ስልጠናው የደንብ ማስከበር አባላት የአገልጋይነት ስሜት እንዲላበሱ የሚያስችል ነው

ሠንዳፋ፡- ለደንብ ማስከበር አባላት እየተሰጠ ያለው ስልጠና የአገልጋይነት ስሜት እንዲላበሱና ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲፈጽሙ የሚያስችል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታወቀ።

በመዲናዋ የሚታየውን ሕገ-ወጥነት ለመቆጣጠር የሚረዳ የአቅም ግንባታ ስልጠና በትናትናው ዕለት በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ መስጠት ተጀምሯል።

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ስልጠናው የደንብ ማስከበር አባላት በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን ደንብ መተላለፍ ቁጥጥር ሥራ የአገልጋይነት ስሜት ተላብሰው ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲፈጽሙ የሚያስችል ነው።

የደንብ ማስከበር አባላት ሀገራቸውን መውደድ ይኖርባቸዋል ያሉት ሻለቃ ዘሪሁን፤ ሰልጣኞች በሚኖራቸው የስልጠና ቆይታ ስለ ሀገር ወዳድነት ምንነት ያላቸውን ግንዛቤ የሚያጎለብቱበት እንዲሁም በቂ ትምህርት የሚያገኙበት ነው ብለዋል።

ሥራቸውን በሚከውኑበት ወቅት በተለይ ሥነ-ምግባር ጋር በተገናኘ የአገልጋይነት ስሜት እንዲላበሱና በከተማ ውስጥ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የደንብ መተላለፎችን እንዴት መከላከል እንደሚችሉ እውቀት የሚቀስሙበት መሆኑን ገልጸዋል።

በአቅም ግንባታ ስልጠናው አምስት ሺህ ነባር ኦፊሰሮች የሚሳተፉ ሲሆን፤ በአምስት ዙር ከአንድ ወር በላይ ጊዜ እንደሚቆይ ሻለቃ ዘሪሁን ጠቁመዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከተማዋን ለነዋሪው ምቹና ጽዱ ለማድረግ ከኮሪደር ልማት በተጨማሪ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ አውስተው፤ ባለስልጣኑም የልማት ሥራዎቹ በተያዘላቸው እንዲጠናቀቁ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ብለዋል።

አባላቶቹ ለረጅም ጊዜ ሳይሰለጥኑ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ባለስልጣኑ በተሻለ መንገድ ሕዝብን ለማገልገልና ውጤታማ እንዲሆን ስልጠና መስጠቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አጫጭርና ረጅም ስልጠናዎችን የሚሠጥ ስመ ገናና ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ገልጸው፤ ሰልጣኞች በተለይ በከተማዋ በሚገኙ አደባባዮችና መንገዶች ላይ የሚደረጉ ሕገ ወጥ ንግዶች፣ ሕገ ውጥ የቤት ግንባታና መሬት ወረራ ላይ ውጤታማ የቁጥጥር ሥራ መሥራት የሚችሉ ብቁ ኃይል ሆነው እንደሚወጡ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮምሽነር ጀነራል መስፍን አበበ በበኩላቸው፤ ሰልጣኞች በዩኒቨርሲቲው የሚወስዱት ስልጠና የፖሊስ ተልዕኮን ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

ሰልጣኞች በሚኖራቸው አጭር የስልጠና ጊዜ ለሚሰሯቸው ተግባራት ወሳኝ እውቀት እንዲያገኙ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የደንብ ማስከበር አባላት የተሻለ የአካልና የአእምሮ ቁመና እንዲኖራቸው የሚያግዝ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው በምሥራቅ አፍሪካ ብቸኛ የፖሊስ ማሰልጠኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ከምስረታው ጀምሮ በርካታ መደበኛ የፖሊስ አባላትን ማፍራት ችሏል ብለዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም

Recommended For You