የ‹‹ሚኒማሊዝም›› እሳቤ በመጠኑ መዘነጥ

በፋሽን ኢንዱስትሪው ዘናጭ ፣ ፋሽን ተከታይ፣ ስም ያላቸውን ልብሶች ምርጫቸው የሚያደርጉ አለፍ ሲል ደግሞ ከስሙ እና ከወቅታዊነቱ በላይ ምቾታቸውን የሚያስበልጡ ሰዎች ማግኘት የተለመደ ነው፡፡ ፋሽን ተከታይ ሰዎች በእንግድነት በተጠሩባቸው ቦታዎች የሚመርጧቸውን ልብሶች ለብሰው ከማማር በዘለለ የወቅቱን ፋሽን የተከተለ አለባበስ ይመርጣሉ፡፡

ይህም በእለት ተዕለት ሕይወታቸው በሚጠቀሟቸው አልባሳት ላይም ይገለጻል፡፡ እነዚህ ሰዎች ‹‹ፋሽን መከተል›› የሚል ሃሳብ ተገዢ ናቸው፤ በዚህ የተነሳም ፋሽን መከተላቸው ከዓለም እኩል የመራመድ ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጉ ይመስላቸዋል፡፡

በፋሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ የዓለም አቀፍ ግብይት መስፋፋትን ተከትሎ ስም ያላቸውና በኢንዱስትሪው ላይ ተጽዕኖ የፈጠሩ የፋሽን ኩባንያዎች በሌሎች ሀገራት ያሉ ዜጎች አዳዲስ ምርቶችን በቶሎ እንዲጋሩ እያደረጉ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ፋሽን ተከታዮች በዘመናዊው ፋሽን አልያም ፈጣን እና እጅግ ተለዋዋጭ የፋሽን ኡደት በሚለው እሳቤ ውስጥ የወደቁበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ሁኔታው እነዚህ ሰዎች ዘመናዊ ፋሽን እና ፈጣን ፋሽን የሚሉ እሳቤዎች ሰዎች ለኑሯቸው ከሚያስፈልጓቸው በላይ ልብሶችን በመደርደሪያቸው ላይ እንዲያከማቹ አድርጓቸዋል፡፡ ከፋሽን ኢንዱስትሪው በዘለለም ሰዎች አሁን ላይ ትርጉም ያለው ሕይወት ከመኖር ይልቅ ከልክ በላይ ቁሳቁስ በመሰብሰብ እንዲጠመዱ እንዳደረጋቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ሰዎች በዚህ ተጽዕኖ ስር እንዲሆኑ ያደረጓቸው ሌሎች ምክንያቶች ደግሞ ከመጠን በላይ ለሆኑ መረጃዎች ተጋላጭ መሆናቸው ፣ በመገናኛ ብዙሃን የሚተዋወቁና ፍጹም የተጋነኑ የሰዎችን አዕምሮ የሚቆጣጠሩ የፋሽን ማስታወቂያዎች እና ራሳቸውን በዙሪያቸው ካሉ ሰዎች ጋር ማነጻጸራቸው ነው፡፡

የእነዚህ ጫናዎች ውጤት ደግሞ ያሏቸውን አልባሳት በቂ እንዳልሆኑ አርገው እንዲሰማቸው ሌሎች ሰዎች ላይ የሚያዩት መዋቢያ ፣ በሱቅ ውስጥ ተሰቅለው የሚዩዋቸው ልብሶች ደግመው ሳያስቡ እንዲገዙ ፣ በሚያደንቋቸውና ታዋቂ በሚባሉ ሰዎች ላይ ያዩዋቸውን ፋሽኖች አብዝተው በመጠቀም ሱስ ውስጥ እንዲወድቁ ፤ በየጊዜው ልብስ ለመግዛት ብለው የሚያወጡትን ወጪም መቆጣጠር እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል፡፡

እነዚህ ሰዎች ያንን ማድረግ ባልቻሉበት ጊዜ ወደኋላ የመቅረት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡ በመደርደሪያ ውስጥ ተሰቅለው የሚመለከቷቸው ልብሶች ፋሽን በቂ እንዳልሆነ ያስባሉ፡፡ በአብዛኛው ጊዜም ሴቶች በልብስ መስቀያቸው ላይ በርከት ያሉ አልባሳት ቢኖሯቸውም ‹‹ምንም ልብስ የለኝም፣ አልፎበታል ፣ የምሄድበትን ቦታ አይመጥንም ›› የሚል ድብርት እና ውድድር ውስጥ ይገባሉ፡፡

እነዚህ ዓይነት ሰዎች አብዝተው ለቁሳቁስ ተገዢ መሆን ያሳሰባቸው ወገኖች ደግሞ በመጠኑ መኖር የሚል እሳቤን ማስተዋወቅ ጀምረዋል፡፡ ይህ የአኗኗር ዘይቤ በእለት ተዕለት አለባበሳችን ላይ የሚሰራ ሲሆን፣ በመጠኑ መዘነጥ በእንግሊዘኛው ደግሞ ‹‹ Minimalism Fash­ion›› ተብሎ ይጠራል ፡፡

‹‹ሚኒማሊዝም›› ወይንም በመጠኑ የመዘነጥ እሳቤ ሰዎች በሕይወት ከሚኖሩለት አላማ ጋር ተያይዞ ለቁስ ተገዢ ሳይሆኑ ውስን በሆኑና በርግጥም የሚያስፈልጋቸውንና ደስታና ምቾት የሚሰጣቸውን አለባበስ ብቻ ተከትለው ሕይወታቸውን እንዲመሩ የሚያስችል ነው፡፡

ሃሳቡ በፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ቀደም ተብሎ እንደተጀመረ ይነገርለታል፡፡ ይህ ሃሳብ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ የመጣ ሲሆን፤ ይህን የሕይወት መርህ የሚከተሉ ሰዎች ከጥድፊያና ከውድድር ሕይወት ወጥተው ደስታ እና እርጋታ የተሞላበትን ሕይወት እንዲመሩ እንዳስቻላቸውም ይነገራል፡፡

በመጠኑ የመዘነጥ ሃሳብም ትኩረቱን የሚያደርገው ከብዛት ይልቅ ጥራት ላይ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ልብስ ለመምርጥ የሚያጠፉትን ጊዜ ለመቀነስ ሲሉ ተመሳሳይ የቀለም ዓይነትና በጥሩ የጥራት ደረጃ ላይ የሚገኙ ልብሶችን በርከት አድርገው በመግዛት ሕይወታቸውን ይመራሉ፡፡ ይህም አንዱ በመጠኑ የመዘነጥ አካሄድ ሲሆን፣ ሰዎች መቀነስ የፈለጉትን ነገር በማመዘን በተለያየ መንገድ ሊተገብሩት ይችላሉ፡፡

በመጠኑ የመዘነጥ እሳቤን የሚከተሉ ሰዎች ከብዛት ይልቅ ጥራት፣ ሌሎች ሰዎች ላይ አይተው ከወደዱት ልብስ ይልቅ፣ ከራሳቸው የሰውነት ቅርጽ እና ከሚወዱት የአለባበስ ዓይነት ፣ ወቅቱን የጠበቀ ነው ከተባለለት ፋሽን ይልቅ ምቾት ላይ ትኩረታቸውን ያደርጋሉ፡፡

‹‹የሚኒማሊዝም ፋሽን››ን የሚከተሉ ሰዎች በአብዛኛው ከቆዳ ቀለማቸውና ከሰውነት ቅርጻቸው ጋር ጥናት አድርገው የሚለብሱ በመሆናቸው ሃሳቡ በመጠን የማነስ ጉዳይ ቢሆንም በእይታ ግን ለየት ያሉ እና በጣም ዘናጭ ሆነው እንዲታዩ ያደርጋቸዋል፡፡

በዚህ የፋሽን ዓይነት በብዛት ተመራጭ የሚሆኑት የቀለም ዓይነቶች ከማንኛውም ልብስ ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉ እና ተቀናጅተው ቢለበሱ ውበትን ማላበስ የሚችሉ የቀለም ዓይነቶች ናቸው፤ ጥቁር ፣ ነጭ ፣ ቤዥ እና ብዙውን ጊዜ ደመቅ ያላሉ የቀለም ዓይነቶች ይህንን እሳቤ በሚከተሉ ሰዎች የልብስ መስቀያ ውስጥ ሊታዩ ይችላሉ፡፡

ገቢውን በተለያየ ጊዜያት በሚገዛቸው፣ ነገር ግን ደስታ በማያገኝባቸው ልብሶች የጨረሰ፣ በየጊዜው አዳዲስ ልብሶች መግዛት ቶሎ በሚሰለቹ ፋሽኖች ሳጥኑ የሞላ ሰው በመጠኑ መዘነጥ የሚለውን ሕግ ለመከተል ለረጅም ጊዜ ሳይለብሳቸው የቆዩ ልብሶችን ከመደርደሪያው ላይ በማስወገድ የሚወዳቸውን ብቻ ለይቶ ማስቀረት ይኖርበታል፡፡ ከዚያም የልብስ ምርጫውን ጥራት ፣ ትክክለኛ ፍላጎትና ምቾት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ያደርጋል፡፡

ሰዎች በመጠኑ የመኖር አልያም የመዘነጥ እሳቤን ሲተገብሩ ገንዘባቸውን በመቆጠብ ሌላ ቁም ነገር ላይ ሊያውሉት ይችላሉ፡፡ በየእለቱ ከእንቅልፋቸው ሲነሱ ምን ልልበስ በሚል ጭንቀት ውስጥ አይወድቁም፤ ሰዓታቸውን ልብስ በመምረጥም አባክኑም፡፡ ጊዜው የጥድፊያ እና የውድድር እንደመሆኑ ይህም ሃሳብ ገበያውን ብቻ ሳይሆን የሰዎችን የግል ሕይወት እና ስሜት እየተቆጣጠረ ይገኛል፡፡

በመጠኑ የመዘነጥ ሃሳብ ሰዎች ውስን በሆኑ አልባሳት፣ ምቾት በሚሰጧቸው እና ምርጫቸው ባረፈባቸው አልባሳት ብቻ ጥራቱን የጠበቀ የአለባበስ ስብጥር በራሳቸው ፈጥረው እንዲኖሩ ያስላቸዋል፡፡ ሃሳቡ ሰዎችን ከአላስፈላጊ ወጪ ያድናል፤ ራሳቸውን ከሌሎች ጋር ለማወዳደር በሚያደርጉት ጥረት ሊከሰትባቸው ከሚችለው የአዕምሮ መታወክ እንዲጠበቁ ያደርጋል፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You