በግብርና ምርቶቿ በዓለም ገበያ የምትታወቀው ኢትዮጵያ አሁን አሁን ደግሞ በተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ይህንኑ አጠናክራ በመቀጠል ተወዳዳሪ ለመሆን እየታተረች ትገኛለች። ለዚህም መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ትልቅ ድርሻ አለው። ይህን ተከትሎም በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፉን እየተቀላቀሉ ፣ ነባሮቹም እየተስፋፉ ናቸው።
በተለይም ሀገራዊ ሁኔታውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ማብቃትና ማስፋፋት ላይ ሰፊ ዕቅድ ተይዞ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻ ከፍ እንዲልና የኤክስፖርት ምርትም እንዲሁ መስፋት እንዲችል አድርጓል።
አምራች ኢንዱስትሪዎች በምርቶቻቸው ማህበረሰቡ የሀገሩን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝቶ መጠቀም እንዲችልና በሀገሩ ምርት እንዲኮራ ለማድረግ እየሠሩ ይገኛሉ። ከዚህም በላይ ሀገሪቷ ወደ ውጭ ከምትልከው ምርት በእጥፍ እያደገ የመጣውንና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቀውን የገቢ ምርት በመቀነስ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ እየተቻለ ነው። ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ›› በርካታ የሀገር ውስጥ አምራቾች ምርቶቻቸውን ራሳቸውን ጠቅመው ሕዝብና ሀገርም እንዲሁ በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ በማድረግ የድርሻቸውን እየተወጡ ናቸው።
አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ ካሉ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች መካከል የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ አንዱ ሲሆን፤ በተለይም የጋርመንት ዘርፍ /አልባሳት ማምረት / ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። በጋርመንት የልብስ ስፌት ሙያ ተሰማርተው በሀገር ውስጥ የተመረቱ አልባሳትን ዜጎች መልበስ እንዲችሉ ካደረጉ በርካታ የዘርፉ አምራቾች መካከል የዕለቱ እንግዳችን የኮዚ ዌር የልብስ ስፌት ድርጅት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዮዲት መስፍን አንዷ ናት።
ወይዘሮ ዮዲት፤ በጋርመንት የልብስ ስፌት ተሰማርታ አልባሳትን እያመረተች ለሀገር ውስጥ ገበያ ታቀርባለች። ወደ ልብስ ስፌት ሙያ ከገባች ከአምስት ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። ተወልዳ ያደገችው ደሴ ቢሆንም ዕድሜዋ ለትምህርት ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ ኑሮዋን ያደረገችው አዲስ አበባ ከተማ ነው።
አዲስ አበባ ከቤተሰቦቿ ጋር የመጣችው ወይዘሮ ዮዲት፤ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችውም በአዲስ አበባ አፍሪካ አንድነት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በኋላም ከአድማስ ኮሌጅ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት ዲፕሎማ አግኝታለች።
ከትምህርት በኋላ ወደ ሥራ ወደ ማማተር የገባችው ወይዘሮ ዮዲት፤ ተቀጥሮ የመሥራት አጋጣሚ አልገጠማትም። እሷም ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ የራስን ቢዝነስ አጥንቶ መሥራት አዋጭ እንደሆነ ታምን ነበርና በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ተሰማርታ ሰርታለች።
የራሷን ቢዝነስ ለማቋቋም ከፍተኛ ፍላጎትና ተነሳሽነት የነበራት ወይዘሮ ዮዲት፤ በውስጧ ያለው ጥረትና ተነሳሽነት የንግድ ሥራውን በመኖሪያ ቤቷ ለመጀመር አስገድዷታል። በመኖሪያ ቤቷ ውስጥ የባልትና ውጤቶችን በማምረት የንግድ ሥራዋን ‹‹ሀ›› ብላ ጀምረች። በርካታ የሥራ ዕድል በመፍጠር የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን ጨምራ በርበሬ፣ ሽሮ፣ ሚጥሚጣ፣ የአጥሚት እህል፣ የገንፎ እህል እንዲሁም ጠጅ ሳይቀር አዘጋጅታ ለገበያ ታቀርብ እንደነበር አጫውታናለች።
‹‹የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ›› እንዲሉ ታዲያ ምርቶቿ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለውና ጥሩ ገበያ የነበራት በመሆኑ በመኖሪያ ቤቷ እያመረተች በተለያዩ የመሸጫ ሱቆች ለበርካቶች ታደርስም ነበር። ይሁንና መኖሪያ ቤቷ ለልማት በመፍረሱ ምክንያት የባልትና ሥራዋን መቀጠል አልቻለችም። ከውስጥ በመነጨ ፍላጎት ወዳውና ፈልጋው ስትሰራ የነበረው የባልትና ሥራዋ ተቋረጠባት። ወይዘሮ ዮዲት ግን ከአካባቢ ቀየርኩ ብላ እጇን አጣጥፋ አልተቀመጠችም፤ ይልቁንም ሌሎች የሥራ ሃሳቦችን ማውጠንጠን ጀመረች እንጂ።
ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ የራስ ሥራን በራስ አቅም መሥራት አዋጭና ተመራጭ ነው የሚል ጽኑ ዕምነት ያላት ወይዘሮ ዮዲት፤ ለምዳና አለማምዳ ተመችቷት ስትሰራ ከነበረው ከባልትና ሥራዋ ስትስተጓጎል አማራጭ የሥራ ሃሳቧ ከፋሽን ዲዛይን ላይ አረፈ። ጊዜ ሳታጠፋ የፋሽን ዲዛይን ትምህርቷን ለአንድ ዓመት በመከታተል ወደ ልብስ ስፌት ሥራ አቅናች።
የልብስ ስፌት ሙያን በኔክስት የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤት የተከታተለችው ወይዘሮ ዮዲት፤ የልብስ ስፌት ሥራን ምርጫዋ በማድረግ የተማረችውን በሥራ አውላለች። የመጀመሪያው የልብስ ስፌት ሥራዋም የሀገር ባህል አልባሳት ሲሆን፤ አበሻ ልብስ በስፋት ከሚመረትበት ሽሮሜዳ ገብታ ለአምስት ዓመታት የሀገር ባህል አልባሳት ስትሰራ ቆይታለች። የሀገር ባህል አልባሳቱን በብዛት ስትሰራ የነበረው በትዕዛዝ በመቀበል ደንበኞች በሚፈልጉት ዲዛይን እንደነበር በማስታወስ በዚህም በርካታ ደንበኞችን አፍርታለች።
የሀገር ባህል አልባሳቱ ወቅት ጠብቆ የሚሰራ እንደመሆኑ ሥራውን ለማስፋት አመቺ አልሆነላትም። እናም የልብስ ስፌት ሥራዋን ለማሳደግ ስታስብ ከሀገር ባህል አልባሳት ሥራ ወጣ ማለት እንዳለባት በማመን ሙያዋን ወደ ጋርመንት ልብስ ስፌት ቀየረች። የሀገር ባህል አልባሳቱ ወቅታዊ በመሆኑ በየጊዜው የሚመረት አይደለም። የምትለው ወይዘሮ ዮዲት፤ የሀገር ባህል አልባሳት በብዛት የሚፈለገው በበዓል ወቅት እንደሆነና በየጊዜው በስፋት ማምረት እንደማይቻል ነው የገለጸችው።
እሷ እንዳለችው፤ የፋሽን ዲዛይን ሙያን አስፍቶ ለመሥራት የስፌት ሥራ አንዱ እንደመሆኑ ወደ ጋርመንት ሥራ ገብታለች። ጋርመንት ላይ የሚመረቱ አልባሳት በማንኛውም ጊዜ የሚለበሱና በጣም ተፈላጊ እንደመሆናቸው ያለገደብ በማንኛውም ጊዜ መመረት የሚችሉ ናቸው። በተለይም የልጆች ልብስ እንደ ቱታ፣ ቲሸርት፣ ቁምጣና ሌሎችም በብዛት የሚፈለጉ አልባሳት ናቸው። እሷን ጨምሮ ልጆች ያላቸው በርካታ ሰዎች ቀለል ያለና በየጊዜው መለበስ የሚችሉ አልባሳትን ይፈልጋሉ። ይህ ከፍተኛ ፍላጎት በመረዳት የሀገር ባህል አልባሳት ማምረት ሥራዋን በጋርመንት ልብስ ሥራ ቀይራለች።
‹‹ልጆች ከትምህርት ቤት መልስ በቤታቸውና በአካባቢያቸው በሚኖራቸው ቆይታ የሚለብሱት ቱታ፣ ቲሸርትና ቁምጣ እንደመሆኑ በየጊዜው ይጨርሳሉ። በመሆኑም ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት አለ። እኔም ይህን ፍላጎት በማጥናትና በመረዳት ነው ወደ ሥራው የገባሁት›› በማለት ያስረዳችው ወይዘሮ ዮዲት፤ ከልጆች በተጨማሪም አዋቂዎች ጭምር በቤት ውስጥና በመኖሪያ አካባቢያቸው በሚቆዩበት ጊዜ ቀለል ያለ እንደ ቱታና ቲሸርት ዓይነት ልብሶችን ይፈልጋሉ ትላለች። እነዚህን አልባሳት ታዲያ በሀገር ውስጥ በጥራት ማምረት ቢቻል ሰፊ ፍላጎት በመኖሩ አምራቹ፣ ተጠቃሚውና ሀገርም ጭምር ተጠቃሚ ይሆናል ትላለች።
እኔን ጨምሮ ቀለል ያሉና በተመጣጣኝ ዋጋ መገዛት የሚችሉ አልበሳትን ለሚፈልገው ሕዝብ ጋርመንት ልብሶች ተመራጭ እንደሆኑ ያነሳችው ወይዘሮ ዮዲት፤ ስለዚህ አምራቾች በጥራትና በስፋት ማምረትና ከውጭ የሚመጣውን በሀገር ውስጥ ለመተካት ብዙ መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሳለች። ከዚህም ባለፈ አልባሳትን በሀገር ውስጥ ማምረት ልብሶቹን ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ እንደልብ ለመሸመት ዕድል የሚሰጥና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል በመሆኑ አበረታች ነው ትላለች።
ሥራውን ወድጄ ነው የምሰራው የምትለው ወይዘሮ ዮዲት፤ የምታመርታቸው አልባሳት በብዛት የልጆች እንደሆኑና ገበያ ውስጥም በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኙ መሆናቸውን ታብራራለች። ወላጆች አልባሳቱን ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ እንደልባቸው ገዝተው መልበስና ማልበስ ያስቻላቸው ሲሆን፤ ኮዚ ዌር ጋርመንት በዋናነት እያመረተ ያለው የአዋቂና የልጆች ቱታ፣ የተለያዩ የወንድና የሴት ቲሸርቶች፣ የልጆች ቁምጣ ከነቲሸርቱ እና ለመኝታ የሚሆኑ የተለያዩ አልባሳትን ጭምር እንደሆነ አስረድታለች።
አያት ክብር ደመና አካባቢ በሚገኘው የማምረቻ ቦታዋ እነዚህን አልባሳት በማምረት ለሸማቹ እያቀረበች የምትገኘው ወይዘሮ ዮዲት፤ ጥሬ እቃውን ጭምር በሀገር ውስጥ መጠቀሟ ሥራዋን ቀልጣፋና ምቹ አድርጎላታል። ይሁንና ምርቶቹ የበለጠ ተመራጭ መሆን እንዲችሉ ጥሬ ዕቃውን ማለትም ብትን ጨርቁን የሚያመርቱ አካላት ጥራት ያለው ጨርቅ ቢያመርቱ የጋርመንት ምርቶች የበለጠ ተፈላጊና ተመራጭ ይሆናሉ ስትል ትገልጻለች። በተወሰነ ደረጃ የብትን ጨርቆቹ ጥራት ዝቅተኛ እንደሆነና ይህም የመጨረሻ በሆነው ውጤት ላይ ተጽዕኖ እንደሚያደርግ አመልክታለች።
ለምርቶቻችን የጨርቁ ጥራት ትልቅ ድርሻ አለው ስትል ወይዘሮ ዮዲት አስገንዝባ፤ ብትን ጨርቆቹ አሁን ካላቸው የጥራት ደረጃ የበለጠ መሻሻል ከቻሉ ከውጭ ከሚገቡ አልባሳት የበለጠ በሀገር ውስጥ አሳምረን ማምረት እንችላለን ትላለች። እሷ እንዳለችው ፤ፖሊስተርና ኮተን ተቀላቅሎ የሚመረት እንደመሆኑ ኮተኑ በዛ ቢል የተሻለና ጥራት ያለው ጨርቅ ማምረት ይቻላል። ነገር ግን ኮተኑ አነስተኛ ሆኖ ፖሊስተሩ ከበለጠ ጥራቱ ዝቅ ይልና ለሰውነት የሚኖረው ምቾትና ልሰላሴ ይቀንሳል።
እሷ እንዳብራራችው፤ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች የተሻለ ጥራት ያላቸውን የተለያዩ ዓይነት ጨርቆችን ማምረት ቢችሉ በሀገር ውስጥ የሚገኙ ጋርመንቶች ብዙ ሥራ መሥራት ይችላሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን እንደ ሌሎች ሀገራት ሁሉ የራሳቸውን ምርት በራሳቸው አምርተው መጠቀም እንዲሁም ኤክስፖርት ማድረግ ይችላሉ። ለዚህም በአሁኑ ወቅት እየተስፋፋ ያለው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አንድ ማሳያ እንደመሆኑ ማህበረሰቡም የሀገሩን ምርት የመጠቀም ልምድ ማዳበር አለበት።
ህንድ እራሷ አምርታ፣ አቅልማ፣ ሸምናና አዘጋጅታ መልበስ በመቻሏ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ከዓለም አንደኛ ሆናለች የምትለው ወይዘሮ ዮዲት፤ ኢትዮጵያም ዘርፉን ማሳደግ የሚያስችል ትልቅ አቅም እንዳላትና ገና እንዳልተጠቀመችበት ነው ያመለከተችው። እሷ እንዳለችው፤ እየተስፋፋ ያለውን የጋርመንት ኢንዱስትሪ መንግሥት መደገፍና ማበረታታ አለበት። ከዚህ አኳያ የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም፣ በትክክል የሚሰሩ ሰዎችን ለይቶ መደገፍ ግን ይኖርበታል። ይህን ማድረግ ከተቻለ ከውጭ የሚገቡ አልባሳትን ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ መተካት ይቻላል።
የቻይናና የዱባይ እንዲሁም ልባሽ ጨርቆች ገበያ ውስጥ በስፋት የሚታዩት በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ፍላጐት በመኖሩ ምክንያት ቢሆንም፤ የሀገር ውስጥ አምራቾች ዘመናዊ የስፌት ማሽን በመጠቀም ጥራት ያላቸውን ልብሶች እያመረቱ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችሉ ታስረዳለች። እሷም በዋናነት የምታመርታቸው የልጆችና የአዋቂ ቱታዎች በጅምላ ነጋዴዎች አማካኝነት ገበያ ውስጥ መግባት ችለዋል። በተለይም ከውጭ የሚገቡ የልጆች ቱታዎች ውድ በመሆናቸው የሀገር ውስጥ ቱታዎች በጣም ተፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል ነው ወይዘሮ ዮዲት የምትለው።
እሷ እንዳለችው አጠቃላይ የአልባሳቱ ዋጋ ከ300 እስከ 1600 ብር ነው። የአንድ ቲሸርት ትንሹ ዋጋ 300 ብር ሲሆን እንደ ሳይዙ 400 እና 500 ብር ድረስ አለ። የልጆች ቱታ ሱሪ ከነአላባሽ በ600 ብር ሲሸጥ ለአዋቂ የሚሆን ትልቅ ሳይዝ ቱታ ከነአላባሹ 1600 ብር እንደሚሸጥ አመላክታለች።
ኮዚ ዌር ካለው አቅም በላይ በስፋት ለማምረትና ገበያ ውስጥ ለመግባት የቦታ ጥበት ያለበት መሆኑን ያነሳችው ወይዘሮ ዮዲት፤ ለፋብሪካው የማስፋፊያ ቦታ እንዲሰጣት ለመንግሥት ጥያቄ እያቀረበች መሆኑን ገልጻለች። ጥያቄው ምላሽ አግኝቶ የፋብሪካ ማስፋፊያ ቦታ ካገኘች አሁን እየሰራችባቸው ካሉ ሶስት ዓይነት ማሽኖች በተጨማሪ ሌሎች ማሽኖችን እንዲሁም የሥራ ዕድል በመጨመር ዘርፉን የማስፋት ፍላጎት እንዳላት አጫውታናለች። በአሁኑ ወቅትም ቀንጫቢዎችን ጨምሮ ለአስር ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለች ሲሆን፤ የስፌት ሙያውን ይዘው ከመጡ ባለሙያዎች ውጭ የስፌት ፍላጎት ላላቸው ሠራተኞች ጭምር ሙያውን በማሰልጠን ወደ ሥራ እንዲገቡ ታደርጋለች።
አብዛኞቹ የልብስ ስፌት ባለሙያዎች ሴቶች እንደሆኑ የጠቀሰችው ወይዘሮ ዮዲት፤ ሴቶች የያዙትን ሥራ ትኩረት በመስጠት ጥንቅቅ አድርገው እንደሚሰሩ ተናግራለች። በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ በተለይም በልብስ ስፌት ዘርፍ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ጠቅሳ፣ ሴቶች ብዙ ለውጥ ለማምጣትና ዘርፉን ከፍ ለማድረግ እንደሚችሉ ያላትን እምነት ገልጻለች።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም