በተስፋና በስጋት የታጠረው የዱኤሻገላ አርሶአደሮች የሙዝ ልማት

አቶ ሹክራላ ሃጂሉል ባሮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን ሻሸጎ ወረዳ የዱኤሻገላ ቀበሌ አርሶ አደር ናቸው። እሳቸውም ሆኑ መላው የዱኤሻገላ አርሶ አደሮች በቆሎና መሰል አዝዕርቶችን በአመት አንዴ ብቻ ያመርቱ ነበር። ይህ ደግሞ እንኳን ገበያ አውጥተው ሊሸጡት ይቅርና ለቤተሰባቸውም በቂ አልነበረም።

በዚህ ምክንያት ሁልጊዜም ቢሆን የመንግሥት እጅ ጠባቂ ነበርን ሲሉ አቶ ሹክራላ ይገልጸሉ። ከአራት ዓመታት ወዲህ በክልሉ በተፈጠረው መነቃቃት ሌሎች ሰብሎችንና ፍራፍሬዎችን እንዲያመርቱና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሰፊና ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናወናቸውን ያመለክታሉ።

በተለይም ደግሞ የአካባቢያቸው የአየር ንብረት ለፍራፍሬ ምርት ምቹ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እሳቸውና ሌሎች የተመረጡ አርሶአደሮች አርባ ምንጭ ሄደው ተሞክሮ መቅሰማቸውን ይጠቁማሉ። የሙዝ ችግኝ አምጠተው በማሳቸው ላይ ተከሉ፤ ብዙ ጊዜ ሳይወስድም ፍሬውን ማየት መቻላቸው ይበልጥ ትኩረታቸውን በሙዝ ችግኝ ላይ እንዲያደርጉ እንዳነሳሳቸው ይገልፃሉ። እናም ማሳቸውን በማስፋፋት ከቤት ፍጆታ አልፎ ለገበያ በማቅረብ የገቢ አቅማቸውን ለማሳደግ እንዳስቻላቸው ያብራራሉ።

‹‹መጀመሪያ ላይ ሙዝ አምጥቼ ስተክል ብዙ የአካባቢያችን አርሶአደሮች ተቃውመውኝ ነበር፤ ጥቂት የማይባሉትም ለትከስር ትችላለህ ብለው አስፈራርተውኛል፤ ሆኖም ዘጠኝ ወር ባልሞላ ጊዜ ምርት ማየት ስጀምርና በሙዙ ተጠቃሚ መሆን ስንችል አመለካከታቸው ተቀየረ፤ የእኔን ተሞክሮ አይተው ብዙዎቹ ችግኝ እንድሰጣቸው ጠይቀውኝ ተክለዋል›› ይላሉ። በዋናነት ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት የብላቴን ወንዝ በመጠቀም በመስኖ ማልማት በመቻላቸው ውጤታማ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአካባቢው ዋነኘና ብቸኛ የመስኖ አውታር የሆነው የብላቴ ወንዝ ግድቡ በመሰበሩና አቅጣጫውን ከመሳቱ ጋር ተያይዞ በመስኖ የሚመጣላቸው ውሃ መመናመኑን ጠቅሰው፣ በዚህ ምክንያት በተለይ አዳዲስ የተከሏቸው የሙዝ ችግኞች የደረቁባቸው መሆኑን ያስረዳሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ ቶሎ እልባት ካልተሰጠው የማሳቸውን ሙዝና ሌሎች ፍራፍሬዎች በሙሉ እንዳይጠፋባቸው ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ነው ያብራሩት።

ሌላው አርሶአደር ይቴቦ ሽጉጤ በበኩላቸው ፤በክልሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በተጀመረበት ወቅት የቀበሌው ሊቀመንበር ሆነው ሰርተዋል፤ ሙዝ የማልማት ሃሳብ በግብርና ቢሮው ሲቀርብ አርሶአደሩ ፈፅሞ ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልነበረ አርሶ አደር ይቴቦ ያስታውሳሉ። የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ከተሰራ በኋላ እሳቸው ለሌሎች አብነት ለመሆን በማሰብ ቀድመው በራሳቸው ማሳ ላይ ሙዝ መትከላቸውን ይጠቁማሉ።

ሙዙ እስከሚያፈራ ድረስም ጎን ለጎን ቶሎ የሚደርሱ እንደጎመን ያሉ ሰብሎችን በመትከል ተጠቅመዋል። ‹‹ሙዙ ከሰባት ወር በኋላ ምርት መስጠት የጀመረ ሲሆን፤ የመጀመሪያውን የምስራች ያየነው በእኔ ማሳ ነበር›› ሲሉ ይናገራሉ። ይህንን ያዩ አርሶአደሮች መነሳሳት ተፈጥሮባቸው ችግኝ ከእሳቸው ወስደው መትከላቸውን ገልጸዋል።

አርሶአደር ይቴቦ እንደሚሉት፤ መጀመሪያ ላይ ሰባ የሙዝ ችግኝ ብቻ የተከሉ ሲሆን፤ ውጤቱን ካዩ በኋላ ግን የሙዝ ልማቱን በማሳቸው ላይ አስፋፍተዋል። በተጓዳኝም ሌሎች የጓሮ አትክልቶችን የሚያለሙ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምርቱ የቤተሰባቸውን የምግብ ፍጆታ ሙሉ ለሙሉ ማሟላት አስችሏቸዋል። አንዱን የሙዝ ግንድ ከ400 እስከ 500 ብር በመሸጥ ከሳምንት ሳምንት የማይቋረጥ የገቢ ምንጭ ሆናላቸዋል።

ከሙዙ ባሻገር አቦካዶና ቡና ጭምር አምርተው በመሸጥ የገቢ አቅማቸውን የሚሳድጉበት እድል ተፈጥሮላቸዋል።ከዚህ ባሻገርም ከእሳቸውና ከሌሎች አርሶ አደሮች ማሳ ዘጠኝ ሺ የሙዝ ችግኝ በማሰባሰብ ለወረዳው የምግብ ዋስትና በመሸጥ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉበትን ሁኔታ ጠቅሰዋል።

‹‹ዘንድሮ በመስኖ ግድቡ ላይ በጎርፍ በደረሰ ጉዳት መቀልበሻው በመሰበሩ የውሃ እጥረት አጋጥሞናል፤ በዚህ ምክንያትም ምርት ቀንሶብናል፤ ችግኝም እጥተን መሸጥ አልቻልንም›› የሚሉት አርሶአደር ይቴቦ፤ ከዚህ ቀደም በስንዴ ይሸፈኑ የነበሩ ማሳዎች አሁን ላይ በተከሰተው ችግር ፆም ያደሩበት ሁኔታ መፈጠሩንም ጠቁመዋል። ይህም በአርሶአደሩ ህይወት ላይ ስጋት የጋረጠበት መሆኑንና ቶሎ መፍትሔ ካልተሰጠው ችግሩ ከዚህም በላይ ሊብስ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ቀድሞም ቢሆን ሲያንገራግር የነበረው የአካባቢው አርሶአደር ሰፊ የአመለካከት ክፍተት ያለበት መሆኑን ጠቅሰው፣ የክልሉ አመራር ግድቡን ከመጠገን ባለፈ አርሶአደሩ ላይ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መስራት እንደሚገባው አርሶአደር ይተቦ ያስገነዝባሉ። ‹‹በተለይም በክላስተር ተደራጅቶ ማልማት ያለውን ጠቀሜታ አርሶአደሩ በአግባቡ ባለመገንዘቡ ምክንያትና ሁሉም በተናጠል የሚለፋ በመሆኑ ብዙ ሃብትና ጉልበት እየባከነ ነው፤ ተደራጅተን ብንሰራ ግን በዋናነት በገበያ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን እንችላለን፤ ይህንን በሚመለከት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራት ይገባል›› ሲሉም ያክላሉ።

