የቴክኖሎጂ ተግባራትን ለውጤት የሚያበቃ አሠራር በፖሊሲ ተደግፎ እየተተገበረ ነው

አዲስ አበባ፦ ለሀገራዊ ልማቱ መቀላጠፍ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ተግባራትን የሚደግፍና ለውጤት የሚያበቃ አሠራር በፖሊሲ ጭምር ተደግፎ እየተተገበረ እንደሚገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ መርቀው የከፈቱት ስትራይድ ኢትዮጵያ 2024 ኤክስፖ “ሳይንስ በር ይከፍታል፣ ቴክኖሎጂ ያስተሳስራል፣ ፈጠራ ወደፊት ያለምዳል’’ በሚል መሪ ቃል በሳይንስ ሙዚየም ለሕዝብ ትናንት ክፍት ተደርጓል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ኤክስፖውን በሳይንስ ሙዚየም በከፈቱበት ወቅት እንደገለጹት፤ ኤክስፖው በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። መንግሥት የቴክኖሎጂ ሃሳቦችን በማሰባሰብ ሀገራዊ ልማቱን የሚያቀላጥፉና ችግር ፈቺ የሆኑ የምርምር፣ የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራትን ለማሻሻል የሚያግዙ አሠራሮች እየተገበረ ነው። ስትራይድ ኢትዮጵያ 2024 ኤክስፖም የዚሁ አንድ አካል ነው።

ለሀገራዊ ልማቱ መቀላጠፍ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ተግባራትን የሚደግፍና ለውጤት የሚያበቃ አሠራር በፖሊሲ ጭምር ተደግፎ እየተተገበረ ይገኛል ያሉት ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር)፤ በዚህም የባለድርሻ አካላትን የማገናኘት፣ እንደሀገር የተደረሰበትን ቴክኖሎጂ የመገምገም፣ የኢኖቬሽን ሥነ ምህዳር እና የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

እነዚህ ሥራዎች ዓለም አቀፍ እውቀትና ልምድ ለመቅሰም ከአላቸው ሚና በዘለለ ቴክኖሎጂንና ፈጠራን በትብብር ለመሥራት የላቀ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተናግረው፤ ሚኒስቴሩ ለሀገር እድገትና ልማት ለሚበጁ አዳዲስ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች ተገቢውን እገዛ እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ይህም ኢንተርፕራይዝ አቋቁሞ የፈጠራ ሥራዎችን እስከ መደገፍ እንደሚደርስ ጠቅሰው፤ እውቀት ኑሯቸው ሀብት የሌላቸውን በማገዝ ለውጤት እንዲበቁ የማድረግ ሥራዎች በመሠራት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የስትራይድ ኢትዮጵያ 2024 ዓላማ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርምር፣ ኢኖቬሽን፣ ዲጂታልላይዜሽን እና ኢንተርፕረነርሺፕ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ለማስተዋወቅ፣ በአገልግሎት ሰጪ እና ተቀባይ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርና ትብብር ለመፍጠር እንደሆነም ገልጸዋል።

የመንግሥት ተቋማት፣ ባንኮች እና የኢ-ኮመርስ ድርጅቶች፣ ኩባንያዎች፣ የፈጠራ ሥነ ምህዳር ገንቢና ተዋናዮች፣ የግሉ ዘርፍ የአይሲቲ ኩባንያዎች በኤክስፖው ተሳታፊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የፓናል ውይይት መድረኮች፣ በኢንዱስትሪው ልዩ አበርክቶ ላላቸው አካላት የተዘጋጁ የእውቅና እና የሽልማት ፕሮግራሞች፣ የማነቃቂያ መድረኮች፣ የወጣቶች እና የታዳጊዎች ዝግጅቶች ጨምሮ በርካታ ሁነቶች በኤክስፖው እንደሚካሄዱም ተናግረዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You