ማህበራዊ ሚዲያ ለብዙዎች የነጻ ንግግር መብታቸው እንዲከበር ያደረገውን ያህል በዚያኑ ልክ የብዙዎቹ ድብቅ አሉታዊ ባህሪ ጎልቶ እንዲወጣም አድርጎታል:: ከሁሉ በላይ ግን ጎልቶ እንዲወጣ ያደረገው በሁላችንም ውስጥ የተደበቀውን አምባገነንነት ባህሪ ነው:: ይህን ለማለት ለረጅም ጊዜ የማህበራዊ ሚዲያ ውይይታችንን ማስተዋል በቂ ነው::
እኔ ምደግፈውን ካልደገፍክ፣ የምቃወመውን ካልተቃወምክ ብሎ የሚበሻሸቀው ሰው ቁጥር አንድና ሁለት አይደለም:: በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚስተዋለው በብሔር፣ ሃይማኖትንና ማንነት ላይ መሰረት ያደረገ የስድብና እና የእርግማን አይነት እጅን በአፍ እንደሚያስጭን ማንም የሚያውቀው ሀቅ ነው:: መቃወም መብት ነው:: በመቃወም እና በመሳደብ መካከል ግን ሰፊ ልዩነት አለ:: የብዙዎች ተቃውሞ ሳይሆን ስድብ ነው::
ስድቡ ደግሞ አጸያፊ ከመሆኑ የተነሳ ይሄ ስድብ ሃይማኖተኛ ነው ከሚባል ህዝብ የሚወጣ አይመስልም:: ያሳፍራል:: የበለጠ አሳፋሪው ነገር ደግሞ አንድን ሰው ሆን ብሎ ለመጉዳት ቤተሰብ ላይ ሳይቀር የሚወርደው ስድብ ዘግናኝ መሆኑ ነው:: የሞተ ዘመድ አዝማድ ሳይቀር ይሰደባል:: ይህ ጸያፍና ነውር ነው:: ይህ ክብረ ነክ ነው::
ብዙዎቻችን በነጻነት ሃሳብን ስለመግለጽ ስንሟገት በጣም ኃይለኞች ነን:: ሁሌም መንግሥትን የምንተቸው በዚህ ነው:: እገሌ ብእር ብቻ ነው የያዘው፤ ብእር የያዘን ሰው ማሰር ፍርሀት ነው ምናምን የሚለው ሰው ቁጥር ጥቂት አይደለም:: ነገር ግን የመናገር ነጻነትን በመቀማት ከመንግሥት ይልቅ እኛ እንደምንቀድም ዞር ብለን አስተውለን አናውቅም:: ብናስተውልም እኛ ትክክል እንደሆንን ብቻ ማሰብና ማመንን ባህላችን አድርገነዋል::
ሁሉም ሰው የመናገር ነጻነት መከበር አለበት ብሎ የሚያምነው እሱ ሲናገር ወይም እሱ ሊናገር የፈለገውን ሌላ ሰው ሲናገርለት ነው:: ከዚያ ውጭ የመናገር ነጻነት እሱ መስማት ለማይፈልገውም ሃሳብ እንደሚሰራ አይገነዘብም ወይም ሆን ብሎ ይክዳል:: ይሄ የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴያችን ያጋለጠው ሀቅ ነው::
ዲሞክራሲ በባህሪው ከስር እየተገነባ የሚሄድ እንጂ ከላይ የሚሰጥ አይደለም:: እኛ ግን ከቤታችን ያላሳደግነውን ዴሞክራሲ ነው ከመንግሥት ቢሮ የምንፈልገው:: ቤቱ እየተኮረኮመ ያደገ ሰው ቢሮ ሄዶ በነጻ ሃሳብ የሚያምን ይሆናል ማለት ዘበት ነው:: ህዝብ እርስ በርሱ አንዱ ሌላውን በሃሳብ እየሞገተ ሲያድግ ዴሞክራሲ ያብባል አልያም ግን አንዱ ሌላውን እየጠለፈ እና እያሸማቀቀ የሚቀጥል ከሆነ ዴሞክራሲ እንኳን ሊያብብ እንዲያውም ለአምባገነን መንግሥት መፈጠር በር ሊከፍት ይችላል::
እርግጥ እንደ ህዝብ ካሉብን ችግሮች መካከል እኛ ሊኖረን የሚገባውን ነገር በሙሉ ከመንግሥት መጠበቅ አንዱ ነው:: ለምሳሌ ያህል የትምህርት ጥራት እንዲሻሻል እንፈልጋለን:: ነገር ግን የልጃችንን ደብተር ለማየት፤ የቤት ስራ ለማሰራት ፤ ለማስጠናት ፍላጎት የለንም:: ትምህርት ጥራት ግን የብዙ ነገር ድምር ውጤት ነው:: ካላስጠናን፣ የቤት ስራ ካላሰራን ፣ አጋዥ መጽሐፍትን ካላቀረብን ፤ እንዳይርባቸው ካላደረግን ፣አእምሮአቸው ትምህርት ላይ ብቻ እንዲያተኩር ካላገዝን ፣ ውሏቸውን ካልተከታተልን ልጆች ትምህርት ቤት ውስጥ ብቻ በሚደረግ ስራ ውጤታማ ሊሆኑ አይችሉም:: ያን ሳናደርግ ግን ስለ ትምህርት ጥራት ብናወራ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ የሚለው ተረት በኛ ላይ ይፈጸማል::
ሁላችንም ፍትህ እንዲሰፍን እንፈልጋለን:: ፍርድ ቤት እኛ በምናውቃቸው ሰዎች ላይ የሚወሰነውን እያንዳንዱን ውሳኔ እንከታተላለን ፤ የፖሊስን ችግር እንነቅሳለን ፤ አቃቤ ህግ ብዙ ችግር እንዳለበት እንዘረዝራለን:: እኛ ያለ ጥፋታቸው ታስረዋል ለምንላቸው ሰዎች እንዲህ ስንሟገት ላየን ሰው ስለ ፍትህ ያለን ተቆርቋሪነት በጣም ከፍተኛ ሊመስለው ይችላል::
ነገር ግን በዚያው ልክ ባለስልጣን ዘመድ ካለን ተማምነን ኢ ፍትሀዊ ነገር ስናደርግ ቀዳሚዎቹ እኛ ነን:: ለፖሊስ እና ለአቃቤ ህግ ጉቦ ሰጥተን ክስ ስናዘጋም ማንም አይበልጠንም:: ሌላም ሌላም:: እኛ በግላችን ጉዳይ የማናደርገውን ነገር መንግሥት ግን ወንጀል ፈጽመዋል በሚላቸው ሰዎች ላይ እንዲፈጽም እንጠብቃለን::
የብዙዎቻችን ስድቦችም ተቀባይነት የላቸውም:: አንድን ሰው ለሰራው ስራ ቤተሰቡን አብሮ የመውቀስ አዲስ ባህል ሁሉ አምጥተናል:: ልጅን በአባቱ ጥፋት መውቀስ፤ ሚስትን በባሏ ጉዳይ መተቸት፤ እህትን በወንድሟ ጉዳይ ማንጓጠጥን ሃሳብን በነፃነት ከመግለፅ ጋር የምናያይዝ ጥቂት አይደለንም:: ይሄ ኢትዮጵያዊ ባህሪ አይደለም::
ይህ ሃሳብን በነፃነት በመግለፅ ሂሳብ እያዳበርነው ስለመጣነው አምባገነንነት ትልቅ ማሳያ ነው:: ይህ አዲስ ባህል አደገኛ ነው:: አምባገነን ህዝብ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት አይኖረውም:: በፌስቡክ ላይ የሌለውን ዴሞክራሲያው ውይይት በምክር ቤት ልናገኘው አንችልም:: ይህ የሚያመለክተን ነገር ቢኖር እኛ ራሳችን በነጻነት ሃሳብን የመግለጽ መብትን እያፈንን መንግሥት ግን እንዲያከብር እና እንዲያስከብር እንደምንፈልግ ነውና እያስተዋልን::
ስራዬ ብለው ዘርን ሃይማኖትንና ማነትን መሰረት አድርገው ለመሰዳደብና ለመበሻሸቅ ወደ ማህበራዊ ሚዲያው ብቅ የሚሉ ግለሰቦች እዚሁ ሀገር ውስጥ ቢኖሩም በርካቶቹ በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወይም ትውልደ ኢትዮጵያውያን ናቸው። እርግጥ ነው ማህበራዊ ሚዲያዎችና ተከታዮቻቸውን ተጠቅመው ሀገርና ወገንን የሚጠቅም ለስጋም ለነብስም እረፍት የሚሰጥ አስደማሚ የረድኤት ተግባራትን የሚሰሩ ብዙዎች አሉ።
ከእነሱ በተቃራኒ ስራዬ ብለው ለስድብ የተሰማሩ ግለሰቦች ቁጥር ግን ቀላል አይደለም። በእነዚህ ግለሰቦች ዘንድ የፖለቲካ፣ብሔር ምናምን ጉዳዮች የመሰዳደቢያ አጀንዳዎች መሆናቸው የተለመደ ነው። ይህ ደግሞ እኛ ጋር እንጂ በሌላው ዓለም ስለመኖሩ አጠራጣሪ ነው። ከተማ መኖርና የከተማ ሰው መሆን ይለያያል።
የሰለጠነ ዓለም መኖርና ስልጡን መሆንም እንደዛው። በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የማህበራዊ ሚዲያ ብሽሽቅ የምንታዘበው ነገር ግራ ያጋባል። በየትኛውም ጉዳይ ላይ መሰዳደብ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ተደርጎ እስከመቆጠር፣ እርስበርስ ከፍ ዝቅ ተደራርጎ መዘላለፍ እስከ ድብድብ እስካልደረሰ መብትና የስልጣኔ መገለጫ እየተደረገ ተለምዷል። ከሀገር ርቄያለሁ ብሎ እትብቱ የተቀበረበትን ሀገርም ይሁን ግለሰብ ከጥላቻም የዘለለ የፈለጉትን መናገር ነፃነትን እንደማጣጣም ተቆጥሯል።
ነፃ ንግግር ማለት የጥላቻ ንግግር ማለት እንዳልሆነ በሰለጠነ ዓለም እየኖሩ መዘንጋቱ ይበልጥ አስገራሚ ነው:: ነፃነት ሌሎችን መስደቢያ ወይም ማሸማቀቂያ ፍቃድ አይደለም:: ነፃነት ከባድ ኃላፊነት ነው:: ነፃነት ስድነት አይደለም:: ነፃነት ገደብ የሌለው እንዝላልነትም አይደለም:: ነፃነት ገደቡም ሆነ ኃላፊነቱ ሕሊናዊ ነው:: ነፃነትን ባግባቡ ለመጠቀም እውቀት ይፈልጋል፤ ስነምግባር ግድ ይላል::
በነፃነት ስም ሌሎችን የሚያጥላላና ማንነታቸው ላይ የስድብ ናዳ ማውረድ የነፃነትን እውነተኛ ትርጉም መሳት ነው:: ዘመኑ የዕውቀት ነውና የሃሳብ ልዩነትን በሃሳብ ፍልሚያ ብቻ መታገል የስልጣኔ ምልክት ነው:: እኔ ብቻ ነኝ ልክ፣ እኔ ብቻ አንደኛ፣ እኔ ብቻ ልጠቀም፣ ሌላው የራሱ ጉዳይ የሚል ራስወዳድ አስተሳሰብ ያልበሰለ ሃሳብ ነው::
ብዝሃ ሃሳብን ማክበርና የሌሎችን ማንነት መቀበል የዘመናዊነት ምልክት ነው:: አውሮፓውያን ከጨለማው ዘመን ወደ ሕዳሴው ዘመን የተሸጋገሩት ለብዝሐ ሃሳብ እውቅና በመስጠት ነው:: ከጥላቻ ምንም እንደማይገኝ በመረዳታቸው ነው አሁን ለደረሱበት ሥልጣኔ ብዝሃ ሃሳብን በነፃነት የሚያንሸራሽሩት:: በሃሳብ ተከራክረው፣ ተጨቃጭቀውና ተፋልመው ተቃቅፈውና ተጨባብጠው የሚለያዩት ሰውየው ላይ ሳይሆን ሃሳቡ ላይ በማተኮራቸው ነው::
‹‹ፍቅር የጥላቻ መድኃኒት ነች›› ይባላል:: ሌላውን የሚጠላ ራሱን አይወድም:: ራሱን የሚጠላ እንዴት ሌላውን ሊወድ ይችላል? ፍቅር በማድረጉ፣ ለሌሎች ቅን በማሰቡ፣ ደግ ሥራ በመስራቱ የሚደሰት እንጂ የሚፀፀት ማንም የለም:: ሌሎችን እንደራስ ማየት የሚያረካ እንጂ አያስቆጭም:: ሰው ጥሪው ለፍቅር እንጂ ለጥላቻ አይደለም:: የጥላቻ ንግግር ጠላትን ያበዛል፣ ሰላምን ይነሳል እንጂ ወዳጅን አያተርፍም፤ ፍቅርንም አያመጣም::
ነፃነት ነፃ አይደለም:: የዕውቀትን ዋጋ ያስከፍላል ዕውቀት መዳረሻ አይደለም:: ዕድሜ ልክ የሚደረግ ጉዞ ነው:: አዎ! ነፃነት እውቀት ይፈልጋል:: አለበለዚያ ነፃነት ራሱ ነፃ አይሆንም:: ነፃነት መዳረሻው ሰው መሆን ነው:: ሰው መሆን ደግሞ ከዘረኝነት፣ ከጥላቻ ንግግር አስወጥቶ ከሰብዓዊነት የሚያገናኝ መሠረት ነው:: ሰው ‹‹እውነተኛ ሰው›› ከሆነ ሌላውን እንደራሱ ያያል እንጂ በጥላቻ ንግግር ሰውነቱን አያበላሽም:: ሰው ክቡር ሆኖ ሳለ እንስሶችን መምሰል የለበትም::
ሃሳብ ላይ እንጂ ማንነት ላይ አናተኩር! ነፃነትን ለበጎ ነገር እናውለው:: የጥላቻ ንግግር ለሰዳቢውም ለተሰዳቢውም አይጠቅምም:: ቴክኖሎጂውን ለበጎ ነገር ከተጠቀምንበት ሃሳብን የሚያሳድግ፣ ሕሊናን የሚያበስል፣ ወደፊት የሚያራምድ መልካም ትምህርት ልናገኝበት እንችላለንና::
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም