ስታርት አፕን ለሀገራዊ እድገት

ስታርት አፕ ሲባል ማንኛውም በአነስተኛ ደረጃ የተጀመረ የሥራ መስክ ማለት አይደለም። ስታርት አፕ ሃሳብ በፈጠራ ሃሳብ (ኢኖቬቲቭ አይዲያ )ቴክኖሎጂን ተንተርሶ አንድን ችግር ለመፍታት የሚቋቋም ዘር ማለት ነው። ቴክኖሎጂን ካልተጠቀመ የፈጠራ ሃሳብ ከሌለ እና የሚፈታው ችግር ከሌለ ሥራ መጀመር ብቻ ስታርት አፕ አያስብለውም።

ስታርት አፕ ማለት ይሄ ነው ካልን በኋላ ግን ይሄ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይም አዲስ ቋንቋ ነው ከቴክኖሎጂ ውልደት እና መብዛት ጋር ተያይዞ የመጣ እሳቤ ነው። የቆየ ቀደም ሲል የሚነገር ቋንቋ ሳይሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም ላይ እየተነገረ የመጣ ቋንቋ ነው በእኛም ሀገር ከጠቀሜታው አንጻር ስታርት አፕ የሚሉ ቋንቋዎች በመጠኑም ቢሆን እየተነገሩ መጥተዋል።

ብዙ ጊዜ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚፈጠሩ ሥራዎችን የሚፈጥሩት ሁለት እና ከዛ በላይ ሰዎች ናቸው። የአፈጣጠር ባህሪው እራሱ የቡድን ሥራ በጋራ የመሥራት ባህሪ እና ዝንባሌ አለው፤ እስካሁን በታየው ልምድ ዓለም ላይ ስኬታማ የሆኑ ስታርት አፖች ዕድሜያቸው በአማካይ ከሠላሳ አምስት እስከ አርባ የሚደርሱ ሰዎች ናቸው። በስታርት አፕ የተሳካላቸው የሚባሉት እነዚሁ ነበሩ ።

ስታርት አፕ ላይ ለሚሳተፉ ሃሳብ አለን የሚሉ ትናንሽ ተቋማት መፍጠር እንችላለን ማደግ እንችላለን የሚሉ ወጣቶች ግን አሁን አሁን ብቅ እያሉ በዘርፉም ስኬትን እየተቆናጠጡ ነው። ነገር ግን እነዚህ ወጣቶች ወደ ሥራ ፈጠራው መግባታቸው በጣም ጥሩና የሚበረታታ እንደ ሀገርም ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም ያሰቡበተ ስኬት ላይ ለመድረስ ግን መጀመሪያ አራቱን የ“መ” መርህዎችን (ፕሪንሲፕል) መከተል ወይም ማሟላት ይኖርባቸዋል። እነዚህን አላሟሉም ማለት ግን ሥራውን ቢጀምሩትም ስኬት ይሉት ደረጃ ላይ መድረሱ አስጊ ነው የሚሆነው። አራቱን “መ” ዎች ካላሟሉ ግን ከ 90 በመቶ በላይ ስኬታማ ነው የሚሆኑት ።

አራቱ “መ”ዎች ምንድናቸው?

የመጀመሪያው ሊሰሩት ያሰቡትን ነገር ሐሳብ “መውደድ” ነው ፍቅሩ አለኝ? ወይ እወደዋለሁ ወይ? የሚለውን ነገር ለራሳቸው መመለስ ይገባቸዋል፤ ምክንያቱም ሰው የሚወደውን ነገር ሲሰራ አያደክምም። አይሰበርም፣ መከራን ቢያሸክመውም እንኳን አይከብደውም ስለዚህ መጀመሪያ መውደድን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ሁለተኛው ደግሞ መውደድ ብቻውን በቂ ስላልሆነ “መቻል’’ ያስፈልጋል። ሥራውን እችለዋለሁ ወይ? የሚለውን መመለስም ግድ ነው። ለምሳሌ አውሮፕላን በአየር ላይ ሲሄድ አይተህን በጣም ደስ ይለናል ግን አውሮፕላን መሥራት እንደምንችል ካላሰብን መተው ነው ያለብን እኔ ሃሳብ አለኝ ምናምን ማለት ውጤታማ አያደርግም። ከመውደድ ቀጥሎ መቻልንም ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

መውደድ እና መቻል በቂ ስላይደሉ ሶስተኛው ስታርት አፕን ስኬታማ የሚያደርገው ነገር “መፈለግ’’ ነው። ያ የምንወደው እና የምንችለው ነገር በማርኬቱ በገበያው በሕዝብ ይፈለጋል ወይ? ገበያ አለው ወይ? ሰዎች የሚያደምጡት የሚፈልጉት የሚገዙት ነገር ነው ወይ? የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል።

አራተኛው “መሸጥ’’ ነው ገንዘብ ማምጣት ነው። መውደድ፣ መቻል፣ መፈለግ፣ መሽጥ። እነዚህን አራት “መ” ዎች ማሳካት እንግዲህ በስታርት አፕ ሂደት ላይ ስኬታማ እንደሚያደርግ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ ሀገራችን መለስ ስንል ሀገራችንም በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድል እንዳላት የሚያመላክቱ ነገሮች ያሉ ሲሆን እነሱንም እውን ለማድረግና ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት እያደረገች ትገኛለች። ለምሳሌ የማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል፣ ዘመናዊ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ግብርናን ዘመናዊ በማድረግ በምግብ ራስን ለመቻል፣ ለጤና ብሎም በወታደራዊ አገልግሎት ላይ ውጤታማ ለመሆን ቴክኖሎጂ መሠረታዊ ነገር መሆኑም ገብቶን ወደ ሥራ ገብተናል።

የቴክኖሎጂ አቅም ማደግም ከሀገር ውስጥ አገልግሎትን ከማሻሻል አንስቶ በውጭ ሀገራት ለሚገኙ በዚህ ዘርፍ ያሉ የቴክኖሎጂ ፍላጎቶችን ለማሟላት የራሱን አስተዋፅኦ የሚያደርግ ነው። አሁን ላይ ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂ ልማት ሰፊ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑን በመንግሥት ተደጋግሞ ይገለፃል። የዚሁ አካል የሆነ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም ከመጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለሶስት ሳምንት ያህል ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› በሚል ዓውደ ርዕይ ሲካሄድ ሰንብቷል። በዓውደ ርዕዩም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ‹‹ስታርት አፖች›› ሥራዎቻቸውን አስተዋውቀዋል፤ እንደ ሀገርም ቴክኖሎጂን መሠረት ባደረጉ የሥራ ፈጠራዎች ላይ የደረስንበትን ደረጃ የሚቀሩንን ሥራዎች ለማየትና ለመታዘብ ችለናል።

በእለቱ በርካታ ወጣቶች በቴክኖሎጂው ዘርፍ ሥራን ፈጥረው ለውጭ ሀገራት ካምፓኒዎች በማገልገል ዶላር የሚያመጡ ወጣቶች መኖራቸውንም አይተናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም አሜሪካ ውስጥ ለሚገኘው “ማክዶናልድ” ለተባለ ምግበ አቅራቢ ተቋም የሚሰሩ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች መኖራቸውን በ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› ዓውደ ርዕይ ላይ መክፈቻ ላይ ተናግረው አረጋግጠዋል። ታዲያ ይህን ተስፋ ሰጪ ጅምር ከግቡ እንዲደርስ ሰዎችን የማብቃት ሥራው ተጠናክሮም መቀጠል ያለበት ነው።

በየዓመቱ የሚመረቁ የሶፍትዌር ኢንጂነሮች፤ የአይቲ ባለሙያዎችም የዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያለን ሥራ በመሥራት በሀገራቸው ተቀምጠው ራሳቸውን ጠቅመው ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪን እንዲያስገኙም ማበረታታቱ ከዚህ መጀመር አለበት ። በሌላ በኩል ደግሞ በሀገር ውስጥ ያሉ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ሀገሪቱ ያላትን ርካሽ የሰው ጉልበት በመጠቀም የሥራ አጦችን ቁጥር መቀነስ ይቻላል። የሀገራችን የሰዓት አቆጣጠራችን ለብዙ ሀገራት የተመቸ መሆኑ፤ በቴክኖሎጂው የሰለጠኑ ወጣቶች መበርከታቸው በተወሰነ ስልጠና ለገበያው የተስማሙ ብቁ አቅም ያላቸው ወጣቶች መኖራቸው የውጭውን ፍላጎት ለመያዝ ያስችለናል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቴክኖሎጂው ዓለም ውስጥ በርካታ እቅም ያላቸው፤ የቴክኖሎጂ እውቀታቸው የላቀ ወጣቶች እየተፈጠሩ ነው ወጣቶች ቴክኖሎጂን የመረዳት አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑ ለዚህ አስተዋፅኦ አድርጓል።

አሁን ያለው የትምህርት ሁኔታ በተለይም በከተማ አካባቢ ወጣቶችን የሚያበቃ ነው። ከዚህ አንጻር ከቴክኖሎጂ አንድ ነገርን ይዞ በትእግስት የመጨረስ አቅም ያላቸውን ወጣቶች እያፈራን ነው። ወጣቶች ይህንን ሥራ መሥራታቸው በራሱ ሌላ አቅም የሚፈጥር ሆኗል።

በሚገርም ሁኔታ ወጣት ሴቶች እንኳን አግብተው፤ ወልደው ቤት ውስጥ ሆነው መሥራት የሚችሉበት የቴክኖሎጂ ሥራ ነው። በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን ትምህርት ማግኘት በእጅ ያለ ስለሆነ በስልክ መማር እና መሥራት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

በሀገሪቱ በርካታ ሶፍትዌር ኢንጂነሮች መገኘታቸው፤ ሥራ ፈጣሪዎች መበራከታቸው፤ በቀደመ ጊዜ ከነበረው በተለየ ለቴክኖሎጂ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ መስክ ወደፊት እንደምትራመድ አመላካች ነው።

ከታላላቆቹ እኩል መራመድ እንችል ዘንድ፤ እየተፈጠረ ያለውን የቴክኖሎጂ ግብዓት የታጠቀ ትውልድ ማፍራት አስፈላጊ ነው። ስለዚህም አሁን ስታርት አፖችን ለማበረታታት የተወሰደው ዓይነት ገንቢ አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ይህ የስታርት አፕ ሥራ በሀገራችን እውን ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተናገሩት ይህንን ነው፤” እንደ መንግሥት በፈጠራ ላይ የተመሠረተና የመፍትሔ ሃሳብ ያላቸውን ‘ስታርት አፖች’ መደገፍ ኢንቨስትመንት እንጂ ርዳታ አይደለም “ስታርት አፕ” ማለት ማንኛውም ሥራ ሳይሆን በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ፣ ገቢ የሚያመነጭ እንዲሁም ለአንድ ጉዳይ መፍትሔ ያለው አዲስ የሥራ ፈጠራ ነው። ስታርት አፖችን መደገፍ ከቻልን የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ” ብለውም ነበር።

የግብር ገቢንም ማሳደግ ይቻላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እንደ መንግሥት በጋራ ጥቅም ላይ በመመስረት በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ ሃሳቦች ወደተግባር እንዲወርዱ የተለያዩ ሥራዎችን አከናውነናል፤ በቀጣይም እናከናውናለን። በዓለም ላይ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሀብት ያላቸው አንድ ሺህ 200 ስታርት አፖች አሉ፤ በአጠቃላይ ሀብታቸው አራት ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ደርሷል። ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን አንድ ቢሊዮን ዶላር ሀብት ያለው ስታርት አፕ አለመፈጠሩንና ጉዳዩ በጅማሮ ላይ ያለ መሆኑን መዘግየትን ቢያመለክትም። ከአምስት ዓመታት በፊት በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ 50 ስታርት አፖች መኖራቸውን ግን ማስታወስ እንደሚገባ አነስተዋል፤ አሁን ላይ ግን ቁጥራቸው 900 መድረሳቸውና ከቁጥር ዕድገቱ ባለፈ በተለያዩ መስኮች ላይ የተሰማሩ መሆናቸው እንደሀገር ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል። መንግሥት በፖሊሲ፣ የቴክኖሎጂ ማዕከላትን በማስፋፋት እንዲሁም ምቹ አሠራርን በማስተዋወቅ ስታርት አፖችን ለማበረታታት ሰፊ ሥራ እያከናወነ ነው።

የፈጠራ ሥራዎቹ ግን በዋነኛነት በግሉ ዘርፍ እንጂ በመንግሥት የሚከናወኑ ባለመሆናቸው ሁሉም የበኩሉን ጥረት ሊያደርግ ይገባል ሲሉም ነበር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት። ወጣቶች አዲስ ፈጠራ ሲጀምሩ በቅድሚያ ሥራውን መውደድ፣ ቀጥሎም ሥራውን በራሱ መቻላቸውን ማረጋገጥ እንዲሁም ፈጠራው ተፈላጊና በገበያ ላይ ሊሸጥ የሚችል መሆኑን ማወቅ አለባቸው ሲሉ አስረድተዋል። ወጣቶች ትልቅ አስበው ከትንሽ በመነሳት ለሀገር የሚተርፍ የፈጠራ ሥራ ማከናወን እንዲሁም ውስጣቸው ያለውን ችግር ፈቺ የፈጠራ ሃሳብ ወደተግባር በማዋል ገቢ መፍጠር እንዳለባቸው አመላክተዋል::

የስታርታፕ አውዱ ጅማሮ ላይ ቢሆንም ችግሮች ግን የሉበትም ማለትም አይደለም ፤ የኢንተርኔት ዋጋ፣ የቢሮ ኪራይ፣ የኤሌክትሪክ ዋጋው ሲታይ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ለስታርት አፖች ውድ ቢሆንም በጋራ በመደጋገፍ ስኬታማ መሆን ይቻላል:: ከለውጡ በፊት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፋይናንስ አገልግሎት (ፊንቴክ) የሚያከናውን ካለ በሕግ ደረጃ ወንጀለኛ ሆኖ ተጠያቂ ይሆን ነበር ፤ አሁን ላይ ግን በርካታ ተቋማት በዘርፉ ተሰማርተው ገንዘብ እያንቀሳቀሱ ይገኛሉ። መንግሥት ስታርት አፖችን መደገፍ ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘቡ የተለያዩ ማበረታቻዎችን እያደረገም ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ግንቦት 2 /2016 ዓ.ም

 

Recommended For You