ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራት ስብራትንለመጠገን የሚያስችል አሠራር ቀርጾ ወደ ሥራ ገብቷል

አዲስ አበባ፡- በትምህርት ጥራት ላይ የሚስተዋለውን ስብራት ለመቅረፍ የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ብርሀነመስቀል ጠና (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በትምህርት ጥራት ላይ የሚስተዋለውን ስብራት ለመቅረፍ ፍኖተ ካርታና የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል።

ኢትዮጵያ ላለፉት 100 ዓመታት አንድም የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሳይኖራት ትምህርትን ስትመራ የኖረች ሀገር ናት ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ እንደሚያስፈልግ አመላክቷል። በዚህም ለውጡን ተከትሎ እንደገና ከተደራጁ ተቋማት አንዱ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ነው ብለዋል።

በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ከ800 ሺህ በላይ መምህራን አሉ ያሉት ዶክተር ብርሀነመስቀል፤ በዩኒቨርሲቲ ውስጥም 40 ሺህ የሚደርሱ መምህራን ይገኛሉ። ይህን ሁሉ መምህር ይዘን ስለትምህርት ውድቀት ማውራት በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው ሲሉም ተናግረዋል። ስለሆነም ዩኒቨርሲቲው ትውልድ የሚገነቡ መምህራንን ለማፍራት በትኩረት እየሠራ ነው።

ዩኒቨርሲቲው በዳይሬክተር የሚመሩ አምስት ማእከላትን መክፈቱን ጠቅሰው፤ ከእነዚህ ማዕከላት አንዱ በማስተማር ሙያ ላይ ለተሰማሩ ዜጎች የሥራ ላይ ስልጠና የሚሰጥ ነው። ይህም መምህር ሳይሆኑ የሚያስተምሩትን መምህር ማድረግን ያለመ ነው።

በተለይ በግል የትምህርት ተቋማት ከሚያስተምሩ መምህራን አብዛኞቹ የመምህርነት ስልጠና ያልወሰዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህ ደግሞ በሕፃናት የነገ ሕይወትና በሀገርም ላይ ትልቅ አደጋ የሚያስከትል ነው። በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍ የሥራ ላይ ሥልጠና መስጠት የሚያስችል ማዕከል ከፍተናል ብለዋል።

መምህርነት አማራጭ ሲታጣ የሚገባባት ሳይሆን፤ መከበር አለበት ትልቅ ሙያ ነው ያሉት ፐሬዚዳንቱ፤ በየትኛውም የትምህርት መስክ የሰለጠነ ሰው ድንገት ተነስቶ መምህር መሆን የለበትም። ከሰለጠነበት ሙያ ባለፈ የማስተማር ፍላጎት ካለውም ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ እንዴት ማስተማር እንዳለበት መሰልጠን አለበት ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ የሚቀበለው ከ600 እስከ 700 የሚደርሱ ተማሪዎችን እንደሆነ ያስታወቁት ፕሬዚዳንቱ፤ ተማሪዎችን ትምህርት ሚኒስቴር ይመድብለታል፤ ዩኒቨርሲቲውም ማስታወቂያ አውጥቶ በመምህርነት ሙያ ለመሰልጠን ፍላጎት ያላቸውን ተማሪዎች ይቀበላል ሲሉም አስረድተዋል።

ከዚህ በላይ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ለመቀበል የዶርሚተሪ/ማደሪያ ስፍራ/ እጥረት እንቅፋት እንደሆነበት አንስተው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 17 ሺህ ሄክታር ቦታ ማበርከቱንም ጠቁመዋል። ዛሬ ካልተዘራ ነገ ስለማይታጨድ አይሲቲን ጨምሮ የሌሎችም መሠረተ ልማቶችን ችግር ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ትኩረትና እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ትምህርት መሠረታዊ ችግር የሚስተዋለውን ስብራት በጥናት ላይ ተመስርቶ ከመፍታት ይልቅ በጨበጣ ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶች ናቸው ያሉት ዶክተር ብርሀነመስቀል፤ የሚደረጉ ጥናቶችም በለጋሽ ድርጅቶች ላይ የተንጠለጠሉ በመሆናቸው የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገቡ አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ በሌላ ሀገር የተደረጉ ጥናቶች የስም ለውጥ ብቻ ተደርጎባቸው ለኢትዮጵያ እንደተሠሩ ተደርገው የሚቀርቡበት ሁኔታም አጋጥሟል ብለዋል።

መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል እውቀቶችን መሠረት ያደረገና በእኛ ሙያተኞች የተሠራ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን ጠቁመው፤ ሀገራዊ ችግርን መሠረት ያደረገና ሀገራዊ ራዕይ የሰነቀ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድም መዘጋጀቱን አብራርተዋል።

ብቁ መምህራንን ለማፍራት ከሚያከናውነው ሥራ ጎን ለጎን ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናትና ምርምሮችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ በድሀ ሕዝብ ገንዘብ የሚሠሩ ጥናቶች ደግሞ መሬት ወርዶ ችግር የሚፈታ እንዲሆን ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በዚህ ዓመትም ከሚያከናውናቸው በርካታ ጥናትና ምርምሮች መካከል የኢትዮጵያን ትምህርት ችግር ማዕከል ያደረጉ አራት ትልልቅ ጉዳዮች ላይ ጥናት እያደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህም በርካታ እንከኖችን ለመቅረፍ ትልቅ ሚና ይጫወታል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራት በተወሰኑ አካላት ጥረት ብቻ ሊረጋገጥ አይችልም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የሀገሪቱን የትምህርት ስብራት ለመጠገን ሁሉም ባለድርሻዎች የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም

Recommended For You