
አዲስ አበባ፦ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ሞዴል መመሪያና ውል ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች መላኩን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የቤቶች ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጸጋዬ ሞሼ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 24 ቀን 2016ዓ.ም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ አጽድቋል። አዋጁ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ በሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፤ ለተፈጻሚነቱም ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የአዋጁን ወጥ አፈጻጸም የመከታተል ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን፤ ለዚህም ጥብቅ ክትትል የሚያደርግ ቡድን በማዋቀር ወደ ሥራ ገብቷል ያሉት አቶ ጸጋዬ፤ አዋጁ ወጥ አፈጻጸም እንዲኖረው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ ሞዴል መመሪያና ውል ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች ተልኳል ብለዋል።
ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተላከላቸውን ሞዴል መመሪያና ውል ከነባራዊ ሁኔታዎቻቸው ጋር አጣጥመው ይጠቀማሉ ያሉት አቶ ጸጋዬ፤ አዋጁን በሚገባ ለማስፈጸም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አስፈጻሚ አካላትን የማደራጀትና የሰው ኃይል የማጠናከር ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል ብለዋል።
ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎችን ከመሥራት አንጻር አመራሩንና ፈጻሚውን፣ አከራዩን እና ተከራዩን የማወያየት ሥራዎች በየደረጃው እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ጸጋዬ፤ አዋጁ የአከራዮችን እና የተከራዮችን ጥቅምና መሠረታዊ መብቶች ሚዛን በጠበቀ መልኩ ለማስተናገድ የሚያስችል በመሆኑ ለተፈፃሚነቱ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ጸጋዬ ገለጻ፤ ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች በተላከው ሞዴል መመሪያ መሠረት ጥቆማ የሚቀርብባቸው ጉዳዮችና የጥቆማ አቀራረብ ሥርዓት የተመላከተ ሲሆን፤ ጥቆማ የሚቀርበውም ቤቱ በሚገኝበት የታችኛው የቤቶች ልማት አስተዳደር ጽህፈት ቤት ማለትም በወረዳ ወይም በቀበሌ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ነው። ጥቆማው በየደረጃው እየታየ ችግሩ እንዲፈታ የሚደረግ ይሆናል።
በዋናነት ውል የሚመዘገበው በታችኛው መዋቅር ማለትም በወረዳ ወይም በቀበሌ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ጽህፈት ቤቶች መሆኑን ገልጸው፤ የተለየ ሁኔታዎች ካሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ውል የሚመዘግቡባቸውን ቦታዎች በማስታወቂያ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
አዋጁ በአከራይም ሆነ በተከራይ ላይ ጫና የማይፈጥር እና የአከራይንና የተከራይና መብት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የሚያስጠብቅ በመሆኑ በሚገባ ወደ መሬት እንዲወርድ አከራዩም ተከራዩም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር ሥርዓት ለኢትዮጵያ አዲስ ቢሆንም በሌሎች ሀገራት የተለመደና ለረዥም ጊዜ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ መሆኑንም ተናግረዋል።
አቶ ጸጋዬ፤ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለማቃለል የቤት አቅርቦት ላይ በሰፊው መሥራት እንደሚገባ አመልክተው፤ ለዚህም በመንግሥት ከሚደረግ የቤት አቅርቦት በተጨማሪ የግል ዘርፉ በቤት ልማት እንዲሰማራ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየገባ ነው ብለዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን የቤት አስተዳደርን በሚገባ መምራት የሚገባ ከመሆኑ አንጻር ይህ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅ በሚገባ ማስፈጸም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም