያደበዝዝ የነፍጥ ተልዕኮ ለማስፈጸም የሚደረግ እንቅስቃሴ እንወክለዋለን በሚሉት ሕዝብ ዛሬ ላይ ብቻ ሳይሆን በልማት ተስፋ የሚያደርጋቸውን ብሩህ ነገዎች እንደሚያደበዝዝ አግባብ ባለው መንገድ ማየት ተገቢ እና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነው።

ለዚህ ደግሞ እነዚህ ኃይሎች ከሁሉም በላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተደጋጋሚ እንደ አንድ ኃላፊነት የሚሰማው የለውጥ መሪ ለሚያቀርቡት የሰላም ጥሪ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት፤ የሕዝባቸውን የመልማት መሻት ተጨባጭ በሚያደርግ የልማት ተግባር ላይ መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል።

ይህ አይነቱ ውሳኔ ራስን ከጥፋት ከመታደግ ባለፈ፤ ስለ ሀገር እና ስለሕዝብ ተስፋ የሚከፈል ትልቅ ዋጋ ያለው ጭምር ነው። እንደ ትውልድም ራስን ከተጠያቂነት በማዳን፤ ለራስ የተሻለ ታሪክ ማስቀመጥ የሚያስችል፤ ከሁሉም በላይ አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር ለሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ስኬት ባለ ዕዳ ከመሆን የሚያድን ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በጫካ ለምትገኙ ወንድሞች መገዳደል ይብቃን፤ ጥፋት ይብቃን፤ የኢትዮጵያን ሕዝቦች በእኩል የማያከብር ጉዞ ስለማይጠቅመን ኑ ወደ ክልላችሁ ተመለሱ፣ ክልላችሁን አልሙ፣ ሰላማችሁን ጠብቁ። ያን ስታደርጉ እኛም በሙሉ ልብ ከጎናችሁ ሆነን አብረናችሁ እንሠራለን፤ በማይገባ ነገር መገዳደል ይበቃል” ማለታቸው ይህንኑ እውነታ ታሳቢ ያደረገ ነው።

“ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፤ በብዙ ዓይነት የሰላም እጦት ውስጥም ቆይታለች፤ አሁን የሚያስፈልገን ነፃነት፣ ወንድማማችነት፣ እና መከባበር እንዲሁም እኩል ዜጋ ሆኖ ኢትዮጵያን በጥረት መገንባት ነው፤ ይህችን ታላቅ ሀገር ክብሯን ጠብቀን ለልጆቻችን ማሻገር እንድንችል ከጎናችን ሁኑ “ሲሉ ለአማራ ሕዝብ እና መንግሥት ጥሪ ማቅረባቸው የአማራ ሕዝብ በሀገረ መንግሥት ምስረታው የነበረውን ትልቅ ታሪክ፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት እንዲደግመው ለሚያስችል፤ ሕዝብን ለሌላ የታሪክ ከፍታ የሚያበቃ ነው!

አዲስ ዘመን  ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You