የሻሸጎ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት እርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደረጀ ሜጊሶ በበኩላቸው፤ በዱኤሻገላ ቀበሌ ከብላቴ ወንዝ በሚገኘው ውሃ 4 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ ሙዝ እንዲሁም 371 ሄክታር መሬት ላይ ደግሞ የበጋ መስኖ ስንዴ ይለማ እንደነበር ይጠቅሳሉ። እንዲሁም በርበሬ፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲምና ሚጥሚጣ በስፋት ይለማ እንደነበርም ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የክልሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ኢኒሼቲቭ በሆነው 30-40-30 መርሀ-ግብር ሲጀመር በወረዳው 60 ሺ የሙዝ ችግኞች ተተክለዋል። አስር ቀበሌዎችን የያዘ አራት የፍራፍሬ መንደርም ተመስርቷል። በተለይ ዱኤሻገላ ቀበሌ የሙዝ ምርት በከፍተኛ መጠን በመስፋፋቱ ችግኙን ወደ ሌሎች ቀበሌዎች የማዳረስ ስራ ተሰርቷል።

አርሶአደሩ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ማምረት መጀመሩ የቤተሰቡን የምግብ ስርዓት የተመጠጠነ ከማድረግ አኳያ ጉልህ ሚና ማበርከቱን ከዚያ ባሻገር የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆን ከቀበሌው አስተዳደር ጀምሮ ቅንጅታዊ ስራ መሰራቱን በዚህም ምክንያት ነጋዴዎች ማሳ ድረስ በመምጣት ምርቱን የሚገዙበት ሁኔታ መኖሩን ያስረዳሉ።

ከዱኤሾ ቀበሌ ውጪ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ግን ሰፊ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት በመኖሩ ልማቱ እንደቀጠለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹በዚህም ቀበሌ ቢሆን ግድቡ ከተበላሸ በኋላ እንደ ሌሎቹ አይስፋፋ እንጂ በጉድጓድ ውሃ የማልማት ስራ የጀመሩ አርሶአደሮች አሉ›› ይላሉ።

እሳቸውም እንዳሉት፤ ግድቡ ብልሽት ከደረሰበት ወዲህ የቀበሌው ምርት ቀንሷል። ወንዙ ላይ ያለው ግድብ የተበላሸውም በ2015 ክረምት ላይ ሲሆን፣ ብልሽቱም ከክልል በመጡ ባለሙያዎች ጥናት ተደርጎበታል፤ ጠግኖ መልሶ ወደ ልማት ለማስገባት ወደ 40 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ የተጠየቀውን ፋይናንስ በወረዳም ሆነ በዞን ደረጃ የሚቻል አይደለም። ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል የቀረበ ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥትም በቅርቡ ጨረታ አውጥቶ ግድቡን ለመጠገን እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ብለዋል።

አቶ ታደሰ ሞኮሮ የሻሸጎ ወረዳ ምክትል አስተዳደሪና ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። እንደእርሳቸው ገለፃ፤ ወረዳው የአየር ንብረቱም ሆነ ስነ ምህዳሩ ለግብርና ስራዎች ምቹ ከሚባሉት የዞኑ አካባቢዎች አንዱ ነው። ይሁንና አርሶአደሩ በዝናብ ጥገኝነት ላይ የተመሰረተ የግብርና ስራ የሚከተል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአካባቢው ማህበረሰብ ኑሮ ከእጅ ወደአፍ የሚባል አይነት ነበር። የብላቴ ወንዝ የመስኖ ግድብ ከተሰራ ከአስር ዓመት በፊት ቢሆንም አርሶአደሩ ተጠቃሚ አልነበረም።

ይሁንና እንደሃገርም ሆነ እንደክልል የተለያዩ የልማት መርሃግብሮች ይፋ ከተደረጉ ወዲህ ግን የወረዳውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን ያስታውሳሉ። በተለይ ደግሞ የብላቴን ወንዝ በመጠቀም አርሶአደሩ የመስኖ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ያመለክታሉ።

የወረዳውን አርሶአደሮች ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ተግባራዊ ከሆኑት መርሃ ግብሮች መካከል የሌማት ቱሩፋት ዋነኛው ሲሆን፣ በተለይም በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በዶሮ እርባታና ንብ ማነብ ስራዎች የማስፋፋት ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል።

‹‹ከዚህ ባሻገርም የክልሉ 30-40-30 የአትክልት ፍራፍሬ ኢንሼቲቭ ስራ በይፋ የተጀመረው እዚሁ ሻሸጎ ወረደ ላይ ነው›› የሚሉት አቶ ታደሰ፤ መጀመሪያ ላይ አርሶአደሩ ቶሎ ለመቀበል ባለመቻሉ እንቅፋት ሆኖ እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይም በአካባቢው ሙዝ የማይታወቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሙዙ ባይበቅል ልንከሰር እንችላለን የሚል ስጋት አርሶአደሩን ወደ ልማቱ እንዳይገባ ሰቅሶ ይዞት እንደነበረ አይሸሽጉም።

‹‹አርሶአደሩ መጀመሪያ ላይ ሙዝ ላለማምረት ከጠበቅነው በላይ ሲያንገራግርና ሁሉንም ነገር በጥርጣሬ ሲመለከት ስለነበር፤ እኛው ራሳችን እየገባን እየሰራን እና የባለሙያ ክትትል ቀን በቀን ታክሎበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ማየት ችለናል››ይላሉ።

ሙዙ ከተተከለ በኋላ ግን የአርሶአደሩ አሉታዊ አመለካከት በሂደት እየተለወጠ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። ‹‹መጀመሪያ ላይ በራሳቸው ማሳ ላይ የተከልነውን ሙዝ ውሃ ለማጠጣት እንኳን ፍቃደኛ አልነበሩም፤ እኛው ራሳችን እየመጣን ነበር የምናጠጣው›› የሚሉት አቶ ታደሰ፤ ውጤቱን ካዩ በኋላ ማገዝና እንዲያውም የማስፋፋት ፍላጎት እያደረባቸው መምጣቱን ያስረዳሉ። በክላስተር ተደራጅተው ሙዝና ስንዴን በስፋት ማምረት መጀመራቸውን ይገልጻሉ።

እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በወረዳው በመደበኛም ሆነ በበጋ መስኖ ልማት 4 ሺ 50 ሄክታር የማልማት አቅም ያለ ሲሆን፤ ከዚያ ውስጥ 3ሺ897 ሄክታሩን ማልማት ተችሏል። በተጨማሪም በወረዳው በሙዝ ብቻ አራት ክላስተር አለ፤ ዱኤሻገላ አንዱ ክላስተር ሲሆን፤ በዚህም አርሶአደሩ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ ባለፈ የገቢ ምንጩን ማሳደግ ችሏል። ከዚህ ባሻገር በሌማት ትሩፋቱም ሆነ በ30-40-30 የልማት መርሃግብር ለአካባቢው ስራአጥ ወጣቶች የስራ አድል ተፈጥሯል። 50 የሚሆኑ ወጣቶች በግብርና ልማት ለመሰማራት ተደራጅተው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ዘንድሮ በመስኖ አውታሩ ላይ በደረሰው ጉዳት ምክንያት ምርት መቀነሱን እሳቸውም አረጋግጠዋል። በዚህም ምክንያት 210 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ ማልማት የተቻለው 76 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ይህንን ያህል ማልማት የተቻለውም አርሶአደሩ ባደረገው ርብርብ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የክልሉ መንግሥት በአፋጣኝ ወደ ሥራ ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀው፤ በቅርቡ በክልል ደረጃ በተደረገ ውይይት ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች መኖራቸውን ይናገራሉ። ‹‹ የመስኖ መሰረተ ልማቱን ዳግሞ ወደ ልማት ማስገባት ከተቻለ የተጀመረውን የልማት መርሀ ግብር አጠናክሮ የማስቀጠል ሥራ ይሰራል›› በማለት ተናግረዋል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ግንቦት 5 /2016 ዓ.ም

Recommended For You