በዞኑ የወባ ወረርሽኝ 74 በመቶ መድረሱ ተገለጸ

ሚዛን አማን፡– በዞኑ የወባ ወረርሽኝ 74 በመቶ መድረሱን የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን ገለጹ፡፡ ችግሩ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚያሻው ጠቁመዋል፡፡

አቶ ሀብታሙ ካፍትን ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ በቤንች ሸኮ ዞን የወባ ወረርሽኝ መጠን 74 በመቶ ደርሷል፡፡ የወባ የዞኑ ትልቅ ፈተና ሁኗል፡፡ አንድ ሰው እስከ 20 ዙር ድረስ በወባ በሽታ እየተያዘ ነው፡፡ በቅርቡ በተደረገው ግምገማም ወረርሽኙ እየጨመረ እንደሚገኝ ያሳያል፡፡

አካባቢው ሦስት ዓመት ሙሉ በወባ ወረርሽኝ ውስጥ ቆይቷል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ የወባ ወረርሽኝ ዝርያውን ቀይሯል የሚል መረጃ እየወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወረርሽኙን ለመቀነስ በማህበረሰብ ንቅናቄ ውሃ የተኛባቸውን አካባቢዎች ቦይ በማውጣት እንዲፋሰስ የማድረግ እና የኬሚካል ርጭት መከናወኑን የገለጹት አቶ ሀብታሙ፤ ለሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ አጎበር መሰራጨቱን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ፤ ስርጭቱን በማህበረሰብ ንቅናቄ ለመቆጣጠር ሙከራ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ስርጭቱን መቀነስ አልተቻለም፡፡ የወባው ዝርያ ቀይሯል የሚል ሃሳብ በመነሳቱ ይህንን በጥናት ለማረጋገጥ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡

አሁን ላይ በሁሉም ቦታ ርጭት ለማድረግ ኬሚካል አቅርቦት ውስንነት እንዳለ የጠቆሙት አቶ ሀብታሙ፤ ዞኑ በወረርሽኝ ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ችግሩን ታሳቢ ያደረገ ኬሚካል አቅርቦትና ስርጭት ሊኖር እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የኬሚካል ድጋፉ በልዩ ሁኔታ ታስቦበት ድጋፍ እንዲደረግ በዞኑ ለምልከታ ለመጡ የሕዝብ ተወካዮች ቋሚ ኮሚቴ መግለጻቸውን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ ዞኑ ከሌሎች አካባቢዎች በከፍተኛ ሁኔታ ወረርሽኝ ውስጥ ስለሆነ እንደሌሎች መድኃኒቶች በነበረው ቀመር ከሚሰጥ ይልቅ 74 በመቶ የሆነ የወባ ወረርሽኝ ውስጥ እንደሚገኝ ዞን በልዩ ሁኔታ ሊታይ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤልያስ ምናሴ በበኩላቸው፤ አዲሱ ክልል ከተመሰረተ ወዲህ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በቤንች ሸኮ ዞን ለረጅም ጊዜ የቆየ እና 74 በመቶ የሚደርስ የወባ ወረርሽኝ አለ፡፡ ይህም ኅብረተሰቡን ለከፋ ችግር እየዳረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከመከላከል አኳያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ መዋቅሮች የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ አንጻር በሚዛን አማን ወረዳ ከአጋጠመው የአጎበር እጥረት ውጪ በዞኑ ለሚገኙ ወረዳዎች በሙሉ አጎበር መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡

ከኬሚካል ርጭርት ጋር ተያይዞ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ርጭት ቢደረግም ስርጭቱን መቆጣጠር አለመቻሉን አመልክተዋል፡፡

የፌዴራል የጤና ሚኒስቴር ጉዳዩን እንደሚያውቅ እና ችግሩን ለመቅረፍ ባለሙያዎችን በመላክ ጭምር በርካታ ሙከራዎች ቢደረግም ወረርሽኙን ማስቆም አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ባለሙያዎች እንዲሁም የቦንጋ እና ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በመተባበር የችግሩን ምንነት ለማወቅ እና መፍትሔ ለማበጀት ጥናት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ወረርሽኙ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ለሚመለከተው አካል ቢያሳውቁም፤ እስካሁን ችግሩን መቅረፍ የሚያስችል ምላሽ አለማግኘታቸውን አቶ ኤልያስ ጠቁመዋል፡፡

ሞገስ ተስፋና ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You