ቲክቶክ ተጠቃሚዎች የ60 ደቂቃ ቪዲዮ እንዲጭኑ ለመፍቀድ ሙከራ እያደረገ ነው

ቲክቶክ ተጠቃሚዎች የ60 ደቂቃ ቪዲዮ እንዲጭኑ ለመፍቀድ ሙከራ እያደረገ መሆኑን ገለጸ። በአጫጭር ቪዲዮዎች ተወዳጅነትን ያተረፈው ቲክቶክ፣ ተጠቃሚዎች እስከ 60 ደቂቃ የሚረዝም ቪዲዮ እንዲጭኑ ለመፍቀድ ሙከራ እያደረገ መሆኑን ያሆ ቴክ ዘግቧል።

ቲክቶክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2017 በአሜሪካ ሲጀምር 15 ሰከንድ ብቻ የሚቆይ ቪዲዮ ነበር መጫን የሚቻለው። ነገር ግን ንብረትነቱ የቻይናው ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባይቲዳንስ የሆነው ቲክቶክ ከእዚያ ጀምሮ ባሉት ዓመታት ገደቡን እያሻሻለ አሁን ላይ ተጠቃሚዎች ለ10 ደቂቃ የሚቆይ ቪዲዮ እንዲጭኑ ፈቅዷል።

ባለፈው ጥር ወር ደግሞ የተወሰኑ የኮንቴንት ክሬተሮች ወይም ይዘት አዘጋጆች 30 ደቂቃ የሚረዝሙ ቪዲዮዎች እንዲጭኑ የፈቀደ ሲሆን፤ ሰብስክሪፕሽን(አባልነት) የሚሸጡ ደግሞ እስከ 20 ደቂቃ የሚረዝም ቪዲዮዎችን እንዲጭኑ መፍቀዱ ይታወሳል። ቲክቶክ አሁን ላይ የሚጫኑ ቪዲዮዎችን የጊዜ እርዝማኔ በድጋሚ ስለመጨመር እያሰበ ነው።

ቲክቶክ ባለፈው አርብ እለት ለሲቢኤስ ኒውስ እንዳረጋገጠው፤ ይህ ማሻሻያ በቅርቡ ይለቀቃል ተብሎ ባይገመትም፣ የተወሰኑ ተጠቃሚዎች አሁን የ60 ደቂቃ ቪዲዮ መጫን ይችላሉ። አሁን የሙከራ ወቅት ላይ መሆኑን የገለጸው የቲክቶክ ኩባንያ፤ አዳዲስ አሠራሮችን ቋሚ ከማድረጉ በፊት ሁልጊዜም ሙከራ እንደሚያካሂድ ገልጿል።

የማህበራዊ ሚዲያ አማካሪ የሆነው ማት ናቫራ ቲክቶክ ሙከራ መጀመሩን የሚያሳይ መልእክት ከደረሳቸው ውስጥ አንዱ ነው። “እስከ 60 ደቂቃ የሚረዝም ቪዲዮ ጫን። መተግበሪያው አፕቱዴት ወይም የተሻሻለ መሆኑን ካረጋገጥህ በኋላ ከመተግበርህ ወይም ከዴስክቶፕ ቲክቶክ.ኮም(tiktok.com) ጫን” ይላል ለናቫራ የደረሰው መልእክት።

የቲክቶክ በአጫጭር ቪዲዮዎች ተወዳጅነት ማግኘት እንዲሜታ እና ዩቲዩብ ያሉ ትልልቅ ኩባንያዎች ተመሳሳይ የሆነ የአጭር ቪዲዮ ማጋሪያ ፕላትፎርሞችን እንዲጨምሩ አስገድዷቸዋል። ቲክቶክ በአንጻሩ በአሜሪካ ያለው እጣፈንታ እክል የገጠመው ቢሆንም ቀስ እያለ ረዘም ያሉ ይዘቶች እንዲጫኑ እያደረገ ነው።

ባለፈው ሚያዝያ ወር ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባይትዳንስ በዘጠኝ ወራት ውስጥ የማይሸጠው ከሆነ ቲክቶክ በአሜሪካ እንዲታገድ የሚያስችል ሕግ ፈርመዋል። ቲክቶክ እና ባይቲዳንስ በሰጡት ምላሽ እርምጃው ሕገ መንግሥታዊ አይደለም በማለት ክስ ማቅረባቸውን አል ዐይን ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You