የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናትን እሴት ጨምሮ ለገበያ የማቅረብ ውጥን

ኢትዮጵያ እንደ ኦፓል፣ ኤመራልድ፣ ሳፋየር፣ ሩቢ፣ አጌት እና ኳርትዝ የመሳሰሉ በዓለም ላይ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት እምቅ ሀብት ያላት ሀገር ነች። ይሁን እንጂ እስካሁን ሀገሪቱ ያላትን እምቅ የማዕድን ሀብቶች በማልማት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን እንዲያስገኙ በማድረግ ረገድ የተሠሩ ሥራዎች እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም። በተለይ መኖራቸው እንኳን በጥናት የተረጋገጡት የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት በማልማት የውጭ ምንዛሪ ከማግኘት አኳያ የሚደረጉ ጥረቶች እምብዛም ውጤት እያስገኙ እንዳልሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በዓለም አቀፍ ደረጃ በከበሩና በጌጣጌጥ ማዕድናት ዘርፍ በዓመት 250 እስከ 300 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት ይንቀሳቀሳል። በኢትዮጵያም እስከ አለፈው ዓመት ድረስ ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን ዶላር ሀብት ያስገኘ ነው። ይህም የሚያሳየው የዓለምን ኢኮኖሚ እያንቀሳቀሰ የሚገኘውን ሀብት በሚገባ ለመጠቀም የሚያስችሉ ሥራዎች ከተሠራ አመርቂ ስኬቶችን ማግኘት እንደሚቻል ነው።

ከባለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን በመንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶት ሥራዎች በመሠራታቸው አበረታች ለውጦች እየታዩ ነው። በተለይ ደግሞ የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት ለውጭ ገበያ በመላክ ለኢኮኖሚ ጠቀሜታ እንዲውሉ የማልማት ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በአሁኑ ወቅት የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን እንዲያመጡ እየተደረገ ይገኛል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የሚበልጠውን ገበያ የያዙት ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨመርባቸው በጥሬው የሚላኩት ማዕድናት ናቸው።

የዘርፉን የአምስት ዓመታት የውጭ ገበያ መረጃ ይህንኑ የሚያመላክት ነው። በአምስት ዓመታት ለውጭ ገበያ ከተላኩት የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት 95 በመቶ ያህሉ በጥሬው (ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨመርባቸው) እየተላኩ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ አምስት በመቶ ያህሉ ብቻ እሴት ተጨምሮባቸው የሚላኩ መሆኑን ነው።

ይህም ሀገሪቱ ያላትን የማዕድን ሀብት በማልማት ከማዕድናቱ ማግኘት የሚገባት የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ብዙ ሥራዎች መሥራት እንደሚጠይቅ ያመላክታል። በተለይ በዚህ ዲጂታል ዘመን ያደጉ ሀገራት የደረሱበት ርቀት ላይ ለመድረስና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችሉ አማራጮችን መጠቀምን ይጠይቃል። ለዚህም በዘርፉ ከተሰማሩ አካላት ብዙ ይጠበቃል።

በማዕድን ዘርፉ ተሰማርተው ሀገሪቷ ያላትን የማዕድን ሀብት ለማስተዋወቅ እየሠሩ ካሉ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን አንዱ ነው። ኮርፖሬሽኑ ላለፉት 80 ዓመታት በማዕድን ዘርፍ ተሰማርቶ እየሠራ የቆየው ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት በዓለም እንዲተዋወቅና ደረጃቸውን የጠበቁ የማዕድናት ጌጣጌጦች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲመረቱ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል።

ኮርፖሬሽኑ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ የማዕድን፣ ነዳጅ እና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ሲሆን፤ የስም ለውጥ አድርጎ የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን ተብሎ በአዋጅ ቁጥር 462/2012 እንደገና የተቋቋመ የልማት ድርጅት ነው። የተቋቋመበት ዓላማም በማዕድን፣ በነዳጅና በባዩ ፊውል ሥራዎች፣ ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍ የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት በተገቢው ሁኔታ በማልማት ተጠቃሚ እንድትሆን ማስቻል ነው።

የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን ተወካይ ዳይሬክተር አቶ አሕመድ አባጊሳ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ማዕድን ኮርፖሬሽን በማዕድን ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ እየሠራ ያለ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው። ኮርፖሬሽኑ በማዕድን ዘርፍ የማዕድናት ፍለጋና ቁፋሮ፣ ማዕድናትን መመርመርና መለየት፣ የከበሩ ማዕድናት ለገበያ ማቅረብና እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ መላክ፣ ለዘርፉ ስልጠናዎች መስጠት እንዲሁም ማማከር እና መስል ሥራዎችን ይሰራል።

ኮርፖሬሸኑ ያለው ረጅም ዓመታት ልምድ በመጠቀም የኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት እያደረገ መሆኑን አቶ አሕመድ ያመላክታሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የተለያዩ ለውጦች በማድረግ በዘርፉ ይበልጥ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል። ኢትዮጵያ ያላት የማዕድን ሀብት መጠቀም እንድትችል በበኩሉን ድርሻ ለመወጣት በርካታ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይ የከበሩ ማዕድናት ላይ እሴት ጨምሮ የውጭ ምንዛሪን ከፍ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት ለዓለም በማስተዋወቅ በዲጂታል ገበያ አማካይነት ማዕድናት ለገበያ በማቅረብ ሀገሪቱ ማግኘት የሚገባት የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ እንዲሁም ሕገ ወጥ የማዕድን ዝውውር ለማስቀረት ጥረት እየተደረገም መሆኑንም አመላክተዋል።

‹‹ኮርፖሬሽኑ በሰው ኃይል እና በቁሳቁስ ቀደም ሲል ከነበረው በላይ በማጠናከር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ በመንግሥት ኃላፊነት ተሰጥቶት እየሠራ ነው›› ያሉት አቶ አሕመድ፤ ወርቅ፣ ታንታለም፣ የከበሩ ማዕድናት፣ ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት እና ሌሎች በርካታ ማዕድናት ዓይነቶች ብዙ ሥራዎችን እንደሚሰራ አስታወቀዋል። በተለይም በኢትዮጵያ በሚገኙ የከበሩ ማዕድናት ኦፓል፣ ኤመራልድ፣ ሳፋየር እና ሌሎች ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ ለማቅረብ ጥረቶች እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል። አሁን ላይ ኦፓል ማዕድን ላይ በስፋት የተሠራ መሆኑን ጠቅሰው ፤ ሌሎችም ከዚሁ ጋር ተያያዥ የሆኑ የከበሩ ማዕድናት ላይ ብዙ ተግባራትን ለማከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ በሙያ የሰለጠኑ ብቁ ባለሙያዎች እና አስፈላጊ የሆኑ ማሽኖች አሟልቶ የያዘ የከበሩ ማዕድናት የማበልጸጊያ ወርክሾፕ ያለ መሆኑን የገለጹት አቶ አሕመድ፤ በወርክሾፑ የከበሩ ማዕድናትን በመቅረጽ ደረጃቸው የጠበቁ ጌጣጌጦችን ለማምረቻነት እንደሚያገለግል አስታወቀዋል። የጌጣጌጦቹን በብርና በወርቅ ለመሥራት የሚሰራበት ማሽን ለመግዛት ሂደት ላይ መሆኑን ይገልጻሉ። አሁን ላይ ማዕድናቱን በመቅረጽ የአንገት ሀብል ፣ የእጅ አምባር እና የጆሮ ጉትቻ እና የመሳሰሉ በርካታ ጌጣጌጦች እየተሠሩ መሆኑን ያመላክታሉ። በተጨማሪም ከወርቅ እና ከብር ጋር የተለበጠ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኙ የሚችሉ የተለያዩ ዓይነት የጌጣጌጥ ምርቶች እንደሚያመርትም አብራርተዋል።

‹‹የከበሩ ማዕድናት ላይ የሚሰሩት ሥራዎች እያሳደገን በተለያየ መልኩ በመሥራት ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውሉ እያደረግን ነው›› የሚሉት ተወካይ ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ በርካታ ያልታወቁ ማዕድናት ያሏት ሲሆን፤ ኦፓል ደግሞ በጣም ረጅም ዓመት ያልቆየ በቅርብ እየታወቀ ያለ ነው። በመሆኑም ኦፓል በጥሬና እሴት ተጨምሮበት የሚሸጥበት ሁኔታ መኖሩን ይገልጻሉ። ‹‹ የከበሩ ማዕድናት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥም ያላቸው ድርሻ ውስን ስለሆነ ማዕድናቱን በማስተዋወቅ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከፍ ለማድረግ ጭምር እየተሠራ ነው›› ብለዋል።

