ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያስጀመሩት “የጽዱ ጎዳና-ኑሮ በጤና” ሀገራዊ የንቅናቄ ማድረክን እውን ለማድረግ በተያዘ እቅድ መሠረት ብዙ ተቋማትና ግለሰቦች በገንዘብና በሌሎች ነገሮች ለማገዝ ቁርጠኝነታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ፕሮጀክቱ ካለው ግዝፈትና ለዜጎች ኑሮ ተስማሚና ተመራጭ አካባቢን ከመፍጠር አኳያ የብዙዎችን ርብርብ እና እገዛን የሚፈልግ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተባባ ሪነት “በገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ” በሚሉት የንቅናቄና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ኢትዮጵያን በብዙ ደረጃዎች ከፍ ማድረግ የሚችሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ተሠርቶ በመጠናቅቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ሀገርን በሁሉም ነገር ጽዱና ለዜጎቿ የምትመች ለማድረግ እነዚህ ብቻ በቂ ባለመሆናቸው እቅዶችን በማውጣትና ተጨማሪ ውበትን ማላበስ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን ማብዛት ሕዝብና መንግሥት በጋራ ሊሠሩት የሚገባ እንደሆነ ብዙዎችን የሚያስማማና የሚያግባባ ሃሳብ ነው፡፡
አንድ ሀገር እና ከተማ ከቆሻሻ የጸዳና ውብ ከሆነ በአካባቢው ለሚኖረው ኅብረተሰብም ሆነ ከሌላ ቦታ ለጉብኝትና ለመዝናናት የሚመጡትን ሰዎች ቁጥርን ከመጨመሩም በላይ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በማህበራዊ ጉዳዮች ተጠቃሚና የበላይነቱን እንዲቆናጠጥ ያስችለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውብ የሆኑ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለቤት ብትሆንም ጽዱና አመቺ በማድረግ ከቱሪዝሙ የተጠቀመችው ነገር ብዙ የሚባል አይደለም፡፡
የቆሻሻ አወጋገድ ባህላችን ባለመዳበሩ በተለይ በከተሞች አካባቢ መጥፎ የቆሻሻ አወጋገድ እና ዜጎችን ለጤና እክል የሚያጋልጥ ሁኔታ ፈጥሮ ለብዙ ጉዳቶች እያጋለጠን አብሮን ቆይቷል። ቆሻሻ ሀብት ነው ቢባልም እሱ ቀርቶ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን አስከትሎብን በሌሎች ሀገራት ከተሞች ጽዳት እና ውበት ብቻ እየቀናን ኖረናል፡፡ አሁን ግን ያ ጊዜ አብቅቶ በሀገራችን የሚገኙት ከተሞች በጽዳታቸው ለሌሎች ተምሳሌትና ለኑሮ ተመራጭ ሚሆኑበት ጊዜ የመጣ ይመስላል፡፡
በሀገራችን በጽዳታቸውና በንድፋቸው ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችሉ እንደ ሃዋሳና ባህርዳር ያሉ ከተሞች ቢኖሩንም እነሱም ላይም የሰራነው ነገር በቂ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ጽዱ ውብና ለነዋሪ ምቹ የሆኑ ከተሞችን የምንፈጥርበት ትክክለኛ ጊዜ አሁን በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ ይህን በጎ የሆነና ሀገርን በብዙ መልኩ ሊቀይር የሚችል ተግባር በሚችለው አቅም ሁሉ መደገፍ አለበት፡፡
ሁሉም ዜጋ በትብብርና በአንድነት ቆሞ የሚሠራ ከሆነ ነገሩን በአጭር ጊዜ እውን በማድረግ የሀገራችንን ከተሞች ከአውሮፓ፣ አሜሪካና በሌሎች ዓለማት ከሚገኙ ውብና ጽዱ ከተሞች ተርታ ማሰለፍ እንችላለን፡፡ ይሄንን ትልቅ ሃሳብ እውን ለማድረግ የሀገሬው ዜጋ በብዙ መንገዶች ድጋፉን ማድረግ ይችላል፡፡ ከነዚህም መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያክል በገንዘብ፣ በእውቀት፣ የባህሪ ለውጥ በማምጣትና የባለቤትነት ስሜትን በማዳበር ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል፡፡
ፕሮጀክቱ በሚፈለገው መልኩ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ መዋል የሚችል ከሆነ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ በመሆኑ በትልቅ መነቃቃትና ሞራል ከግብ ማድረስ ይገባል፡፡ ሃሳቡ ይፋ ከሆነበትና የንቅናቄ መድረኩ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት፣ የግል ተቋማት እና ግለሰቦች የተለያየ የገንዘብ መጠንን እያበረከተ ንቅናቄውን መቀላቀላቸውን እያሳወቁ ነው፡፡
