ዜጎች በቴሌ ቶን ዝግጅቱ ባላቸው አቅም ሁሉ ተሳታፊ መሆን ይጠበቅባቸዋል!

ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የአካባቢ ፅዳት ወሳኝ ነው፤ በተለይም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በተላላፊ በሽታዎች ምክንያት ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች ተጋላጭ በሆኑባቸው እንደ እኛ ባሉ ሀገራት፤ ችግሮቹን በቀላሉ መከላከል የሚቻለው በአካባቢ ንጽህና ዙሪያ ተገቢውን ግንዛቤ መፍጠር የቻለ ማኅበረሰብ መገንባት ሲቻል ነው።

የትኛውም ማኅበረሰብ ከንጽሕና ጋር የተያያዘ ዘመን ተሻጋሪ ፤ ከጓዳው ጀምሮ ያለውን የመኖሪያ አካባቢውን ለጤናው ሆነ ለሁለንተናዊ ማህበራዊ እንቅስቃሴው በሚያመች መልኩ የሚቃኝ የዳበረ ባህል አለው። ከንጽህና ጋር በተያያዘ፤ በዘመናት መካከል ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችንም አሸንፎ ዛሬ ላይ መድረስ የቻለውም እነዚህ ባህላዊ እሴቶች በፈጠሩት አቅም እንደሆነ ይታመናል።

እነዚህ እሴቶች እያንዳንዱ ዘመን በፈጠረው ዕውቀት እና የቴክኖሎጂ አቅም እያደጉ/ እየተሻሻሉ፤ አሁን ላይ የሰው ልጅ አካባቢውን በተሻለ መልኩ ለኑሮው አመች ማድረግ የሚችልበትን መልካም አጋጣሚ መፍጠር ችለዋል። ከአካባቢ ንጽሕና ጋር በተያያዘ ሊፈጠሩ የሚችል የበሽታ ወረርሽኞችንም በአግባቡ መቆጣጠር እንዲችል ረድተውታል።

ይህም ሆኖ ግን ዛሬም ከአካባቢ ንጽህና ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ የአመለካከት ክፍተቶች የዜጎቻችውን ሕይወት ለመገበር፤ ከፍተኛ ሀብታቸውን ለማባከን የተገደዱ ሀገራት ጥቂት የሚበሉ አይደሉም። በችግሩ ምክንያት ስለፈውስ የሚጮሁ በርካታ ድምጾችን የሚያስተናግዱ ብዙ ናቸው።

እንደ ሀገር በአካባቢ ንጽህና ዙሪያ ተገቢ ግንዛቤ ያለው ማኅበረሰብ ለመፍጠር ትኩረት ሰጥተው ባለመሥራታቸው፤ በቀላሉ የአካባቢን ንጽህና በመጠበቅ ብቻ መከላከል በሚቻሉ በሽታዎች በየወቅቱ የሚፈተኑ ሀገራት /ማኅበረሰብ ቁጥር በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

በተለይም በድሆቹ እና ኋላቀር በሚባሉ ሀገሮች ችግሩ መሠረታዊ የጤና ችግር እየሆነ ካሉበት ድህነት እና ኋላቀርነት ጋር ተዳምሮ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ሆኖባቸው ሕዝባቸው ለተጨማሪ የሕይወት ፈተና ተዳርጓል። ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያደርጉትንም ጥረት ውስብስብ አድርጎታል።

ችግሩ በእኛም ሀገር በጤናው ዘርፍ ለሚያጋጥሙ ሀገራዊ ተግዳሮቶች እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚቆጠር ነው። በሀገሪቱ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አካባቢን ለኑሮ በሚያመች መንገድ በንጽህና መያዝ የሚያስችሉ ዘመን ተሻጋሪ ማኅበራዊ እሴቶች ቢኖራቸውም ፣ ለእሴቶቹ እውቅና ሰጥቶ በተደራጀ መንገድ ወደ ሥራ መግባት አለመቻላችን “ሸክላ ሰሪ በሰባራ ገል ይበላል” እንደሚባለው ሆኖብናል።

በተለይም ንቃተ ህሊናው አድጓል የሚባለው በከተሞች አካባቢ የሚኖረው የማኅበረሰባችን ክፍል፣ ከዚያም ባለፈ በየከተሞች የሚገኙ የሕዝብ አስተዳደር አካላት ፣ ችግሩ እንደ ሀገር በሁለንተናዊ መንገድ ጤናማ ማኅበረሰብ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ፈተና መሆኑን ተረድተው ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ መንቀሳቀስ አለመቻላቸው የችግሩን አድማስ አስፍቶታል።

በተለይም የአፍሪካ መዲና፣ ሦስተኛዋ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ከተማ ለሆነችው አዲስ አበባ ችግሩ ከጤና ስጋት ባለፈም ፣ በብሔራዊ ክብራችን ላይ ያነጣጠረ ፈተና ነው። ከዚህም ባለፈ ለነገ የማንለው፣ ዛሬ ላይ ተረባርበን ዘላቂ መፍትሔ ልናስቀምጥለት የሚገባ፣ የዘመናዊነትና ለውጥ ተግዳሮት አንድ አካል አድርገን ልንወስደው የሚገባ ነው።

በለውጡ ማግስት ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የጀመርነው መራራ ትግል ከሁሉም በላይ በሁለንተናዊ መልኩ ጤናማ ማኅበረሰብን መገንባትን የሚጠይቀን ነው፤ ለዚህ ደግሞ የአካባቢ ንጽህና ካለው የጎላ አስተዋጽኦ አኳያ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን ልንቀሳቀስ ይገባል።

ከዚህ አኳያ መንግሥት አሁን ላይ ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት “የጽዱ ኢትዮጵያ ኑሮ ለጤና ትብብር ንቅናቄ” በሚል ቀደም ባለው ጊዜ በአዲስ አበባ የጀመረው እና በየክልሉ እየሰፋ ያለው ንቅናቄ እንደ ሀገር ጤናማ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ለጀመርነው ጥረት ስኬት መነሻ ትልቅ ስትራቴጂክ አቅም ነው።

መላው ሕዝባችን የንቅናቄውን ዓላማ ተገንዝቦ ለንቅናቄው እውቅና መስጠት፤ ራሱንም የንቅናቄው አካል ማድረግ ይጠበቅበታል። አካባቢውን በዘላቂነት በግል እና በቡድን ከማጽዳት አንስቶ ንቅናቄውን በገንዘብ ለመደገፍ ትልቅ ዕድል በሆነው በነገው የቴሌ ቶን ዝግጅት ባለው አቅም ሁሉ ተሳታፊ መሆንና ዐሻራውን ማስቀመጥ ይኖርበታል!።

አዲስ ዘመን  ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You