በፀጥታ ችግሮች ሳቢያ የደም አሰባሰብ በከተሞች ተወስኗል

አዲስ አበባ፡- በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ የፀጥታ ችግሮች ሳቢያ የደም አሰባሰብ ሂደት በከተማ መወሰኑን የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ። የአቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ ከተቋማት ጋር እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎትና ቀይ መስቀል ማህበር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ትናንት ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ደምና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ ባሉት የፀጥታ ችግሮች ሳቢያ የደም አሰባሰብ ሂደት በከተማ ተወስኗል።

በሀገሪቱ ያሉ የፀጥታ ችግሮች የደም አቅርቦት ማነስን ማስከተሉን ጠቁመው፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት ስምንት ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ የደም ማሰባሰብ ንቅናቄ እንደሚካሄድና በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የቀይ መስቀል ማህበርና በ48 የደም ባንክ ቅርጫፎች ላይ ደም እንደሚሰበሰብ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደም አገልግሎትን ለዘመናት ሲሰጥ ቆይቷል ያሉት ዶክተር አሸናፊ፤ የጋራ መግባቢያ ሰነዱ ሁለቱ ሰብአዊ ተቋማት በሕይወት አድን ሥራ በመቀራረብ ለመሥራት የሚያስችላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ምክትል ፀሐፊ አቶ አበራ ሉሌሳ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ንቅናቄ በመፍጠር የሚፈለገውን የደም መጠን ለማሰባሰብ የሚያስችል ነው።

ማህበሩ ላለፉት 89 ዓመታት በርካታ ሰብዓዊ አገልግሎቶችን ሲሰጥ መቆየቱን የገለጹት አቶ አበራ፤ በተለይም የደም ባንክ አገልግሎትን ለ42 ዓመታት ሲመራ ቆይቷል ብለዋል።

የደም አቅርቦት ሕይወት የማዳን ሥራ በመሆኑ ከማህበሩ ዓላማ ጋር በቀጥታ ግንኙነት እንዳለው ጠቅሰው፤ ማህበሩ በሰው ሰራሽ፣ ተፈጥሮ አደጋዎችና በጸጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል።

የቀይ መስቀል ማህበር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ200 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች እንዳሉት ገልጸው፤ የደም ማሰባሰብ ሂደት ሕይወት የማዳን ተግባር በመሆኑ በሁሉም ቅርንጫፎች ተግባራዊ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማህበር በዓልን ምክንያት በማድረግ ከነገ ጀምሮ እስከ ግንቦት ስምንት “ደስታን እለግሳለሁ ደስታውም ሽልማቴ ነው”በሚል መሪ ሃሳብ ደም የማሰባሰብ ሥነ ሥርዓት እንደሚካሄድም ተገልጿል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም

Recommended For You