ዓለም በርካታ የፖለቲካ ስሪትን ያለፈች፣ እያለፈች ያለችም፣ ወደፊትም የምታልፍ ነች:: አንድ የነበሩ ሀገራት ብዙ ሆነው፣ብዙ የነበሩ አንድ ሆነው አይተናል፣ ሰምተናል፣ እየሆነም ነው:: ኢትዮጵያም በእነዚህ ውስጥ በአንዱ ወይም በሌላው አልፋለች::
ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት ሀገር ብትሆንም የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ሳይኖራት ብዙ ክፍለ ዘመናትን ተሻግራለች:: ሁሉም በሚባል ደረጃ መንግሥታቷ ስልጣን የሚያስረክቡት በኃይል ሲሆን ይህም ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል::
ሀገራችን ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናት የቆየችበት ጤናማ ያልነበረው የፖለቲካ ሂደቷ በርካታ ውስብስብ ችግሮችን እንድታስተናግድም አድርጓታል:: በየጊዜው የሚመጡት መንግሥታትም ልዩነቶችን በውይይትና በድርድር ከመፍታት ይልቅ አፈሙዝን ቀዳሚ ምርጫቸው በማድረግ አመጾችን፣ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን እና የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎችን ሲያስተናግዱ መኖራቸው የሚታወስ ነው::
የመንግሥታቱ ያላዛለቀውና የማያዛልቀው ምርጫዎቻቸውም እንደሀገር መሠረታዊ ቅራኔዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆነዋል:: በእነዚህ ጥቅል የዘመናት ችግሮችም በየጊዜው የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ በርካታ ሀብት ንብረት ወድሟል:: በሕዝቦች መካከልም መቃቃርና መጠራጠር ተፈጥሮ እንደሀገር አሁን የደረስንበት የጎጥና የጥላቻ ፖለቲካ ላይ አርፈናል::
ይህም በመሆኑ የፖለቲካ ባሕላችንን ማዘመንና የተሄደበትን መንገድ መቀየር የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ ሆኗል:: ለኢትዮጵያ ፈተና የሆነባትን ችግር ከሥር መሠረቱ ማወቅና መረዳት መፍትሔም ማፈላለግ ተገቢ ነው:: አሁን ላይ በልዩነት መነፅር ውስጥ የምትዋልል ሀገር ለነገው ትውልድ አስቀምጠን ማለፍ ለታሪክ ተወቃሽነት ለህሊናም ፀፀት የሚዳርግ ነው::
ነገን ዛሬ እንስራ የሚል እሳቤና ፍልስፍና በዓለም ላይ በናኘበት በዚህ ዘመን እኛ ትላንት ላይ ቆመን መቆዘም ረብ የለውም:: ለዚህም ከፋፋይ ትርክቶችን እየዘጋን ወደ አሰባሳቢ ትርክቶች የሚወስዱ መንገዶችንና አሠራሮችን ብሎም የርዕዮተ ዓለም እሳቤዎችን ገቢራዊ ማድረግ ሀገርን መታደግ ነው::
ለዚህም ነው የዘመናት ጥርቅም ችግሮቻችንን ለመፍታት፣ ሰላም የሰፈነባትና ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ያስችላል በሚል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በርካታ ተግባራትን እየከወነ የሚገኘው:: ትልቅ ኃላፊነት የተጣለበት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሀገራችን ብሩህ ተስፋን ይዞ እንደመጣ በብዙዎች ታምኖበታል::
ምክንያቱም መመካከር ፀብን የሚያርቅ፣ ሕዝብን የሚያቀራርብ፣ መፍትሔ የሚያመነጭ መድረክ በመሆኑ ነው:: እንደ ሀገር በመሠረታዊ ቅራኔዎች ተወጥረን በምንገኝበት፣ አለመስማማቶች ሰፍተው በሚታዩበት፣ በተለይ ከፖለቲካ በሚመነጩ መሠረታዊ ቅራኔዎች በምንታመስበት በአሁኑ ወቅት ውይይት ተገቢው መንገድ ነው:: አሉ የሚባሉ ቅራኔዎችን ለመፍታትም ያልተሞከረውና እንደ ትልቅ ተስፋ የሚታየው ቁጭ ብሎ መመካከር ነው::