ጉዳዩ በዋናነት በመንግሥት ሊሠራ የማይገባውና በተቋማት ደረጃ ሊሰራ የሚገባው ነበር፡፡ ቢሆንም መንግሥት ባለው ቀና እይታ በማስጀመሩና የማስተባበሩን ሚና እየተወጣ በመሆኑ በቶሎ እንዲሳካ ሁሉም ተቋማትና ባለሀብቶች ትብብራቸውን አጠናክረው መቀጠል ይገባቸዋል፡፡ በንቅናቄው በሚሰበሰበው ገንዘብ በሁሉም ከተሞች ጽዱና ምቹ የሆኑ ጎዳናዎችን እና የመጸዳጃ ቤቶችን ለመፍጠር ይቻላል፡፡
ጽዱና ምቹ የሆኑ አካባቢና መንገዶችን መፍጠር ከተቻለ ተቋማት ለአገልግሎት አሰጣጥ እንዲመቹ ማድረግና በተገልጋዮች ተመስጋኝና ተመራጭነታቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል። ለዚህም ከገንዘብም ባሻገር ባላቸው ሀብትና እውቀት በሙሉ ፕሮጀክቱን በማገዝ እውን እንዲሆን ማድረግ የነሱም ትልቁ ማኅበራዊ ኃላፊነትም ጭምር ነው፡፡ ድርብ ኃላፊነትን እንደመያዛቸው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በመወጣት አርአያነታቸውን ማስመስከር አስፈላጊው ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንድ የመንግሥት አገልግሎት ተቋማትም ገንዘብ ከመለገስም አልፎ የራሳቸውን የጽዱ ተቋም እና ጽዱ ሀገርን የመፍጠር ንቅናቄዎችን በማስጀመር ላይ ናቸው።
ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም በየፊናቸው ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ንቅናቄው ሀገራዊ እንዲሆን የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ይገባቸዋል፡፡ ባለሀብቱም በገንዘብ፣ በእውቀትና በሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ሁሉ ተባብሮ በመስራት በአጭር ጊዜ ጽዱ የሆነ አካባቢን የመፍጠሩ እንቅስቃሴ ማሳለጥ ይጠበቅበታል፡፡
ሌላው ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ የሚያስፈልገው ትልቅ መሳርያ እውቀት ነው። ጽዱ የሆኑ የመጻዳጃ ቤቶችን እና የማረፍያ ሥፍራዎችን ለመሥራት ሙያዊ እውቀት አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም በሙያ የታገዘና ዘላቂ ሥፍራዎችን ለመፍጠር ሙያዊ አበርክቶን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ ሀገራዊ እውቀት እንዲዳብር እና ሀገር በቀል ባለሙያዎችን ለማፍራት የማይተካ ሚናን ይጫወታል፡፡
የባህርይ ለውጥና የአኗኗር ዘይቤያችንን በመቀየር የተጀመረው ሃሳብ እውን እንዲሆንና ጽዱና ውብ ከተማን የመፍጠሩን ሥራ ማገዝ እንችላለን፡፡ ይህንን ስል ለጽዳት ያለንን አመለካከትና የቆሻሻ አወጋገድ ባህላችንን በማሻሻል እና ለራሳችን ተገዢ በመሆን ስልጡን ሕዝቦች የሚለውን አባባል እና ባህሪ መላበስ ስንችል ነው፡፡ በየመንገዱና በየአደባባዩ ቆሻሻ ከመጣልና ከመጸዳዳት ተቆጥበን የሚጸዳዱትንና ቆሻሻን የሚጥሉ ካሉ በመተቸትና ትክክለኛውን ባህሪ እንዲለበሱ በማድረግ ጽዱ ከተማ፣ ጽዱ ሀገርና ዓለምን ለትውልድ ማስረከብ እንችላለን፡፡
መጥፎ የቆሻሻ አወጋገድን እንደ ጎጂ ባህል በመቁጠር ጽዱ እና ውብ ከተማን መፍጠር ተጨማሪ የድጋፉ አካል ሊሆን ይገባል፡፡ የአንድ ከተማ ጽዳት የሚለካው በመሠረተ ልማት ደረጃ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ተመራጭነት፣ ለኑሮ አመቺነት እና ለሥራ በሚኖረው ተስማሚነት ይሆናል፡፡
የሚገነቡት መንገዶች፣ አደባባዮች፣ የመንገድ አካፋዮች፣ የመንገድ መብራቶች እና የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች ለከተሞች ጽዳትና ውበት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፡፡ እነዚህን ቦታዎች በእኔነት እና በባለቤትነት ስሜት ማነጽ እና መጠበቅ የሁላችንም ድርሻ ነው፡፡ መንገዶች በመጥፎ የቆሻሻ አወጋገድ ምክንያት ሲታወኩ ብዙ ጉዳቶች እንደሚያስከትል በመገንዘብ ሁሉም ዜጋ ለምን ብሎ መሞገት ይኖርበታል፡፡
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2016 ዓ.ም