የኢንዱስትሪው ዘርፍ በቂ ድጋፍ እና ጠንካራ ክትትል ከተደረገለት ውጤታማ እንደሚሆን በተጨባጭ ታይቷል!

የለውጡ ኃይል መንግሥት ከሆነ ማግስት ጀምሮ ሀገሪቱን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ማሸጋገር የሚያስችሉ የተለያዩ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቷል፤ አሁንም እያደረገም ይገኛል። በዚህም እንደ ሀገር እየተመዘገበ ያለው ውጤት በብዙ መልኩ ተስፋ ሰጭ እንደሆነ መታዘብ እየቻልን ነው።

ለውጡ ገና ከጅምሩ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች አኳያ፣ በነፃ ህሊና ሁኔታዎችን ማየት እና መገምገም ለሚችል ሰው እውነታው ብዙም የሚያነጋግር አይደለም፣ ዓይን ከፍቶ በማየት ብዙውን ነገር መመስከር የሚቻልበት ሁኔታ ሰፊ ነው።

በተለይም መንግሥት ድህነትን ታሪክ በማድረግ ሀገር እና ሕዝብን ከጠባቂነት/ከተመጽዋችነት ለመታደግ ተግባራዊ እያደረገ ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ሀገርን በክፉ ቀን ማሻገር የሚያስችል አቅም መገንባት አስችሏል፣ ለውጡ ብዙ ፈተናዎችን ተሻግሮ ዛሬ ላይ እንዲደርስ ጉልበት ሆኗል።

የፖሊሲው ዓላማ በዋነኛነት ለግብርና፣ ለቱሪዝም፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለዲጅታል ቴክኖሎጂ እና ለማዕድን ዘርፍ ስትራቴጂክ ትኩረት የሰጠ ፤ በየዘርፉ ያለውን አቅም በጥናት በማረጋገጥ አልምቶ ሀገር እና ሕዝብን ተጠቃሚ በማድረግ ብልጽግናን እውን ማድረግ ነው።

በተለይም ለኢንዱስትሪው ዘርፍ በፖሊሲው ውስጥ የተሰጠው ትኩረት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም ለዘመናት ከነበረበት ከግብር እና ከአገልግሎት ዘርፎች ወጥቶ በዋንኛነት በኢንዱስትሪ ላይ እንዲመሠረት ማድረግ የሚያስችል፤ ሀገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለምታደርገው ጉዞ መንገድ ጠራጊ ተደርጎም የሚወሰድ ነው።

ለኢንዱስትሪው ዘርፍ በፖሊሲ ደረጃ የተሰጠው ትኩረት፤ ከዛም ባለፈ ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በተሻለ መንገድ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ለማዋል የተሻለ ዕድል የሚፈጥር፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን አምራች የሰው ኃይል ወደ ሥራ ለማስገባት ስትራቴጂክ አቅም የሆነም ጭምር ነው።

የኢንዱስትሪው ዘርፍ ስትራቴጂ፤ ሀገሪቱ በሁለንተናዊ መልኩ ማስመዝገብ ለምትፈልገው ልማት ትልቅ አቅም እንደሚሆን፤ በተለያዩ ምክንያቶች ለዘመናት ተቀዛቅዞ የኖረውን የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ዘርፍ በማነቃቃት ወደ አዲስ ምዕራፍ ማሸጋገር እንደሚያስችልም ይታመናል።

ይህን ታሳቢ በማድረግም መንግሥት ቀደም ሲል በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ የቢሮክራሲ ችግሮችን ለዘለቄታው ከመፍታት ጀምሮ፤ ከፍተኛ ሀብት በመመደብ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በስፋት በመገንባት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ መሳ ተፍ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች የተመቻቹ ሁ ኔታዎችን እየ ፈጠረ ይገኛል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች እና ሶስት የግብርና ማቀነባበሪያዎች ተገንብተዋል። በቀጣይም ፍላጎቶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተጨማሪ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ለዘርፉ መነቃቃት መንግሥት ዝግጁ መሆኑንም በተለያየ አጋጣሚዎች መግለጹ ይታወሳል፡፡

“ኢትዮጵያ_ታምርት እኛም_እንሸምት” በሚል መሪ ቃል ዘርፉን ለማነቃቃት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ሀገራዊ ንቅናቄው በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ ያቆሙ፤ ከአቅማቸው በታች ሲያመርቱ የነበሩ ፋብሪካዎችን ችግር በመፍታት ወደ ምርት እንዲገቡ አስችለዋል፤ አዳዲስ ባለሀብቶችም ዘርፉን እንዲቀላቀሉ አድርጓል።

ንቅናቄው ዘርፉን ከማነቃቃት ባለፈ ፤ አምራች ኢንዱስትሪውን ከገበያ ጋር በማስተሳሰር ፤ ዘላቂ የሀገር ውስጥ ገበያ መፍጠር አስችሏል። ዜጎች በሀገራቸው ኢንዱስትሪዎች የሚመረቱ ሸቀጦችን እንዲያውቁ እና ጠንካራ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩም መልካም ዕድል ፈጥሯል።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ሀገርን ከከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ መታደግ አስችሏል። ለአብነትም ባለፉት 9 ወራት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከውጭ ሀገር ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል።

በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች በዚህ ዓመት ብቻ “ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሽምት” በሚል መሪ ቃል 83 የምርት ማስተዋወቂያ ኤክስፖዎች ተካሂደዋል፡፡ በእነዚህ ኤክስፖዎችም 3,223 ያህል አምራች ኢንዱስትሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡ 10.78 ቢሊየን ብር የገበያ ትስስር እንዲፈጠር በማድረግም ዘርፉን አነቃቅተዋል።

በርግጥም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊስ እንደተቀመጠው እና ተስፋ እንደተደረገው፣ ዘርፉ በቂ ድጋፍ እና ጠንካራ ክትትል ከተደረገለት በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የላቀ ስፍራ እንደሚኖረው ሀገራዊ ንቅናቄ በተጨባጭ አሳይቷል። ይህንን እውነታ በአግባቡ ተረድቶ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ በዘርፉ የሚገኙ ተዋንያን የጋራ ኃላፊነት ነው!

አዲስ ዘመን ግንቦት 2 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You