የሀገራዊ ምክክር አስፈላጊም ጠቃሚም ነው:: አለመግባባት የፈጠሩትን ጉዳዮች ወደ መድረክ አምጥቶ ሕዝቡ እንዲወያይበት ያደርጋል:: እንደ ሀገር በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አመለካከት ለማዳበርና ሀገሪቱን ወደ ሰላም እንድትመጣ፣ ወደ እድገት እንድትጓዝ ለማድረግ ታስቦ የተቋቋመ የምክክር መድረክ ነው:: አላማው የተቀደሰ ነው::
ሀገራዊ ምክክሩ ያስፈለገው በሀገራዊ ጥቅምና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች መኖራቸው ነው:: ሥራው ለኮሚሽኑ ብቻ የሚተው አይደለም:: የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምክክር ኮሚሽኑ እቅድ መሳካት መትጋትና ከልዩነቶች ይልቅ የሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የነገዋን ኢትዮጵያ አስበው መሥራት ይኖርባቸዋል::
ሂደቱ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍ ያለ ነው:: ፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገራዊ ምክክሩ ቢያንስ ያሉብንን መሠረታዊ ቅሬታዎች ለመፍታት የሚያመላክት መድረክ መሆኑን ማመንና ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል:: የምክክሩን ሂደት በንቃት የሚሳተፍ እና ሃሳብ የሚያቀርብ፣ መፍትሔዎችን የሚጠቁም አካል/ቡድን በመደበኛነት መድበው መንቀሳቀስ አለባቸው::
ፓርቲዎች የሚታገሉለት አላማ፣ የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ሊሳካ የሚችለው ሀገር ሲኖር ብቻ ነው:: ያለችን ሀገር አንድ እስከሆነች ድረስ ለሀገራችን ችግሮች መፍትሔ በሚያመነጭ ምክክር ላይ ከሁሉም በላቀ የፓርቲዎች አስተዋፅኦ የገዘፈ ነው:: ፓርቲዎች ሰላም ከሌለና አሁን በሚታዩ አዝማሚያዎች የሚቀጥሉ ከሆነ ወጥቶ መግባት ሰርቶ መብላት አለመኖሩን ከሌላው አካል በበለጠ ስለሚገነዘቡ ምክክሩ እንዲሳካ የየእለት ተግባራቸው መሆን አለበት::
የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር ኮሚሽኑ አላማ እንዲሳካ ርብርብ ማድረግ የውዴታ ግዴታቸው ነው:: ለምክክሩ ልዩ ትኩረትም ሊሰጡት ይገባል:: ጉዳዩን ሰፋ አድርገው በመመልከት ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል:: ሃሳቦችን አሰባስበው ወደ ኮሚሽኑ ማስተጋባት አለባቸው:: የምክክሩ ውጤት ወደ ተግባር እንዲለወጥና ሕዝቡ ሰላማዊ በሆነ መንፈስ ተወያይቶ፤ ልዩነቶችን በሰላም እየፈታ ሀገሩን እንዲያሳድግ የፓርቲዎቹ ሚና የላቀ ነው::
የምክክር ውጤቱ ውጤታማ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን በመተው የነገዋን ሀገር አስበው ከምክክር ኮሚሽኑ ጋር በጋራና በትብብር መሥራት ይጠበቅባቸዋል:: ብሔራዊ ምክክሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ በንቃት ሊሳተፍ ይገባል::
በተለይ ደግሞ ወጣቱ ትውልድ አደባባይ የሞሉ ትርክቶችን ከራሱ፣ ከማህበረሰቡ፣ ከሀገር ተጠቃሚነት አንፃር በሰከነ መንፈስ ሊመረምራቸው ይገባል:: ለምን ብሎ የሚጠይቅና ሁኔታዎችን በጥልቀት የሚመለከት መሆን አለበት::
አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል የሚሸፍነው ወጣቱ ትውልድ ለብሔራዊ መግባባት መሠረት የሚጥሉና የነጠሩ ሃሳቦችን በማፍለቅ፣ በመተንተን፣ በማስገንዘብና ለሀገራዊ አንድነት አብዛኛውን ዜጋ ሊያስማሙ፣ ሊያቀራርቡ የሚችሉ አማራጮችን ማቅረብ መገለጫው ሊሆን ይገባል::
ወጣቱ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ዜጎች ሀገራችን እየተፈታተናት ከሚገኘው አደገኛ ትርክት ወጥታ ወደ አሰባሳቢ ትርክት ልትመጣ የምትችልበትን መላ ማዋጣት፣ ለገቢራዊነቱም መሥራት ይጠበቅብናል::
ኢትዮጵያ በታሪክ ቅብብሎሽ የብዙ አኩሪ ታሪክ ባለቤት ብትሆንም በዘመናት ቆይታ ውስጥ ግን በፖለቲካው እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳዮች በተፈጠሩ ነጣጣይ ትርክቶች ዛሬ ላይ የግጭት መነሻ ምክንያት እየሆኑ መጥተዋል:: ይህን አሳሳቢ ችግር ለመቅረፍም አሰባሳቢ ትርክቶች ወይም የጋራ ተግባቦት የሚፈጥሩ ትርክቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል::
ብዙዎች እንደሚሉት ሀገራችን ላይ የሚታዩ የትርክት ዓይነቶች ሁለት ዓይነት ይዘት አሏቸው:: አንደኛው አቅላይ ትርክት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የወል ወይም ገዢ /አሰባሳቢ ትርክት ነው:: የመጀመሪያው የትርክት ዓይነት ነጠላ ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ ራስን ብቻ የሚመለከት ‹እኔ ብቻ› የሚል ስሜትን የያዘ ነው:: ሁለተኛው የትርክት ዓይነት ደግሞ ብዝሀነትንና አካታችነትን የሚይዝ ነው::
በርግጥ ኢትዮጵያ ብዝሀነትንና አካታችነትን የሚያንፀባርቁ በርካታ አሰባሳቢ ትርክቶች አሏት:: እነዚህን ትርክቶች እንዴት እንጠቀምባቸው? እንዴት ሊያሻግሩን ይችላሉ? በሚሉ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ውይይትና ምክክር ማድረግ ያስፈልጋል:: በተቃራኒው ታሪክን ማዛባት ልማድ የሆነበትን አላስፈላጊ ፖለቲካ ማፅዳት ተገቢ ነው:: በእውነትና በልክ ማስቀመጥ ግዴታ ነው:: ትርክቶችን በአግባቡ ማስተናገድ እንደሚገባ ሁሉ ከጀርባቸው የያዙትን መልእክትና ዓላማም አብጠርጥሮ ማወቅ ግድ ይላል::
አሁን አሁን ከግለሰብ ወይም ከቡድን የሚመነጩ ነጣጣይ ትርክቶች ሀገር ላይ ተፅእኖ እያሳደሩ ይገኛሉ:: ግጭቶች ይከሰታሉ:: እነዚህ ግጭቶች በአብዛኛው መነሻቸው የግለሰቦች፣ የቡድኖች ፍላጎት ሊሆን ይችላል:: ከተወሰኑ ቡድኖች አካባቢ ሊነሱ ይችላሉ:: የራሳቸውን ጥቅም፣ የራሳቸውን ፍላጎት፣ ራሳቸው ሊያሳኩ የፈለጉትን ግብ በትርክት መልክ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ::
እነዚህ ትርክቶች የሌሎች ወገኖችን ፍላጎት የሚነኩ ይሆኑና በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ወደ ግጭት ያመራሉ:: ግጭቶች እያደጉ ሲሄዱ ደግሞ ተፅዕኗቸው ወደ ሀገር ይመጣል:: ሀገርን ወደ መበጥበጥ፣ ሀገርን ወደ መበተን፣ በጋራ አለመቆምን፣ በጋራ አለመሥራትንና አለመሰባሰብን ያስከትላል::
እንዲህ ሲሆን አንድ መሆናችን፣ በጋራ መቆማችን የሚያንገበግባቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች ደግሞ ዓለም የደረሰችበት የእድገት ደረጃ ያመጣው የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም ሀገርን በሚያፈርስ መልኩ ጨምረውበት ያስተጋቡታል:: ይህም አሰባሳቢ ትርክት ለመፍጠር አንዱ ጋሬጣ ነው::
በማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚወጡ መረጃዎች እንዲሁም በአንዳንድ መደበኛ መገናኛ ብዙሃን የሚለቀቁ መረጃዎች አሰባሳቢ ትርክትን ለመፍጠር ተግዳሮት እየሆኑ መጥተዋል:: ማህበራዊ ሚዲያዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ /ኢንፎርማል የሚቋቋሙ፣ ተቋማዊ ይዘት የሌላቸው በመሆናቸው እነሱ በሚፈጥሯቸው የተዛቡ መረጃዎች ምክንያት ማህበረሰቡ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚሄድበት አጋጣሚ ሰፊ ነው::
በሌላ በኩል ደግሞ መደበኛ መገናኛ ብዙሃኑ መደበኛ የሆነ አካሄድን ጠብቆ ተቋማዊ አሠራርን ተከትሎ የሚሄድ ነው:: የራሱ የሆነ ሥርዓትና ደንብ አለው:: መረጃ ለህብረተሰብ ሊሰጥ ሲፈለግ አሁን ያለው የማህበረሰብ ክፍል ትኩስና የሚያጋግል መረጃዎችን፣ ስሜት ኮርኳሪ ጉዳዮችን ይፈልጋል:: ይህንን እንዳያደርግ ኃላፊነትና ተጠያቂነት አለበት:: ሕግን አክብሮ በመንቀሳቀሱም በማህበራዊ ሚዲያ የመበለጥ ተግዳሮት ገጥሞታል::
ይህም መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል:: በመሆኑም ለግጭት መንስኤ የሆኑ ትርክቶችን በሚያመነጩና በሚያሰራጩ አካላት ላይ ተጠያቂ የሚያደርግ ሥርዓት ሊበጅ ይገባል:: አንዳችን በአንዳችን ላይ ጦር የሚያማዝዙ አማዘውም ያየናቸው በርካታ ትርክቶችን ይዘው አደባባይ ሲወጡ እየተመለከትን ነው:: ይሄንን የሚቆጣጠር አካል የለም ወይ ያስብላል:: ጥላቻን ለሚሰብክ ሀሰትን ለሚነዛው ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ ያስፈልጋል::
ነጣይ ትርክቶችን በመቅረፍ የጋራ እና አንድ ወደሚያደርጉ ትርክቶች ለመምጣት የተለያዩ ውይይቶች ያስፈልጋሉ:: ለዚህም ብሔራዊ ምክክሩ ወሳኝና አስፈላጊ ነው:: የሕዝብ ውይይቶች ወደ ጋራ አንድነት ያመጣሉ:: ተነጋግሮ ተደማምጦ ችግሮችን ፈትቶ ለመሰባሰብ አንድ ለመሆን ይበጃሉ::
አሰባሳቢ ትርክቶችን ከታች ጀምሮ በኢትዮጵያ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተትና እንዲጎለብቱ በማድረግ ትውልድ የሚማርበትን አካሄድ መዘርጋት ያስፈልጋል:: በሁሉም በሚቀርቡ የትምህርት ዓይነቶች አሰባሳቢ ትርክቶችን በማስገባት ቢሰራባቸው ጥሩ ዜጋ ማፍራት ይቻላል::
የጋራ ገዢ ትርክቶች በጋራ ለመፍጠር የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍ ያለ ቢሆንም መገናኛ ብዙሃን፣ የሚታተሙ የሕትመት ሥራዎች እንዲሁም የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሀገራዊ ኃላፊነት ትልቅ ነው::
በአጠቃላይ ነባር ሀገራዊ ችግሮቻችንን በሀገራዊ ምክክር እና በሽግግር ፍትህ ማረም ይገባናል:: የገጠሙን የግጭትና የጦርነት ፈተናዎችን ለመሻገር ደግሞ ሰላማዊ የፖለቲካ አካሄዶችን ተመራጭ ማድረግ አለብን:: በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ የእርስ በእርስ ግጭቶች እና ጦርነቶች ተከስተው እንደ ሀገር ከባድ ኪሳራ ደርሶብናል:: የዚህም ምክንያት ግጭቶችን በውይይትና በስምምነት የመፍታት የፖለቲካ ልምምድ ስለሌለን ነው::
በመሆኑም ፖለቲካችንን ከግንባር ወደ ጠረጴዛ፣ ከጫካ ወደ አዳራሽ እንዲመለስ ማድረግ የሁላችንም የዜግነት ግዴታችን ነው:: ከበዳይ ተበዳይ አዙሪት ልንወጣ ያስፈልጋል። በምሕረት፣ በይቅርታ፣ በካሣና፣ በፍትሕ ታክመን ወደፊት መጓዝ መቻል አለብን። ለዚህ ስኬትም ኢትዮጵያውያን ሁሉ በንቃትና በብቃት ልንሳተፍ ይገባናል። መንግሥትም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አተገባበርን ከሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ጋር የተናበበ እና የሚመጋገብ እንዲሆን በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት!
ታሪኩ ዘለቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም