ኢትዮጵያ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ጀግኖችን ያፈራች ሀገር ናት:: ወራሪ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመዳፈር በመዳፋቸው ስር ሊያስገቧት አስበው ብዙ ሞክረዋል:: መሰል ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ካደረጉት ወራሪዎች መካከል አውሮፓዊቷ ኢጣሊያ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች:: የፍራንቼስኮ ክሪስፒዋ ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን የሽንፈት ካባ በድል ለማካካስ በማሰብ በፋሺስቱ ቤኒቶ ሙሶሊኒ እየተመራች በ1928 ዓ.ም አሰቃቂ ወረራ በመፈፀም ለአምስት ዓመታት ያህል ኢትዮጵያን ቅን ተገዢዋ ለማድረግ ጥረት አድርጋም ነበር::
ይሁን እንጂ መቼውንም ቢሆን በሀገሩና በነፃነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሺስትን አገዛዝ ‹‹አሜን›› ብሎ አልተቀበለውም:: ይልቁንም ጨርቄን ማቄን ሳይል ‹‹ጥራኝ ዱሩ›› ብሎ ለነፃነቱ መፋለም ጀመረ:: የኢጣሊያ ወራሪ ኃይልም አንዲትም ቀን እንኳን እፎይ ብሎ ሳይቀመጥ ከአምስት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሌላ የሽንፈት ማቅ ለብሶ ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረ:: ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም፣ ከስደት የተመለሱት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ በአዲስ አበባ፣ ታላቁ ቤተ መንግሥት ተገኝተው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀሉ::
ታዲያ በዚህ አስገራሚና አኩሪ የመስዋዕትነት ጉዞ ውስጥ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ያሳዩት ደማቅ የጀግንነት ታሪክ ምንጊዜም ቢሆን አይዘነጋም:: ኢትዮጵያውያን አርበኞች በወራሪው የፋሺስት ጦር ላይ ድል የተቀዳጁት እጅግ መራራ ትግሎችን አድርገውና መስዋዕትነቶችን ከፍለው ነው:: የየካቲት 12-15 የአዲስ አበባ፣ የሚያዝያ ሦስት የአመፀኛ ዋሻ እና የግንቦት 12 የደብረ ሊባኖስ አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች የመስዋዕትነቶቹ ማሳያዎች ናቸው::
ይሁን እንጂ የፋሺስት ኢጣሊያ አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች የኢትዮጵያውያንን የፀረ-ፋሺዝም ትግል ማስቆም አልቻሉም:: ጀግኖቹ አርበኞች በቂ ስንቅና ትጥቅ ሳይቀርብላቸው ልጆቻቸውንና የትዳር አጋሮቻቸውን ጭምር በማሠለፍና በዘመኑ የነበረው ውስጣዊ ሽኩቻ ሳይበግራቸው፣ እግራቸውን ለጠጠር ደረታቸውን ለጦር ሰጥተው በከፍተኛ ፍቅርና ጀብዱ እናት ሀገራቸውን ከፋሺስቶች ባርነት ታድገዋል:: ኢትዮጵያንም ብቸኛዋ ለቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከከች አፍሪካዊት ሀገር በማድረግ ስሟን በደማቅ ቀለም አስፍረዋል::
ቀደም ባሉት ዘመናት ኢትዮጵያ በውጭ ጠላቶች ላይ ድሎችን በመቀዳጀት ረገድ ዓለም የሚደነቅባቸው አንፀባራቂ ታሪኮችን አስመዝግባለች:: ጉራዕ፣ ጉንደት፣ ሰሃጢ፣ ዶጋሊ፣ ዓድዋ፣ ካራማራ እና የፀረ-ፋሺስት አርበኞች ድል የእነዚህ ታሪኮች ጥቂት ማሳያዎች ናቸው:: እነዚህ ድሎች ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ በጋራ ተሰልፈው ዓለምን ያስደነቀ ገድል መፈፀማቸውን ለመላው ዓለም ያሳዩባቸው አኩሪ ገድሎች ናቸው::
ይሁን እንጂ እነዚህ ድሎች ያስገኙት በረከትና የፈጠሩት እድል በሚገባ ተመንዝሮ ጥቅም ላይ አልዋለም:: የእነዚህን ድሎች ትርጉሞችና በረከቶችን እያሰብን የኢትዮጵያን ያለፉትን ዓመታት (በተለይ 50 ዓመታት) ጉዞ ስንቃኝ ‹‹ለመሆኑ ኢትዮጵያ/ኢትዮጵያውያንና የጉንደት/ጉራዕ/ ዓድዋ/ካራማራ/የፀረ-ፋሺስት አርበኞች(ሚያዝያ 27) ድሎች ይታወቃሉ?›› ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን:: ሀገሪቱ በረሃብ፣ በግጭት፣ በዘረኝነትና በጦርነት ጎዳናዎች ላይ ደጋግማ መመላለሷና ከድህነት ጋር ተቆራኝታ መዝለቋ እነዚህ ታላላቅ ድሎች ያስገኙላትን በረከቶች መዘንጋቷንና አለመጠቀሟን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል::
ዓለምን ያስደነቀው የጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ታሪካዊ ገድል ሲዘከር፣ የአሁኑ ትውልድ ዙሪያውን የከበቡትን ችግሮች እንዴት በድል መወጣት እንደሚችል ትምህርት መቅሰምና በጥልቀት ማሰብ ይኖርበታል:: ሀገር ከችግር የምትላቀቀው በሁሉም ዜጎች ትብብር እንጂ በተናጠል እርምጃ አይደለም::
አርበኞች በፋሺስት ጦር ላይ ድል የተቀዳጁት በትብብር ባካሄዱት ትግል ነው:: ከተባበሩና ከሁሉም ነገር በፊት ሀገርን ማስቀደም ከተቻለ የኢትዮጵያን አሁናዊ ችግሮች ድል ማድረግ እንደሚቻል ከአርበኞቹ የጋራ ትግልና ድል መማር ይቻላል:: ኢትዮጵያውያን በችግሮቻቸው ላይ ድል ለመቀዳጀት በትብብር መስራታቸው አስገዳጅ ይሆናል:: በትብብር ያልተሰራ ሥራ ዘላቂና አስተማማኝ ውጤት የማስገኘት እድሉ አነስተኛ ነው:: ስለሆነም አቅምን አሰባስቦና ደምሮ በቅንጅት ለመሰለፍ ቁርጠኝነትና ዝግጁነት ሊኖር ይገባል::
ኢትዮጵያ የገጠሟትን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች ድል ለማድረግ ከግል ጥቅም ይልቅ ኢትዮጵያን ማስቀደም ይገባል:: አርበኞች ለኢትዮጵያ ክብር ለመፋለም ሲወስኑ የግል ኑሯቸውን ትተው ነው:: የሀገርን ችግር ለመፍታት ከግላዊ ዓላማና ስንቅ ይልቅ ሀገራዊ ዓላማ መያዝ ያስፈልጋል:: ለሀገር ጥቅምና ኩራት የሚከፈል ዋጋ መራራ ቢሆንም ውጤቱ ግን ጣፋጭና የሚያኮራ ነው::
ኢትዮጵያን ከህመሟ ለመፈወስ በቅድሚያ ሀገርንና ሕዝብን መውደድና ማክበር ይገባል:: የሀገርና የሕዝብ ፍቅር ያለው ግለሰብና ቡድን ሁልጊዜም ቢሆን ኃላፊነት ይሰማዋል:: ኃላፊነቱን ለመወጣት ደግሞ ከሌሎች ጋር ስለመተባበር፣ በጥንቃቄና በፅናት ስለመራመድ ብሎም ስለማሸነፍ ያስባል፤ ይተጋል:: አርበኞች ለሀገራቸው ክብር የተፋለሙት ሀገራቸውንና ወገናቸውን ስለወደዱና ስላከበሩ ነው::
የኢትዮጵያን ችግሮች ለመፍታት የሚያስፈልገው ሌላው ግብዓት ጽናት ነው:: አርበኞችን ለድል ያበቃው ቁልፍ ምስጢር ፅናታቸውና ወኔያቸው ነበር:: የጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ሲወሳ ለአምስት ዓመታት የተደረገ እልህ አስጨራሽ ትግል መሆኑን መዘንጋት አይገባም:: ይህ መራር ትግል ፅናትን የሚፈታተን፤ መፈጠርን የሚያስጠላ፤ አባት፣ እናት፣ ወንድም፣ እህትና ሌሎች ወገኖች ሳይቀሩ በፋሺስቶች ጭካኔ የተጨፈጨፉበት፤ ሞት በየዕለቱ በርካቶችን ያጋዘበት፣ መንደሮች በየቀኑ በፋሺስቶች የጦር አውሮፕላኖችና መድፎች ሲወድሙ የሕፃናትና የእናቶች እሪታ ከዕልቂት ጋር የተሰማበት ነበር::
ፊት ለፊት ከገጠመው ግዙፍ አውሮፓዊ ጠላት ጋር ከሚደረገው ትንቅንቅ ባልተናነሰ፣ በግለሰብ አመራሮች መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ተስፋ አስቆራጭ አጋጣሚዎች የታዩበት፣ ስመጥር አዋጊ አርበኞች ለፋሺስቶች ባደሩ ባንዳዎች በሽምቅ የተገደሉበትና የፋሺስቶች ፕሮፓጋንዳ እየተነዛ መወላወል የተስተዋለባቸው ፈታኝ ሥቃዮች በጽናት የታለፉበት የትግል ጉዞም ነበር::
የኢትዮጵያ ችግሮችም እልህ አስጨራሽ ትግል፣ ጽናትንና ተስፋ አለመቁረጥን የሚጠይቁ ናቸው:: አንዱ ችግር ሲፈታ ሌላ የችግር ምንጭ እንደሚፈልቅ አይተናል:: እነዚህን ችግሮች ጠራርጎ ለማስወገድ ደግሞ ተስፋ አለመቁረጥ ያስፈልጋል:: የሁሉንም ችግሮች ምንጭ ለማድረቅ የሚያስችል የጽናት ኃይል መታጠቅ እጅግ ያስፈልጋል::
ኢትዮጵያውያን አንዱን ችግር ከፈቱ በኋላ፣ ሌላ ችግር ሲፈጠር ተስፋ የሚቆርጡ ከሆነ ሁለ ገብ ድል አይገኝም:: የዘላቂና አስተማማኝ ድል ባለቤት ለመሆን ችግሮች በየጊዜውና በየቦታው ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ቀድሞ መጠበቅና መዘጋጀት እንዲሁም ሁሉንም ችግሮች ለመጋፈጥ በጽናት መቆም ይገባል:: ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች አሸናፊ እንድትሆን የአሸናፊነት ወኔ ሊኖር ይገባል:: ልብ ከደከመና ተነሳሽነት ከሌለ አሸናፊነት አይታሰብም::
ምክንያታዊ አስተሳሰብ ቦታ እንዲያገኝ መትጋት ያስፈልጋል:: ምክንያታዊነት ማሰብን፣ ማሰላሰልን፣ ሚዛናዊ ዕይታንና መመርመርን የሚጠይቅ እንዲሁም ‹‹ምን?››፣ ‹‹እንዴት?››፣ ‹‹ለምን?››፣ ‹‹መቼ?››፣ ‹‹የት?›› የሚሉትንና ሌሎች ተያያዥ መሠረታዊና አመክንዮን የተከተሉ ወሳኝ ጥያቄዎችን በማንሳት እውነትን ከሐሰት አብጠርጥሮ የማጥራት እሳቤን ይይዛል:: ከአርበኞች ድል ተምሮ ኢትዮጵያን በክብር ለማሻገር ‹‹ለምን?›› እና ‹‹እንዴት?›› ብሎ ለመጠያየቅ፣ ለመከራከርና ለመወያየት የሚያስችል የሰለጠነ ባህል ማዳበር እጅግ አስፈላጊ ነው:: ይህን ማድረግ ከቻልን ‹‹የጀግኖች አርበኞች ልጆች ነን›› ብለን የማውራት ሞራል ይኖረናል::
ወንድይራድ ሰይፈሚካኤል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2016 ዓ.ም