ከ815 ቶን በላይ የሻይ ቅጠል ምርት ወደውጭ ተልኳል

  • የ200 ሚሊዮን ዶላር የቡና ግብይት ኮንትራት ተፈርሟል

አዲስ አበባ፡- በዘንድሮ በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 815 ነጥብ ስድስት ቶን የሻይ ቅጠል ምርት ለውጭ ገበያ መቅረቡን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ። በየካቲት ወር በተደረገው የቡና ኤግዚቢሽን የውጭ ሀገር ገዢዎች የኢትዮጵያን ቡና ለመውሰድ የ200 ሚሊዮን ዶላር የግብይት ኮንትራት መፈራረማቸውን ባለስልጣኑ ገልጿል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2016 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት 815 ነጥብ ስድስት ቶን በአግባቡ የተዘጋጀ የሻይ ቅጠል ምርት ለውጭ ገበያ በመላክ አንድ ነጥብ 67 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል።

የተላከው የሻይ ምርት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ204 ቶን ብልጫ እንዳለው አስታውሰው፤ በሻይ ምርት ላይ የተሰማሩት ባለሀብቶች ውስን በመሆናቸው አሁን ላይ በዋናነት ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ እና ጉመሮ ሻይ ቅጠል ምርቱን እያቀረቡ ይገኛሉ ሲሉ አስረድተዋል።

በጋምቤላ ክልል የሚገኘው የሻይ ኢንዱስትሪ እስካሁን ወደተግባር አለመግባቱንና ምርቱ በስፋት ለማምረት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሻይ ቅጠል ልማት ላይ ክልሎች በስፋት እንዲሰሩ ኮሚቴ ተዋቅሮ የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጠው እየተሰራ ይገኛል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ ኢሉባቡር እና ቡኖ በደሌ ላይ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አርሶ አደሮች የሻይ ቅጠል ምርት በስፋት እንዲያመርቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

በተያያዘ በዘንድሮ ዓመት በየካቲት ወር በተደረገው የቡና ኤግዚቢሽን አንድ ሺህ የውጭ ሀገር የቡና ገዢዎች መሳተፋቸውን አስታውቀው፤ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ እና ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ቡና ገዢዎች በኤግዚቢሽኑ ተገኝተው ከኢትዮጵያ ቡና አቅራቢዎች ጋር ግብይት መፈጸማቸውን አስታውቀዋል።

በወቅቱ የኢትዮጵያን ቡና ለመግዛት የሚያስችል የ200 ሚሊዮን ዶላር የቡና ምርት ግብይት ኮንትራት ስምምነት መፈጸሙን አቶ ሻፊ አስረድቷል።

የቡና ኤግዚቢሽኑ የሀገሪቱን የቡና አመራረት ሂደት፤ ባህልና ሌሎች በቡና ዘርፍ የሚገኙ እሴቶችን ለማስተዋወቅ መዘጋጀቱን ያስታወሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ የውጭ ሀገር የቡና ገዢዎቹ ከአቅራቢዎቹ ጋር በቅንጅት እስከ ቡና ማሳ ድረስ ሄደው እንዲጎበኙ መደረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይ ኢትዮጵያ በልዩነት የምትታወቅባቸውን የቡና ምርት ዝርያዎች በማስፋት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You