ትምህርት የዕድገት መሰረት ነው:: ለትምህርት ትኩረት የሰጡ ሀገራት በእድገት ማማ ላይ በመራመድ የዜጎቻቸውን ህይወት መቀየር ሲችሉ በአንጻሩ የትምህርት ሥርዓታቸው ደካማ የሆኑ ሀገራት የድህነትና ኋላቀርነት መገለጫ ለመሆን በቅተዋል:: ድህነት፣ ግጭት፣ ጦርነት፣ስደት፣ረሃብና የመሳሰሉት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከትምህርት ውድቀት ጋር የሚያያዙ የኋላቀርነት መገለጫዎች ናቸው::
ትምህርት በኢትዮጵያ ከአንድ ክፍለ-ዘመን በላይ የዘለለ ታሪክ ቢኖረውም በየዘመናቱ በቂ ትኩረት ባለማግኘቱ ወይም ደግሞ የየሥርዓቱ የፖለቲካ መሳሪያ ሆኖ በመዝለቁ ለሀገር ዕድገት ተገቢውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ተስኖት ቆይቷል:: በተለይም የትምህርት ሥርዓቱ ከፖለቲካ ጥገኝነት የተላቀቀ አለመሆኑ የትምህርት ዘርፉ ሙያዊ ግዴታውን እንዳይወጣ አድርጎታል::
በተለይም በዘመነ ኢህአዴግ ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ዩኒቨርሲቲዎችን እንደ አሸን በየቦታው የማቋቋሙ ተግባር የትምህርት ሥርዓቱንም ሀገሪቱንም በርካታ ዋጋ አስከፍሏቸዋል:: በዘመኑ የነበረው የትምህርት ፖሊሲ ከጥራት ይልቅ ለብዛት ትኩረት ይሰጥ ስለነበረ ተማሪዎች በቂ ዕውቀት ሳይጨብጡ ጭምር ወደ ቀጣይ ክፍል እንዲያልፉ ሲደረግ ቆይቷል::
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ደረጃውን የማይመጥኑ ተማሪዎችና ሰልጣኞችም ከመብዛታቸውም ባሻገር ትምህርታቸውን አጠናቀው ሲወጡ በገበያ የማይፈለጉና በሰለጠኑበት የሙያ መስክ የራሳቸውን ሥራ እንኳን መፍጠር የማይችሉ ዜጎች እንዲበራከቱ አድርጓል:: በዚህ ሂደት ውስጥ አልፈው የሚቀጠሩ ምሩቃንም ብዙውን ጊዜ ባላቸው ብቃት የማይተማመኑ እንዲሁም የዕውቀት እና ክህሎት ችግር የሚታይባቸው ይሆናሉ:: ለመልካም አስተዳደርና ለብልሹ አሰራርም ምክንያት ሆነው ይገኛሉ::
ይህንኑ ችግር ከስር ከመሰረቱ ለመቀየር ከለውጡ ወዲህ አዲስ ፍኖተ ካርታ ተቀርጾና በሂደትም አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተነድፎ ወደ ሥራ ተገብቷል:: ከእነዚህ ለውጦች መካከል ደግሞ በፖለቲካ ተሸብበው የነበሩትን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነጻ ማውጣት እና አስተዳደራዊ ነጻነታቸውን ማወጅ አንዱ ነው::
የትምህርት ሥርዓቱ ይዞ ከመጣቸው ትሩፋቶች መካከል የዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝነት መብት ነው:: አንድ ተቋም ተቋማዊ ነጻነት ተጎናጽፏል ወይም ራስ ገዝ ሆኗል ብለን ስናስብ በዋናነት ከአካዳሚና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ነጻነት ኖሯቸው ይህንንም ከተጠያቂነት ጋር በመያዝ የተሻለና ውጤታማ ሥራን እንዲሠሩ የማስቻል ጅምር ነውⵆ
ይህ መሆኑ ደግሞ የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአጭር ጊዜ ውስጥ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ያስችላል:: ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኳቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ፣ ተወዳዳሪና ብቁ ችሎታ ያላቸው ምሩቃንን ለማፍራትና ጥራት ያለው የምርምር ውጤት እንዲሠሩ ያስችላቸዋል::
ዩኒቨርሲቲዎች ችግር የሚያባብሱ ሳይሆን በሰላም መኖርን፣ ዴሞክራሲን፣ የሚሰብኩ ተቋማት እንዲሆኑ በተለይ ሀገር በቀል እውቀቶችን በምርምር ማወቅ፣ ለችግሮች የመፍትሔ ሃሳብ ማመንጨት፣ የዓለምንና የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ቀጣይ አቅጣጫን ለማመላከትም ነጻነትና ራስ ገዝነት ያስፈልጋቸዋል::
ትምህርት ሚኒስቴር በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አስር የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ እቅድ ይዟል። በዚህ ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱት መካከልም ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ እና መቐለ ዩኒቨርሲቲዎች ይገኙበታል።
ከተቋቋመ ሰባ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ የ“ራስ ገዝ” አስተዳደርን ተግባራዊ በማድረግ የመጀመሪያው ሆኗል:: በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው ከወዲሁ እያሳየ ያለው ለውጥ የሚያበረታታ ነው:: በተለይም ዩኒቨርሲቲው ለዘመናት ቅሬታ ሲቀርብበት የነበረውን የሬጅስትራር አሠራሩን ማዘመኑ የነጻነቱ ውጤት ተደርጎ የሚወሰድ ነው::
የዩኒቨርሲቲው የሬጅስትራር አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ወደ ኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት ተሸጋግሯል:: ቀድሞ እንግልት ይታይበት የነበረው የክፍያና የምዝገባ ሙሉ ለሙሉ ከወረቀት ተላቆ በዲጂታል ሥርዓት ውስጥ ገብቷል::
በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው የራስ ገዝ አስተዳደሩ በፈጠረለት ምቹ ሁኔታ የአሠራር ሥርዓቱን እያሻሻለ ከመምጣቱም ባሻገር ሌሎች ራስ ገዝ ለመሆን በሂደት ላይ ለሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችም አርአያ የሚሆን ተግባር እየፈጸመ በመሆኑ ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም