ነጻ የንግድ ቀጣናው ተጠቃሚዎች ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ያስችላል

አዲስ አበባ፡- የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ተጠቃሚው ማኅበረሰብ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችላል ሲል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

“የኩባንያዎች ዝግጁነት ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተዘጋጀ የፓናል ውይይት ትናንት ተካሂዷል፡፡

በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዓለም አቀፍና ቀጣናዊ ንግድ ትስስር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታገሰ ሙሉጌታ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ነጻ የንግድ ቀጣናው የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ከመሳብ ባሻገር ተጠቃሚው ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያግዛል፡፡

ነጻ የንግድ ቀጣናው በነጋዴዎች መካከል ፍትሐዊ ውድድርን በማጠናከር በተመጣጣኝ ዋጋ ጥራት ያለው ምርት እንዲቀርብ ተጨማሪ አቅም ይሆናል ያሉት አቶ ታገሰ፤ ኅብረተሰቡም በነጻ የንግድ ቀጣናው ትግበራ ተጠቃሚ ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንዳመላከቱት፤ ነጻ የንግድ ቀጣናው ስምምነት በሁለት ምዕራፍ የሚደረግ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ የነበሩ የስምምነቱ ክፍሎች ተጠናቀዋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የምርት ስሪት ሀገር ምንጭን ተመርኩዞ መከናወን ያለባቸው ስምምነቶች በቀጣይ መጠናቀቅ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ 92 በመቶ የሚሆኑ ምርቶች የምርት ስሪት ሀገሮች የተበየነላቸው ሲሆን፤ በጨርቃጨርቅ እና በአውቶሞቲቭ ዘርፎች ላይ እንደአህጉር ከስምምነት ለመድረስ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በሁለቱ ዘርፎች አሠራር ዘርግቶ ከመሥራት አኳያ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ የገለጹት አቶ ታገሰ፤ ኢትዮጵያ በሁለቱም ምዕራፍ በሚደረጉ ስምምነቶች በንቃት እየተሳተፈች መሆኑን አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የታሪፍ አመዳደብና ስሪት ሀገራት አወሳሰን ዳይሬክተር አቶ ካሳዬ አየለ በበኩላቸው እንደገለጹት ፤ ኢትዮጵያ በዋነኛነት ለአህጉሩ ሀገራት የምታቀርባቸው ዕቃዎች የታሪፍ ምጣኔን በተመለከተ ዝርዝር ሰነድ ለአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ጽህፈት ቤት ጸድቋል፡፡

የጸደቀውን የታሪፍ ዝርዝር ደንብ በጋዜጣ የማሳተም ኃላፊነት የገንዘብ ሚኒስቴር በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የታሪፍ ዝርዝሩ በገንዘብ ሚኒስቴር ይገኛል ያሉት አቶ ካሳዬ፤ ሥራው ሲጠናቀቅ በጉምሩክ ሲስተም ላይ ይጫናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አንድ ሀገር በነጻ የንግድ ቀጣናው ምርቱን አቅርቦ ለመነገድ በቅድሚያ ምርቱ የእራሱ ሀገር ስሪት ሊሆን ይገባል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ምርቱ ሲላክ የላኪው ሀገር ስሪት መሆኑን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ካልተላከ የታሪፍ ቅነሳ አይደረግም ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ጉምሩክ ኮምሽኑ የስሪት መረጃ ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ በኩል የሚቀርቡ ምርቶች ላይ ስሪት ሀገር ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለማሳተም እንዲሁም ከሌሎች ሀገራት የሚመጡ ምርቶችንም በዝርዝር ለመለየት የሚያስችል ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You