ማዕድናቱ የውጭ ምንዛሪን ከፍ እንዲል እሴት መጨመርና ዲጂታል ገበያን መጠቀም አማራጭ ማድረጉን ተናግረዋል። አሁን ላይ የከበሩ ማዕድናት መሸጫ ሱቆች በማደራጀት እና በዋናው መሥሪያ ቤት፣ በኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ የውጭ ተርሚናል ላይ እንዲኖር ማድረግ የከበሩ ማዕድናት ለሽያጭ እያቀረቡ መሆኑን አመላክተዋል።

በተጨማሪም ዲጂታል ገበያ በመጠቀምም ሆነ እሴት በመጨመር ማዕድናቱን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው። የከበሩ ማዕድናት በዲጂታል ገበያ ለመሸጥ በዳሽን ባንክ፣ በኢግል ላይን እና በማስተር ካርድ በዓለም ገበያ ተወዳደሮ ለመሸጥ የሚያስችለው ዝግጅቱ ተጠናቅቋል።

የከበሩ ማዕድናት በማስተዋወቅ በሀገሪቱ እድገት ውስጥ የበኩላቸው ድርሻ እንዲጫወቱ ተጨባጭ የሆኑ ሥራዎችን እየተሠሩ ነው ያሉት አሕመድ አባጊሶ፤ ይህን ሥራ የበለጠ እያጠናከሩ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም ይገልጻሉ። ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ በዓለም ላይ ዘመናዊ የሆኑ የከበሩ ማዕድናት ከወርቅና ከብር ጋር ማራኪ በሆነ መልኩ መሥራት የሚያስችሉ የተለያዩ ማቴሪያሎችን እና ጌጣጌጦች ለመግዛት በዝግጅት ላይ እንደሆኑም አክለው ገልጸዋል። ‹‹የዓለም ሀገራት ተሞክሮን ስንመለከት በከበሩ ማዕድናት የሚታወቁ እንደ ህንድ፣ ቱርክ የመሳሰሉ ሀገራት በዘርፉ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። በመሆኑን እነዚህ ማቴሪያሎች ከእነዚህ ሀገራት በማስመጣት ማዕድናቱ ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ መሆን ይቻላል›› ሲሉ አስረድተዋል።

ኮርፖሬሽኑ ማዕድናቱን በዘርፍ ከተሰማሩ አነስተኛ አምራቾች የሚወሰድ ሲሆን፤ ከአራት ወራት በፊት የከበሩ ማዕድናት በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ 34 የሚሆኑ አነስተኛ አምራቾችን ማህበራትን ስልጠና መስጠቱን ተናግረዋል። ስልጠናውም ማዕድናቱን እንዴት ተቀነባብረው ወደ ገበያ በመቀየር እንደሚችሉና ማዘዋወር የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ግንዛቤ እንዲያገኙ ተደርጓል። ከስልጠናው በኋላ ማህበራቱ የሚሳተፉበትን የማዕድን ዓይነት በመለየት፤ በኮርፖሬሽኑ በጋር መሥራት የሚችሉበት ሥርዓትም መዘርጋቱን አመላክተዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ላይ ማዕድናቱ ከተለያየ የኢትዮጵያ አካባቢ (ከትግራይ፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉልና ጋምቤላ ክልል ይመጣሉ። ኦፓል በስፋት በሚመረትበት በአማራ ክልል በወሎ ደላንታ አካባቢ ሲሆን፤ ኦፓል በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ ማህበራትን በስፋት በማስልጠን ሕጋዊ በሆነ የማዘዋወሪያ ፈቃድ ማዕድኑን ለድርጅቱ እንዲሸጡ እየተደረገ ነው። ኮርፖሬሽኑ ማዕድናት ሲገዛ ሕጋዊ መስመር በተከተለ መልኩ የሚሰሩ ማህበራት ጋር ስለሚሰራ በማዕድን ላይ የሚነሳው ሕገ ወጥነት በመከላከል ሕጋዊ ሥርዓትን ተከትለው የሚሰሩ ማህበራት እንዲስፋፉ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

ይህም ሕገ ወጥ የማዕድን ሽያጭና ዝውውር በማስቀረት ሕጋዊ መስመር የተከተለ አሠራር እንዲኖር ያደርጋል። በተጨማሪም ባልተገባ መልኩ ወደ ውጭ ይወጣ የነበረው ማዕድን ማስቀረት ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ በዲጂታል ገበያ አማካይነት ማዕድናቱን በተለያዩ መሸጫ ሱቆች እና በዲጂታል ገበያ ለሀገር ውስጥ ሆነ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ መሆኑን የሚገልጹት አቶ አሕመድ አባጊሳ፤ በተለይ በዲጂታል ገበያ ሀገሪቷ ያሉትን ማዕድናት በዓለም ገበያ በማስተዋወቅ ማዕድናት እንዲሸጡ በማድረግ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪም እንዲጨምር የሚደረግ መሆኑ ያመላክታሉ። በዚህም ሀገሪቱም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባት የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የከበሩ ማዕድናት እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ በማቅረብ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት አቶ አሕመድ አባጊሳ፤ እሴት በመጨመር ረገድ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ትልቅ ሥራ የሚጠይቅ እንደሆነ ይገልጻሉ። ሆኖም ግን አስፈላጊ የሆኑ ማቴሪያሎችን በመግዛት እሴት በመጨመር ከተሠራ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ መሆን የሚቻልበት ሥርዓት እንዲኖር ያስችላል ሲሉ አስገንዘበዋል።

‹‹አሁን ላይ በከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት ዙሪያ እየተሠራ ያለው ሥራ ማዕድኑ በኢኮኖሚ ያለውን ሚና እየተወጣ ነው የሚባል ባይሆንም ፤ በሂደት እያደገ ያለ መሆኑ ያሳያል›› ያሉት ተወካይ ዳይሬክተሩ፤ እሴት ጭመራ ላይ ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች ስላሉ በሚፈለገው ልክ ለመሥራት ብዙ ጥረቶችን እንደሚደረግ አመላክተዋል።

‹‹ማዕድን የሀገራችንን ብልጽግና ከሚረጋገጥባቸው የኢኮኖሚ ምሰሶች አንዱ ሆኖ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው›› ያሉት ተወካይ ዳይሬክተሩ፤ በባለፈው ጥቅምት ወር በማዕድን ሚኒስቴር የተዘጋጀው የማዕድን ኤክስፖ ማዕድናት በዓለም እንዲተዋወቁ ያስችል እንደሆነ አንስተዋል። በተጨማሪም ማዕድን ሀገሪቷ ኢኮኖሚ ውስጥ ሊኖረው የሚችለው ድርሻ እንዲወጣ፣ ሕገ ወጥነት ለማስቀረት፣ ጥራት ያለው የማዕድን ሥራ እንዲሠራ፣ በጥናት ላይ የተመሠረተ ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ ዓይን መክፈቻ እንደነበር አስገንዘበዋል።

ኮርፖሬሽኑም በኤክስፖ ተሳታፊ እንደነበር አስታወሰው፤ በማዕድን በሀገሪቱ እድገት ውስጥ የበኩል ድርሻ እንዲወጣ ሰፊ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ያመላክተዋል። በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ውጤት እየተመዘገበ እንደሆነ ገልጸዋል።

የማዕድን ፍለጋውም ሆነ የማምረት ሥራው ሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚካሄድ በመሆናቸው የሚያጋጥሙ የተለያዩ ተግዳሮቶች መኖራቸው የጠቀሱት ተወካይ ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ ከሰላምና ጸጥታ ጋር ተያይዘው የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በሂደት እየተፈቱና እየተስተካከሉ የመጡበት ሁኔታ ስላለ ወደፊት ለማዕድን ሥራው አጋዥ የሆኑ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ ያላት የማዕድን ሀብቶች እና ሌሎች ሀብቶች ለማውጣትና ለመጠቀም ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ከዘርፉ ሀገሪቱ እንድትጠቀም እየተደረጉ ያለው ጥረቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ አቶ አሕመድ አባጊሳ ሃሳባቸው አጠቃለዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ግንቦት 2 /2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You