
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በተካሄደው አንድ የዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ሴቶች በፖለቲካው ዓለም እየተሳተፉ ቢሆንም ከዚህ የላቀና ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል የሚል ንግግር አድርገው ነበር፡፡
በተለይ ሴቶችን በውሳኔ ሰጪ ቦታዎች ላይ ያላቸውን ድርሻ ከፍ በማድረግ ፍትሐዊ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባ እሙን ነው። ለውጤታማ የማህበረሰብ ዕድገት በየተቋማቱ የሚገኙ ሴት አመራሮችን ማብቃትና በውሳኔ ሰጪነት ረገድ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑም አያጠያይቅም።
በዚህ ረገድ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የሴቶችን አመራርነት አቅም ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። አካዳሚው ከቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የሴቶችን የአመራርነት አቅም የሚያሳድግ ተከታታይ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ተሳታፊ ከሆኑ መካከል የማህበራዊ ችግር ተጎጂዎች ማገገሚያ ልማት ማዕከል ሥራ አስኪያጇ ሲቲና ጅብሪል አንዷ ናቸው።
አካዳሚው የሴት አመራሮችን የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም በማጎልበት የአመራርነት ጥበብን ለማሳደግ የሚረዱ የተለያዩ ክህሎቶችን እንዲቀስሙ እየረዳቸው መሆኑን ይናገራሉ።
ሴቶች በአመራር ክህሎት ዘርፉ አዳዲስ ዕውቀት እንዲገበዩ፣ የእርስ በእርስ ልምድና ተሞክሮዎቻቸውን እንዲለዋወጡ እንዲሁም ሳይንሳዊ ንድፈ ሃሳቦችን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር የአመራር ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚረዳ ዕውቀት መቅሰማቸውን ይገልጻሉ።
የተለያዩ ሴቶች ተመሳሳይ ስልጠናዎች ማግኘት ቢችል የእንስቶችን የአመራር ብቃት በማሳደግ ለሀገራቸው ይበልጥ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበትን ዕድል ማስፋት ይቻላል ሲሉ ያስረዳሉ።
ስልጠናውን መውሰድ ከጀመሩ በኋላ በአመራር ክህሎታቸው ከቀን ወደቀን መሻሻል እያሳዩና፣ የውሳኔ ሰጪነትና በራስ መተማመናቸው እያደገ መምጣቱን የሚናገሩት ደግሞ ከኢትዮጵያ ስታስቲክስ ኤጀንሲ የመጡት ወይዘሮ ሶርሴ ጉተማና ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ተመልምለው በስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት ወይዘሮ ንግስት ኃይሉ ናቸው።
ለሴቶች የአመራር ጥበብ ዓይን ገላጭ በሆነው ተከታታይ ስልጠና ለወራት የተግባር ልምምድ መውሰዳቸውን ገልጸው፤ አካዳሚው ብቁ አሰልጣኞችን በመመደብ ዕውቀት እንዲቀስሙ የሚያደርግበት መንገድ በሕይወታቸውና በሥራ ውጤታማነታቸው ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው ይላሉ።
ሴት ልጅ ከበድ ያለ የቤተሰብ ኃላፊነት ቢኖርባትም ከሠራች ደግሞ የአመራርነት ሚናዋን በብቃት መወጣት እንደምትችል የሚያስገነዝብና በሳይንሳዊ ዕውቀቶች የተደገፈ ትምህርት እያገኙ በመሆኑ ደስተኛ መሆናቸውን ነው ሰልጣኞቹ የሚናገሩት።
በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የሴቶች አመራር ፕሮጀክት ማናጀር የሆኑት አቶ መስፍን በኃይሉ እንደሚያስረዱት ደግሞ፤ ለሴት አመራሮቹ የሚሰጠው ዘርፈብዙ ስልጠና በሙከራ ትግበራ ላይ ያለ ሲሆን፤ ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ ፕሮጀክት ነው።
በመንግሥትና በልማት ድርጅቶች የሚሠሩና በመካከለኛ አመራርነት ደረጃ የሚገኙ 60 ሴት አመራሮች ላይ ትኩረት ያደረገ ተከታታይ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ነው የሚገልጹት።
70 በመቶው የተግባር፣ 20 በመቶው ደግሞ ኔትወርኪንግና ግንኙነት ፈጠራ ስልጠና ሲሆን 10 በመቶው ብቻ የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ላይ እንደሚያተኩርም ያስረዳሉ።
ከስልጠናው ባሻገር ሴቶች አቅማቸውን የሚያሳድጉባቸው የእርስ በእርስ ግንኙነት ማጎልበቻ መድረኮች፣ የትላልቅ ተቋማት ጉብኝት መርሀ ግብሮችና የልምድ ልውውጦች እንደሚከናወኑም ነው ያመላከቱት።
እንደ አቶ መስፍን ከሆነ፤ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የሴት አመራሮች አቅም ግንባታ ስልጠና ፕሮጀክት በመጨረሻ ውጤታማነቱ ሲረጋገጥ በዘላቂነት የአካዳሚው ዋነኛ ሥራ ሆኖ እንዲቀጥል ይደረጋል።
ከፕሮግራሙ የሙከራ ትግበራ በኋላ የሴት አመራሮች በውሳኔ ሰጪነት፣ በራስ መተማመናቸው እንዲሁም የአመራር ጥበብና ክህሎታቸው በእጅጉ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ያስረዳሉ።
ፕሮጀክቱ ሰልጣኞች በሥራ ቦታቸው ላይ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች የሚሻገሩበትን ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማጠናከር ከመካከለኛ ደረጃ ወደከፍተኛ ደረጃ አመራርነት እንዲሸጋገሩ የሚረዳ መሆኑን አቶ መስፍን ያስገነዝባሉ።
በየተሰማሩበት መስክ ዕውቀትን በመጠቀም ለላቀ ውጤት እንዲረባረቡና ለሌሎችም አርዓያ እንዲሆኑ የሚያስችለው ስልጠና በዘለቄታዊነት በማቅረብ የሴት አመራሮችን አቅም ለማጎልበት ጥረት እንደሚደረግም ነው ያመላከቱት።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም