ድርጅቱ 700 ሺህ ዜጎችን የበጎ ተግባራት ተጠቃሚ አድርጓል

አዲስ አበባ፡- በዘንድሮ ዓመት በተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት ለ700 ሺህ ዜጎች ተደራሽ መሆን መቻሉን ኤስ.ኦ.ኤስ የሕፃናት መንደር አስታወቀ።

ኤስ ኦ ኤስ የሕፃናት መንደር 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን አስመልክቶ በትናንትናው እለት መግለጫ ሰጥቷል። በመግለጫው ወቅት የኤስ.ኦ.ኤስ የሀገር ውስጥ ዳይሬክተር አቶ ሳህለማርያም አበበ እንደገለጹት፤ ድርጅቱ በዘንድሮ ዓመት በአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ ድጋፍ፣ በትምህርት፣ ወጣቶችን በማብቃት እና በአማራጭ የቤተሰብ ክብካቤ ለ700 ሺህ ዜጎች ተደራሽ መሆን ችሏል።

ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎች በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት ስምንት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዜጎች ተደራሽ መሆን ችሏል። ተቋሙ በሀገሪቱ በዘጠኝ ክልሎች እየሠራ ይገኛል ያሉት አቶ ሳህለማርያም፤ እ.ኤ.አ በ2027 በአክሱም፣ በደሴ፣ በሰመራ እና አርባ ምንጭ ተጨማሪ የማስተባበሪያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ማቀዱን አስረድተዋል።

በሚገነቡት እና በነባር የማስተባበሪያ ጣቢያዎች የበጎ አድራጎት ተደራሾችን ቁጥር ከ700 ሺህ ወደ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ለማድረስ እቅድ ተይዟል። ለዚህም 210 ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፤ እቅዱን ለማሳካት የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የተለያዩ ገቢ የማሰባሰቢያ ሥራዎች በመሥራት ላይ ይገኛል ብለዋል። በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖሊሲ እና ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ትብስት ሰለሞን (ዶ/ር) ሚኒስትሯን ወክለው ባቀረቡት መልዕክት እንደገለጹት፤ ሕፃናት የተሻለ ስልጠና አግኝተው በተሟላ የአመጋገብ ሥርዓት የሀገራቸውን እሴት ጠብቀው እና በራሳቸው ታሪክና ባህል ሊያድጉ ይገባል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ መመሪያዎች በመቅረጽ እና ተቋማዊ አሠራሮች በመዘርጋት ከፌዴራል እስከ ክልል ባለው መዋቅር እየሠራ ሲሆን፤ በሚሰሩ ሥራዎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

ዶክተር ትብስት እንደገለጹት፤ ኤስ ኦ ኤስ ድርጅትም መንግሥታዊ ካልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች አንዱ እንደመሆኑ፤ በተለያዩ ክልሎች አሳዳጊ የሌላቸውን ሕፃናት በማሳደግ፣ ወላጆችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች በመሥራት ላይ ነው።

ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከኤስ ኦ ኤስ ተሞክሮ በመውሰድ ኢትዮጵያ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለማደግ የምታደርገውን ጥረት እንዲደግፍ በማለት ጥሪ አቅርበዋል። በሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው፤ በጎ አድራጎት ድርጅቱ አሳዳጊ ሕፃናት በመልካም መንገድ በማሳደግ ለሀገር የሚጠቅም ፍሬያማ ትውልድ ማፍራት ችሏል።

በተጨማሪም የተለያየ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋ ሲደርስ በጎ አድራጎት ድርጅቱ ከፍተኛ በጀት በመመደብ አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠ ያለ ተቋም ነው ሲሉ አስረድተዋል። የበጎ አድራጎት ድርጅቱ በ50 ዓመት ጉዞ ያጋጠሙ ብርታቶች እና ጥንካሬዎች ቀምሮ በማስቀመጥ ለሌሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ተሞክሮ ሊሰጥ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ግንቦት 2 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You