ጽዱ ጎዳናዎችን ለማየት

ባዶ ሜዳ ላይ መጸዳዳት ዓለም አቀፍ ችግር ነው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በዓለማችን ላይ 467 ሚሊዮን ሕዝብ በሜዳ ላይ ይጸዳዳል። በኢትዮጵያ ደግሞ 30 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ መጸዳጃ ቤት የለውም። ይህም ማለት ደግሞ ባዶ ሜዳ ላይ ይጻዳዳል ማለት ነው።

ይህ ሀገራዊ ችግር ብሶ የሚገኘው መዲናችን፣ አዲስ አበባ ላይ የመሆኑ ጉዳይ ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ፤ የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት መቀመጫ፤ የአፍሪካ መዲናና ከኒዮርክና ጄኔቫ ቀጥላ ሶስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ በየሜዳው መጸዳዳት እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ ማህበራዊ ጉዳይ አይደለም።

ከተሞች ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መቀመጫነት ሊመረጡ የሚችሉት በቀዳሚነት ጽዱና ውብ ሲሆኑ ነው። ጽዱና ውብ ያልሆኑ ከተሞች ለማንኛውም አገልግሎት ተመራጭ አይሆኑም። ስለዚህም ከ50 ዓመታት በላይ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ሆና የቆየችው አዲስ አበባ በጽዳቷ ምክንያት መቀመጫነቷ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል።

በግልፅ እንደሚታወቀው፣ ባዶ ሜዳ ላይ መጸዳዳትና አካባቢን መበከል በርካታ የሆኑ ውስብስብ ችግሮችን ያስከትላል። ባዶ ሜዳ ላይ የሚጸዳዳ ማህበረሰብ ክብር የለውም። የሰው ልጅ እራሱን ከእይታ ከልሎ ከሚያከናውናቸው ተፈጥሯዊ ተግባራት መካከል አንዱና ዋነኛው መጸዳዳት ነው።

ከዚህ ውጪ ሲሆን ክብርን ያጎድፋል፤ ከሰው ልጅ ተርታ አስወጥቶ ከእንስሳት ተርታ ያሰልፋል። ያውም ደግሞ የድመትን ያህል እንኳን ክብር ያሳጣል። ከዚህም ባሻገር እንደ ኢትዮጵያዊነትም ክብርን ዝቅ የሚያደርግና የጀግንነት ተጋድሎ ላይ ጥላ የሚጠላ ነው።

ኢትዮጵያ የጀግኖች መፍለቂያ ናት። በየዘመናቱ የሀገሬን ሉአላዊነትና ዳር ድንበር አላስደፍርም ያሉ ጀግኖች ልጆቿ እምቢ ለሀገሬ በማለት አጥንታቸውን ከስክሰው፤ ደማቸውን አፍሰውና ህይወታቸውን መስዋዕት አድርገው የሀገራቸውን ሉአላዊነት አስጠብቀዋል፤ ለተተኪው ትውልድም አስረክበዋል።

ኢትዮጵያ ታሪካዊት ሀገር፤ ሕዝቧም የዚህ ታላቅ ጀብዱ ባለቤት ነው። ይህ ጀግና ሕዝብ ደግሞ ስሙ ሁልጊዜ ሲነሳ የሚሰማው ከመልካም ነገሮች ጋር ነው። ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር እንጂ ኢትዮጵያ ‹‹ሕዝቧ ሜዳ ላይ የሚጸዳዳባት ሀገር›› ተብላ መነሳት የለባትም፤ ክብሯንም የሚመጥን አይደለም።

ከዚሁ ሁሉ በሻገርም ኢትዮጵያዊነት ኩሩነት ነው። ኢትዮጵያ ለጊዜው ድሃ ብትሆንም ክብሯን አሳልፋ የምትሰጥ ሀገር ግን አይደለችም። የኢትዮጵያዊነት መገለጫም ጀግነነትና ክብር ነው። አንድ ኢትዮጵያዊ ድሃ ቢሆንም በክብሩ ግን ድርድር አያውቅም። ለአንድ ኢትዮጵያዊ ቆሻሻ መባል ሞት ነው።

ይህ ደግሞ ከባህል፣ ከእምነትና እሴት ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያዊያን ነውራቸውን መደበቅ፤ አፀያፊ ተግባራትን ማውገዝና አርአያነት ያለውን ተግባር መፈጸም መለያቸው ነው። በየሜዳው መጸዳዳት ከዚህ ኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር የሚጣረስና እንደ አረም የወረረ አፀያፊ ተግባር ነው።

የጽዳት ጉዳይ ከዓለማዊ አልፎ ሰማያዊ ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ ከ98 በመቶ በላይ የሆነው ሕዝብ አማኝ ነው። ይህ አማኝ ሕዝብ የሚከተላቸው ሃይማኖቶች ለንጽህና ከፍተኛ ክብርን የሚሰጡ ናቸው። በክርስትናም ሆነ በእሰልምና እምነቶች ንጽህና ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል።

በየሜዳው የሚጸዳዳ ማህበረሰብ ክብር ከማጣቱም ባሻገር ኋላ ቀር ተደርጎ ይቆጠራል። ጽዳት የስልጣኔ አንዱ መገለጫ እንደመሆኑ መጠን ክብር ሳይጠብቁ በየሜዳው መጸዳዳት ከስልጣኔ መራቅን እና ኋላ ቀር መሆኑን ያሳያል። ዓለም በስልጣኔ መጥቆ፤ ከመሬት አልፎ ጠረፍ ላይ ምርምር በሚያደርግበት በዚህ ዘመን የሰው ልጅ ሜዳ ላይ ሲጸዳዳ መገኘቱ እንደጋርዮሽ ዘመን ሰው የሚያስቆጥረው ነው።

ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ስልጣኔን የምናውቅና በርካታ ቁም ነገሮችን ለዓለም ሕዝብ ያስተዋወቅን ከመሆኑ አንጻር፣ 30 ሚሊዮን ሕዝብ ሜዳ ላይ ወጥቶ መጸዳዳቱ ከስልጣኔ እየሸሸን መምጣታችንን የሚያሳይ ነው። ጽዳት ከክብርም በላይ የስነልቦናም ጦስ ይዞ ይመጣል።

ጽዱ ያልሆነ ማህበረሰብ የስነልቦና የበላይነት አይኖረውም። ደረቱን ነፋ አድርጎ መናገርና ከሰው ፊትም መቆም አይችልም። በየቦታው ተጸዳድቶ፤ ቆሻሻ ለቦሶና ቆሻሻ ተመግቦ መኩራራት አይቻልም። ቆሻሻ በሆኑ ቁጥር ሁልጊዜ የበታችነት ስሜት አለ። ሰፊው ሕዝብ ሜዳ ላይ የሚጸዳዳባት ሀገር እንደ ሀገርም ለዛች ሀገር ውርደትን ያስከትላል።

በየትኛውም መድረክ ላይ ተገኝቶ የሀገርን ገጽታ ለመገንባት ይቸገራል። በስነልቦና የተሸነፈ ሀገር ደግሞ በሁሉም ዘርፍ ተሸናፊ መሆኑ አይቀርም። የጽዳትና የንጽህና መጓደል የሀገርን ገጽታ የሚያበላሽና ቱሪዝምንም በእጅጉ የሚጎዳ ነው። የቆሸሸን ሀገር ለመጎብኘት የሚመኝ ማንም ቱሪስት የለም። ቱሪስቶች ለመጎብኘት የመጀመሪያ ምርጫ የሚያደርጉት ውብና ንጹህ አካባቢን ነው።

ኢትዮጵያ ለቱሪዝም የሚሆኑ በርካታ ጸጋዎች ያሏት ሀገር ነች። ኢትዮጵያ የበርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት ነች። የተፈጥሮ ሀብቶቿ ከኤርታኢሌ እስከ ዳሎል፤ ከራስ ዳሽን እስከ ታችኛው ኦሞ ሸለቆ ድረስ የተዘረጉ ናቸው። ከእነዚህም መካከል አስደናቂ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ የአየር ንብረት፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ እንዲሁም የሰው ዘር መገኛ ስፍራዎች ተካተውባታል።

ሃይማኖታዊ በዓላትም የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ሆነው እና በዩኒስኮ ደረጃ ተመዝግበው ዛሬ የዓለም ቅርስ እስከ መሆን ደርሰዋል። በአፍሪካም ቅርሶችን በማስመዝገብ ቀዳሚ ሀገር ነች። እነዚህ ቅርሶች ለጎብኚዎች መስህብ ሊሆኑ የሚችሉት የሀገሪቱ ጽዳት ሲጠበቅ ነው። ኢትዮጵያ ጽዱና ውብ እስካልሆነች ድረስ እነዚህ አማላይ የቱሪዝም መስህቦች የጋን ውስጥ መብራት ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የላቸውም።

በተለይም በአሁኑ ወቅት መንግሥት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ቱሪዝምን እንደዋነኛ የገቢ ምንጭ በወሰደበት ወቅት በጽዳት መጓደል ምክንያት የሚጠበቀው ገቢ ሲታጣ እንደ ሀገር ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ይሆናል።

በንጽህና መጓደል ተላላፊ በሽታዎች ሲከሰቱ ቱሪስቶች ሁልጊዜ ጉዟቸውን ይሰርዛሉ። ይህ ሲሆን ደግሞ ሀገር በርካታ ዶላሮችን ታጣለች። በዚህ ምክንያት የገንዘብ እጥረት ይከሰትና ሊሰሩ የታሰቡ መሰረተ ልማቶች ይታጠፋሉ። የትምህርትና የጤና ተቋማት በበጀት እጥረት የተነሳ ስራቸው ይስተጓጎላል፤ የመንገድ መሰረት ልማት ይቋረጣል። የታሰበው እድገትና ብልጽግና ህልም ሆኖ ይቀራል። ከዚሁም ጋር ተያይዞ ኢንቨስትመንት ይዳከማል።

የውጭ ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉት ጽዱና ጤናማ በሆነ ማህበረሰብ ውስጥ ነው። ኢንቨስተር (ባለ ሀብት) ጤናው የተጠበቀና አምራች የሰው ኃይል ይፈልጋል። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ አካባቢውን በአግባቡ የሚያጸዳ እና ለጤናው ትኩረት የሚሰጥ ዜጋ ሲበራከት ነው።

የአካባቢ ጽዳት መጓደል ከሁሉ በፊት የሚጎዳው ጤናን ነው። በኢትዮጵያ 48 በመቶ የሚሆኑት በሽታዎች የሚከሰቱት ከአካባቢ ጤና መጓደል ጋር በተያያዘ ነው። ከጤና ጥበቃ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በየሜዳው የሚደረገው መጸዳዳት ከፍተኛ የጤና ቀውስ እያስከተለ ይገኛል። በርካቶችንም ለህልፈተ ሕይወት እየዳረገ ነው።

ተላላፊ በሽታ ከሰው ወደ እንስሳት ወደ ሌላ ሰው ወይም እንስሳት ይተላለፋል። ሁሉም ተላላፊ በሽታዎች በዓይን የማይታዩ እንደ ባክቴሪያና ቫይረስ ያሉ ተዋህሲያን እና ጥገኛ የአንጀት ትላትሎች አማካይነት የሚከሰቱ ናቸው። አብዛኛዎቹ ለጤና ጐጂ የሆኑ ተዛማች ተህዋሲያን በበሽታ በተጠቁ ወይንም ተሸካሚ በሆኑ ሰዎች አይነ-ምድር ውስጥ ይገኛሉ። ከአይነ-ምድር ጋር የሚወጡት እነዚህ ጀርሞች በተለያዩ መንገዶች ወደ ሌላ ሰው በመዛመት በሽታን ያስከትላሉ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከዩኒሴፍና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተባባሪ አካላት ጋር ያጠናው ጥናት እንደሚያሳየው ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመፀዳጃ ቤቶች፣ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና አጠባበቅ እና ያልተሟላ የቆሻሻ አወጋገድ ዘዴ ዋና ዋና የጤና ችግሮች መንስኤ ናቸው።

ምንም እንኳን የመፀዳጃ ቤቶች ሽፋን የጨመረ ቢሆንም የጥራትና የአጠቃቀም ችግሮች መስተዋላቸው አሌ የሚባል አይደለም። በገጠር 19% የሚሆን ሕዝብ ብቻ የተሻለ መፀዳጃ ቤት የሚጠቀም ሲሆን፣ 6% የጋራ፤ እንዲሁም 22% ደግሞ መስፈርቱን ያላሟሉ መፀዳጃ ቤቶችን ይጠቀማል። ወደ 53% የሚሆኑ ዜጎች በሜዳ ላይ ይፀዳዳሉ። በተለይም፣ በጣም ተዛማች የሆኑ ተላላፊ በሽታዎች ማለትም ተቅማጥና ኮሌራ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሕዝብ በኢትዮጵያ ለሞት የሚዳርጉበት ምስጢርም ይኸው ነው። የተቅማጥ በሽታዎች በየዓመቱ የ2.2 ሚሊዮን ሰው ህይወትን የሚቀጥፉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 85% ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው።

