የሰው ልጅ ሰብአዊ እሴቶችን ጠብቆ ለመጓዝ የሚያስችሉ የሞራል አስተምሮዎች ባለቤት ነው። እነዚህ እሴቶች በአብዛኛው የሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች መሰረት ሆነው በስፋት የሚጠቀሱ ናቸው። የሰውን ልጅ የለት ተዕለት ሕይወት በመግራት ያላቸው አስተዋጽኦም መተኪያ የሌለው ነው።
እምነት ፣ተስፋ ፣ፍቅር ፣ሰላም ፣ ትህትና ፣ በጎነት ፣ቸርነት ፣ አስተዋይነት እና ይቅርባይነት ወዘተ የየትኛውም ሃይማኖት አስተምህሮ መሰረቶች ናቸው። ከእነዚህ መንፈሳዊ እሴቶች ውጪ ሃይማኖት እና ሃይማኖተኝነትን ፤ ሰው እና ሰብአዊ እሴቶችን ማሰብ የሚቻል አይደለም። የሰው ልጅ ፍጥረታዊ ህልውናም ለእነዚህ እሴቶች የተገዛ እንደሆነ ይታመናል።
ከዚህ የተነሳም የሰው ልጅ እንደ ግለሰብ ሆነ እንደ ማኅበረሰብ ህልውናውን እስጠብቆ ለማቆየት፤ እንደተቀበለው ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ፤ለነዚህ መንፈሳዊ እሴቶች ራሱን አስገዝቶ ለመኖር የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። በተሳካለት መጠን ትርጉም ያለው ሕይወት መኖር የሚያስችለውን እድል ይፈጥራል።
ሁኔታዎች በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ከአቅሙ በላይ ሲሆኑበት /እንደ ግለሰብም ሆነ ማኅበረሰብ/ ትርጉም አልባ ፣ የተዘበራረቀ ሕይወት ለመኖር ይገደዳል። በተለይም የእለት ተእለት ሕይወቱ በነዚህ መንፈሳዊ እሴቶች እየተገራ ካልሄደ ፣ አጠቃላይ የህይወት ጉዞው በብዙ ተግዳሮቶች የሚፈተን እና የተጎረባበጠ መሆኑ የማይቀር ነው።
ከዚህ የተነሳም መንፈሳዊ እሴቶችን ማሰብ እና ለእነርሱ የሚገዛ ህይወት ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ፣ ሃይማኖታዊ በአላት እና በአላትን ተከትሎ በሚደረጉ ሥርዓቶችን ተከትሎ ብቻ የሚከናወን አይደለም፣ ከዚህ ይልቅ እሴቶቹን የህይወት መርህ አድርጎ መውሰድ እና መተርጎምን የሚጠይቅ ነው።
እንደሌሎች ሃይማኖቶች ይህ አስተምህሮ በክርስትና ሃይማኖት ገዝፎ የሚስተዋል ነው። ሃይማኖቱ ከሁሉም በላይ ሰውን ሰው ላሰኙ መንፈሳዊ እሴቶች ከፍ ያለ ትኩረት የሚሰጥ ፣ እነዚህ እሴቶች የእለት ተእለት የህይወት መርህ አድርጎ መውሰድን የመኖር ትርጉም አልፋ እና ኦሜጋም አድርጎ በስፋት የሚሰብክ/የሚያስተምር ነው።
እንደ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደ ማኅበረሰብ ላለን የጋራ ሕይወት ስኬት እነዚህ እሴቶች ዋነኛ ጉልበት እንደሆኑ ከማስተማር ባለፈ ፣ እንደ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ዛሬ ላይ እንደሀገር ፈተና ከሆኑብን ችግሮቻችን ወጥተን ፣ተስፋ ያደረግናቸውን ነገዎቻችን ለመውረስ እነዚህ መንፈሳዊ እሴቶች መ ተኪያ የሌላቸው አቅሞቻችን እንደሆኑ አ በክሮ ያስተምራል።
እነዚህ እሴቶች በአንድም ይሁን በሌላ ለሀገረ መንግሥት ምስረታችን ሆነ፣ ሀገረ መንግሥቱ ዘመናት እንዲሻገር፣ ከዚያም በላይ እንደ አንድ ትልቅ ማህበረሰብ /ሕዝብ ተጋምደን ዛሬ ላይ እንድንደርስ የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ እንደሆነ ይታመናል። ነገ ላይ ተስፋ ለምናደርጋት የበለጸገች ኢትዮጵያም አቅሞች ስለመሆናቸው ለማሰብ የሚከብድ አይደለም።
ዛሬ ላይ እየተፈታተነን ላለው ፍቅር ማጣት ከዚህ የሚመነጭ ጥላቻ እና አለመደማመጥ ከዚህ የሚመነጭ የቋንቋ መደበላለቅ፣ እልኸኝነት ከዚህ የሚመነጭ ዳተኝነት፣ ራስ ወዳድነት ከዚህ የሚመነጭ ሕሊና አልባነት ፣ ስግብግብነት እና ነፍሰ ገዳይነት ልንወጣ የምንችለው በእለት ተእለት ሕይወታችን ለእነዚህ መንፈሳዊ እሴቶቻችን ስፍራ ስንሰጥ ብቻ ነው።
እነዚህም እሴቶች ሃይማኖታዊ በዓላት ፤ለማስታወስ ከዛም በላይ ለመኖር የሚደረጉ ጥረቶች የሚበረታቱ ቢሆኑም ፣ከሃይማኖት ቀናቱ ባለፈ ፣የእለት ተእለት የህይወት መርህ አድርጎ መውሰድ ከያንዳንዱ ምእመናን የሚጠበቅ ነው ።ይህን ማድረግ ስንችል ብቻ ነው እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ ያለን ሕይወት ትርጉም ያለው፤ ከትናንት የተሻለ ፣ ነገን ተስፋ ሊያደርግ የሚችለው።
ከዚያም በላይ ፣እንደሀገር ካለንበት የግጭት አዙሪት ወጥተን ያለንን የተፈጥሮ ሀብት አልምተን ፣ለራሳችንም ሆነ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር የምንገነባው፤ ከአሮጌ ትርክቶች ወጥተን አዲስ የሀገር እና የሕዝብ ልዕልና የተላበሰ ትርክት መፍጠር የምንችለው!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2016 ዓ.ም