የጆርጂያ ፕሬዚዳንት ተቃውሞ ያስነሳውን አዋጅ ውድቅ አደረጉት

የጆርጂያ ፕሬዚዳንት በሀገሪቱ ለሳምንታት ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳውን “የውጭ ኤጀንት” የተሰኘው ሕግ ውድቅ አደረጉት። ባለፈው ማክሰኞ የጆርጂያ የሕዝብ እንደራሴዎች ያፀደቁት አወዛጋቢ አዋጅ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ገለልተኛ ሚድያዎች 20 በመቶ ገቢያቸውን የሚያገኙት ከሀገሪቱ ውጭ ከሆነ “የውጭ ኃይሎችን አቋም የሚያንፀባርቁ” ተብለው ይፈረጁ ይላል።

ፕሬዚዳንት ሳሎሜ ዞራቢቺቪሊ እንዳሉት፤ አዋጁ “በመንፈስ እና በቅርፅ ሩሲያዊ ነው”፤ አልፎም ጆርጂያ የአውሮፓ ኅብረት አባል ለመሆን የምታደርገውን ሂደት የሚያደናቅፍ ነው። ፕሬዚዳንቷ አዋጁን ውድቅ ቢያደርጉትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጆርጂያን ድሪም ፓርቲ ድጋሚ ድምፅ እንዲሰጥበት ካደረገ አዋጁን ሊያፀድቁ የሚችሉ በቂ የፓርላማ አባላት አሉት።

በቴሌቪዥን በተላለፈ ሥርጭት ቅዳሜ ዕለት ንግግር ያሰሙት ፕሬዚዳንቷ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸው “ሕጋዊነት ያለው ነው” ብለዋል።“ይህ ሕግ ምንም ዓይነት ለውጥ የሚደረግበት አይደለም። በቀላሉ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ነው። ይህ ሕግ ሊሻር አይገባም” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንት ሳሎሜ የጠቅላይ ሚኒስትር ኢራክሊ ኮባኺድዜ ተቃዋሚ ሲሆኑ፤ ሕጉን ውድቅ እንደሚያደርጉት ይጠበቅ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ኢራክሊ በበኩላቸው፤ ወጣቶቹ ተቃዋሚዎች 10 ተወካዮች መርጠው ስለአወዛጋቢው ሕግ የሚደረግ ውይይት ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢንተርፕረስ ኒውስ ኤጀንሲ አርብ ዕለት እንደዘገበው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አስፈላጊ የሚባሉ የወጣቶችን ድምፅ መስማት ብቻ ሳይሆን ልጋራቸውም እፈልጋለሁ። ታድያ እነሱም ተመሳሳይ ባህሪ እንዲኖራቸው እጠብቃለሁ” ብለዋል።

ተቺዎች ይህ ሕግ ሕዝቧን የምትጨቁነው ሩሲያ ድምጾችን ለማፈን የምትጠቀምበት ነው በማለት ነቀፌታ ያሰማሉ። ጆርጂያ ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ነው የአውሮፓ ኅብረት አባል ለመሆን የዕጩነት ማዕረግ የተሰጣት። አንዳንዶቹ አዲሱ ሕግ ጆርጂያ የኅብረቱ አባል እንዳትሆን እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

የአውሮፓ ኅብረት አባል ለመሆን ዕጩ ሀገራት የፀረ-ሙስና ሕግ ተግባራዊ ማድረግ እና የመንግሥት ግልፀኝነትን ማስፋት እንዲሁም ሲቪል ሶሳይቲን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል። ሕጉን ተቃውመው አደባባይ የወጡ ጆርጂያዊያን ለአንድ ወር ያክል ድምጻቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።

ማህበራዊ ሚድያ ላይ የተለጠፉ ፎቶዎች እና ቪድዮዎች እንደሚያሳዩት፤ ተቃዋሚዎቹ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You