በአጠቃላይ ሜዳ ላይ መጸዳዳት አደጋው ዘርፈ ብዙ ነው። ይህንኑ በመረዳት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት ‹‹ጽዱ ጎዳና፤ ኑሮ በጤና›› ንቅናቄ ይፋ ሆኗል። ይህ ንቅናቄ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን የሚያሳትፍና መጸዳጃ ቤቶችንም የማስፋፋት አላማ ያለው መሆኑ ተገልጿል። ይህ ንቅናቄ አብዛኛው ማህበረሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክትና እንደ ሀገርም በየቦታው መጸዳዳት እያስከተለ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችል ነው።

ይህ ንቅናቄ እንደ ሀገር የተጀመረውን የ“ጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ዳር ለማድረስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የብዙዎች እምነት ነው። የመፀዳጃ ቤት ችግሩን ለመፍታት እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ የሚታይ ነው። ዜጎችን አስተባብሮ ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶች እንዲገነቡም ዕድል የሚሰጥ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎንም ሜዳ ላይ መጸዳዳት ጸያፍ፤ የሀገርና የሕዝብ ክብርን ዝቅ የሚያደርግ መሆኑን የሚያመላክቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችንም የሚያካትት ነው።

ባለሙያዎች አብዛኛው በሜዳ የመጸዳዳት ልምድ ያለው ማህበረሰብ ሲያጋጥም ጠንከር ያለ የትግበራ ስልት ሊኖር እንደሚገባ ይመክራሉ። በኢትዮጵያ በመተግበር ላይ ያለው አንዱ የትግበራ አካሄድ ማህበረሰብ መር ጠቅላላ ሳኒቴሽን (CLTSH) ነው። ይህ የትግበራ አካሄድ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ሀፍረተ ቃላትን በመጠቀም በሜዳ የመጸዳዳትን ልምድ ጨርሶ የማጥፋት እና የባህሪይ ለውጥ ማምጣጥ የሚያስችል ነው።

አካሄዱ መጸዳጃ ቤት ከመገንባት ጎን ለጎን የባህርይ ለውጥ እንዲያመጣ ማድረግ የሚያስችል፤ እራሱን፣ ማህበረሰቡን በማሳተፍ እና ሂደቱን እንዲመራ በማድረግ በሜዳ ከመጸዳዳት ሙሉ በሙሉ የፀዳ ማህበረሰብን ለመፍጠር የሚያግዝ ነው። በዋናነት ትኩረት የሚያደርገው ማህበረሰቡ የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት እንዲጠቀም፣ ወሳኝ በሆኑ ጊዜ እጅን በሳሙና ወይም በአመድ መታጠብ፤ አስተማማኝ የቤት ውስጥ ውሃ አያያዝና አጠቃቀም ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል (በሁሉም ደረጃ ላይ የሚገኙ ማህበረሰብ፣ የእድሜ ክልል፣ ፆታ ወዘተ) የሚጨምር ነው።

ስልቱ ማህበረሰቡ ባህልና ወጉን መለስ ብሎ እንዲመለከት፤ ሰብአዊ ክብሩን በውል እንዲገነዘብና ውስጡን እንዲጠይቅ የሚያደርግ ነው። ያለ ምንም መደባበቅ ሀፍረተ ቃላትን በመጠቀም ‹‹ባዶ ሜዳ ላይ መጸዳዳት ነውር›› መሆኑን ደጋግሞ በመንገር በሜዳ ላይ መጸዳዳትን መቶ በመቶ ማስቀረት ይገባል። አሁን እንደ ሀገር ችግሩን ለመፍታት የተጀመሩ ንቅናቄዎች ጎን ለጎንም ማህበረሰቡ ወግና ባህሉን፤ እንዲሁም፣ ክብሩን እንዲጠብቅ የሚያስችሉ የግንዛቤ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ግንቦት 5 /2016 ዓ.ም

Recommended For You