ድጋፉ በጃፓን እና በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት ይበልጥ ያጠናክራል

አዲስ አበባ፡- የጃፓን መንግሥት በሲዳማ ክልል በደራ ኦትልቾ ወረዳ ለሚገኘው ተፈሪ ኬላ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያደረገው የማስፋፊያ ግንባታ ድጋፍ በጃፓንና በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት ይበልጥ እንደሚያጠናክር ተገለጸ፡፡

ድጋፉ ሰሞኑን ሲደረግ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ እንደገለጹት፤ የተደረገው የድጋፉ ስምምነት በጃፓን እና በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ያለውን ወዳጅነት የበለጠ ለማጠናከር ይረዳል፡፡ ድጋፉ ለትምህርት ቤቱ አራት የመማሪያ ክፍሎችን ከነሙሉ እቃው አካቶ የያዘ አንድ ህንጻ ለመገንባት የሚረዳ ነው። ግንባታው ሲጠናቀቅም ከ200 በላይ አዳዲስ ተማሪዎችን በትምህርት ቤቱ እንዲማሩ ያስችላቸዋል።

አጠቃላይ ለፕሮጀክቱ እስከ 70 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ እንደሚደረግ ያነሱት አምባሳደሩ፤ የጃፓን መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑንና ትኩረት ከተሰጠባቸው ዘርፎች መካከልም የትምህርት ዘርፍ አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል።

ለሕፃናት መሰረታዊ ትምህርት መስጠት ለሀገር ብሩህ ተስፋ መሆኑን ጠቁመው፤ ፕሮጀክቱ ወደትክክለኛ ትግበራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ ትምህርት ቤቱ በፕሮጀክቱ ትግበራው ወቅት ከኤምባሲው ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደሚኖረው እና ፕሮጀክቱን በፍጥነት በማጠናቀቅ ህፃናቱ አዲሱን የትምህርት ቤት ህንጻ በአፋጣኝ እንዲጠቀሙበት እንደሚደረግ አመላክተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የማንነት አስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ዳይሬክተር ጴጥሮስ ወልደሰንበት በበኩላቸው፤ የቀድሞ ተፈሪ ኬላ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ መሆናቸውንና ለስራ ወደስፍራው በሄዱበት ወቅት ትምህርት ቤቱ እንደነበረ መመልከታቸውን አስታውሰው፤ እንዲሻሻል ፕሮጀክት አዘጋጅተው ተቀባይነት እንዳገኘ ተናግረዋል፡፡

ልጆች የአስተዳደግ ሁኔታቸው ምንም ይሁን ምን ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ሁሉም አካል ሳይታክት መትጋት እንዳለበት የገለጹት አቶ ጴጥሮስ፤ የማስፋፊያ ግንባታው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አመላክተዋል፡፡

ይህ የድጋፍ ስምምነት በኢትዮጵያ የትምህርት ተደራሽነትን እና ጥራትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት አስደሳች ምዕራፍ መጀመሩን እንደሚያሳይና ፕሮጀክቱ መሠረተ ልማቶችን ከማቅረብ ባለፈ ተማሪዎችን ወደ ሙሉ አቅማቸው እንዲደርሱ የሚያበረታታ እና ምቹ የትምህርት አካባቢ ለመፍጠር እንደሚረዳ አቶ ጴጥሮስ ጠቁመዋል።

ጃፓን በኢትዮጵያ የትምህርት እና በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ ድጋፍ ስታደርግ እንደነበር ያነሱት አቶ ጴጥሮስ ለትምህርት ቤቱ ድጋፍ እንዲደረግ ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት የጃፓን ኤምባሲ ላደረገው ድጋፍ እና አጋርነት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29/2016 ዓ.ም

Recommended For You