የኢትዮ – አሜሪካ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን የሚዳስስ የፎቶ ኤግዚቢሽን እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፡– የኢትዮ – አሜሪካ የ120ኛ ዓመት የሁለትዮሽ ግንኙነትን ምክንያት በማድረግ የሁለቱን ሀገራት የዲፕሎማሲ ጉዞ የሚያሳይ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን ተከፍቷል።

ኤግዚቢሽኑ ከሚያዚያ 30 እስከ ግንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን እ.ኤ.አ ከ1903 በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስካሁን ያለው የሁለቱን ሀገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት ጉዞ የሚያሳይ ነው።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያና የአሜሪካ የሁለትዮሽ ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የተጀመረው በዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት እ.ኤ.አ ከ1903 ነው። በዚያን ጊዜ በዳግማዊ አጼ ምኒልክና በአሜሪካው ተወካይ ሮበርት እስኪነር መካከል የንግድ ስምምነት ተፈርሟል።

ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ከሚገኙ ሀገራት መካከል ከአሜሪካ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላት ሀገር ናት ያሉት አቶ ስለሺ፤ ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በፀጥታና ደህንነት፣ በጤና፣ በትምህርት እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች በትብብር እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

እንደ አቶ ስለሺ ገለጻ፤ ሀገራቱ የሕዝብ ለሕዝብ እና የባህል ግንኙነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በአሜሪካ የሚኖሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች ለዚህ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

አቶ ስለሺ እንዳሉት፤ ለእይታ የቀረበው የፎቶ-

 

ግራፍ ኤግዚቢሽን በሀገራቱ መካከል የነበረው የቆየ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት የሚያሳይ ነው።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው፤ ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ጊዜ በቆየ የዲፕሎማቲክ ግንኙነታቸው በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና እንዲሁም በኢኮኖሚ እድገት በጋራ መራታቸውን የፎቶ ኤግዚቢሽኑ ያሳያል ብለዋል።

ኤግዚቢሽኑ የሁለቱ ሀገራት የቆየ ግንኙነት መረጃ በመስጠት በቀጣይ ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር የሚያስችል ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ የፎቶ ኤግዚቢሽኑ የተዘጋጀው የሁለቱ ሀገራት የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ጉዞ በዓል ምክንያት በማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ፣ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የኤምባሲው ሠራተኞች በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ግንቦት 2 /2016 ዓ.ም

Recommended For You