ዩኒቨርሲቲው የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን እያዘመነ ነው

– የሬጅስትራር አገልግሎቱ ወደኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት ተሸጋግሯል

አዲስ አበባ፦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የዩኒቨርሲቲው የሬጅስትራር አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ወደኤሌክትሮኒክስ ሥርዓት መሸጋገሩም ተገልጿል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሬጅስትራር ዋና ዳይሬክተር አደይ ፈለቀ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡ የሬጅስትራር አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዘመነ ይገኛል፡፡

በዚህ ሂደት ሙሉ ለሙሉ ወረቀት ተኮር ከሆነው ሥርዓት ወደኤሌክትሮኒክ ሥርዓት ሽግግር ተደርጓል ብለዋል፡፡

በዚህም በሬጅስትራሩ አሰራር ሥርዓት ተማሪዎች በቅድሚያ በተዘረጋላቸው የኦንላይን መንገድ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ በማሟላት እንዲያመለክቱ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

ከጤና ሚኒስቴር ተመድበው ለሚመጡ ተማሪዎች ብቻ ባለድርሻ አካላቱ የትምህርት እና የጤና ሚኒስቴር ስር በመሆናቸው ሂደቱ እንደሚለይ ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎች ከምዝገባ ጀምሮ የመግቢያ ፈተናቸውንም በኦንላይን በመውሰድ ውጤት እዚያው በፍጥነት እንዲያውቁ እንደሚደረግ ያነሱት አደይ (ዶ/ር)፤ 99 በመቶው የተማሪዎች የማመልከቻ ሥርዓት በኦንላይን እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች በትምህርት ክፍል መረጣ ወቅት፣ ተማሪዎች በሚያመለክቱበት ጊዜና በሌሎችም ሂደቶች በአሰራር ሥርዓቱ ላይም ሆነ በተለያዩ ሁኔታዎች የሚነሱ ቅሬታዎች ሲኖሩ ሬጅስትራሩ እንደ አስፈላጊነቱ ፈጣን ምላሾችን እየሰጠ እንደሆነ ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ሬጅስትራሩ የድህረ ምረቃ፣ የቅድመ ምርቃ እና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ለትምህርት ወደ ዩኒቨርሲቲው በሚመጡበት ወቅት አስፈላጊውን ሂደት አሟልተው እንዲመጡ በማድረግ ወደመማር ማስተማር ሥርዓቱ እንዲቀላቀሉ እያደረገ ነው፡፡

ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው በሚያደርጉት ቆይታ የሚጠበቅባቸውን በማሟላት ትምህርታቸውን አጠናቀው ለምረቃ ብቁ በሚሆኑበት ወቅት ከዩኒቨርሲቲው ሴኔት ጋር በመማከር ምርቃታቸውን የማጽደቅ ተግባር እንደሚያከናውንም ገልጸዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራስ ገዝ መሆን በተለያዩ ዘርፎች የሚፈጥራቸው ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ዶክተር አደይ ተናግረዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን አሠራራቸውን ለማዘመንና ራዕያቸውን እንዲያሳኩ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ከሆነ በኋላ በርካታ መሻሻሎችን እያመጣ መሆኑንም በማሳያነት አንስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከተማሪዎች ቅበላ እና ከክፍያ ስርዓት ጋር ተያይዞ እየተቀየሰ ያለውን ፖሊሲና መመሪያን መሰረት በማድረግ በሚቀጥሉት ዓመታት የትምህርት ክፍያውን ጨምሮ በርካታ የሚሻሻሉ ጉዳዮች ይኖራሉ ሲሉም አክለዋል፡፡

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You