የሲምቢጣን ታሪክ የቀየሩት የአርሶ አደሮቹ እጆች

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ሃላባ ዞን፣ በወይራ ዲጆ ወረዳ የምትገኘውን ሲምቢጣ ቀበሌን የሚያውቃት ሁሉ ሁሌም ከአዕምሮው አንድ ነገር አይጠፋም፤ ይኸውም ዝናብ በጣለ ቁጥር መላውን የሲምቢጣ አካባቢ የሚያጥለቀልቀው ጎርፍ ነው:: ሕዝቡም ቢሆን በብዙ ጥረት ያለማው ማሳና የገነባው ቤት በደራሹ ገርፍ ሲዋጥበት ቤተሰቡንና ራሱን ለማዳን በየዓመቱ ቀዬውን ሲለቅ ኖሯል::

የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስቱ የሲምቢጣ ስም በተነሳ ቁጥር ያ መከረኛ ጎርፍ ስለመምጣቱ አይጠራጠሩም፤ እናም ሕዝቡን ለማዳን ከዚህም ከዚያም ይሯሯጣሉ፤ በጎ አድራጊዎችም ለእርዳታ ይረባረባሉ:: ግን ደግሞ ሁሌም ቢሆን ጎርፉ መምጣቱም ሆነ ሕዝቡም መፈናቀሉና እርዳታ መጠበቁ የማይቀሩ ክስተቶች ሆነው ቆይተዋል::

አሁን ግን ያ ታሪክ ተቀይሯል፤ አንድም ሰው ቢሆን በጎርፍ ምክንያት ቀዬውን ለቆ አይሄድም፤ የእርዳታ እጅም አይጠበቅም:: ይልቁንም ሲምቢጣዎች ቀኑ ነግቶ እስኪመሽ ድረስ የእርሻ ማሳቸውንና ጓሯቸውን ይቆፍራሉ፤ ይተክላሉ፤ የተከሉትን ይንከባከባሉ፤ የደረሰውን ምርት ይሰበስባሉ፤ ገበያ የሚወጣውን ያወጣሉ:: ይህ የብርቱዎቹ ሲምቢዎች የቀን ተቀን ውሎ ነው::

ከእነዚህ ብርቱ የሲምቢጣ አርሶ አደሮች መካከል ደግሞ አርሶአደር ገረመው መሃመድ አንዱ ናቸው:: እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ከዚሀ ቀደም በተወሰነ ደረጃ በቆሎና ስንዴ ያለሙ ነበር:: ይሁንና አብዛኛውን ጊዜ በዘር የሸፈኑት ማሳ በጎርፍ የሚጎዳ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ችግር ውስጥ በመግባታቸው የመንግስትን እርዳታ ጠባቂ ለመሆን ተገደው ነበር:: ሁሌም ቢሆን ጎርፍ በመጣ ቁጥር ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደአጎራባቾቻቸው ቀበሌዎች ቤተሰባቸውን ይዘው ይሄዳሉ::

ልጆችን አስተምሮ ለወግ ማዕረግ ማብቃት ቀርቶ አብልቶ ሕይወትን ለማቆየት ፈተና የሆነበት አጋጣሚ ነበር:: አካባቢው ከሁለት አቅጣጫ በሚመጣ ጎርፍ ይጥለቀለቅ ስለነበርም ከመላው ቀበሌ አንዲት ቅርጫት ምርት እንኳን መሰብሰብ አይቻልም:: ከዚያ ይልቅም ጎርፍ የተኛበትን ሳር ሽጦ የእለት ጉርሱን ለመሸፈን ይጣጣር ነበር::

‹‹ጎርፉ ከሚያደርስብን ጫና የተነሳ ልጆቻችንን ማብላትም ሆነ ማስተማር ለእኛ እጅግ ከባድ ነበር፤ ከሁሉም በላይ ጎርፉን ተከትሎ በሚከሰቱ ወረርሽኞች በሽታዎች ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያጡበትና ሕክምና ለማግኘት የሚያዩት ውጣ ውረድ ከፍተኛ ነበር›› ይላሉ::

ይሁንና ከአምስት ዓመት በፊት ለመፀዳጃ የሚሆን ጉድጓድ በአንድ ሰው አማካኝነት እየተቆፈረ በነበረበት ወቅት በአካባቢው ሰፊ የከርሰ ምድር ውሃ መኖሩ ይረጋገጣል:: ይህንንም ለማጣራት ያስችላቸው ዘንድም መቂ ድረስ በመሄድ ባለሙያ አምጥተው ማስፈተሻቸውን ይጠቅሳሉ:: ከባለሙያውም በአካባቢው ሰፊ የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት በመኖሩ፤ የመስኖ ልማት ቢሞክሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ለአካባቢው አርሶአደሮች ምክር እንደተሰጣቸው ያመለክታሉ:: ‹‹በአሁኑ ወቅት በማህበር ተደራጅቼ ሙዝ፣ አቦካዶ፣ ፓፓያ፤ ቡናና ሌሎችንም አትክልቶች አመርታለሁ፤ በዚህም ከፍተኛ ገቢ እያገኘሁ ኑሮዬን አሻሽያለሁ›› ይላሉ::

‹‹ማንኛውም ዜጋ ድህነትን ቤት ውስጥ አስቀምጦ ልጆች ማሳደግም ሆነ ኑሮውን መለወጥ አይችልም የሚል መግባባት ፈጥረን እናቶችና ሕፃናት ሳይቀሩ ወደ ልማት ገብተናል፤ በዚህም ከዚህ ቀደም ከነበርንበት እርዳታ ጠባቂነት ሙሉ ለሙሉ ተላቀናል፤ ልጆቻችን የተመጣጠነ ምግብ በልተው በጥሩ ሁኔታ እያደጉልን ነው፤ አንዲትም እናት ምግብ ፍለጋ አትሰደድም፤ ከዘይትና ጨው ውጪ ገበያም አትወጣም፤ ምክንያቱም ለምግብ የሚያስፈልጋትን ሁሉ ከጓሮዋ የምታገኝ በመሆኑ ነው›› ሲሉም ያስረዳሉ::

ማኅበረሰቡ በተፈጠረው መግባባት መንግስት የሚሰጠውን የሴፍትኔት ድጋፍ በመተው ፊቱን ሙሉ ለመሉ ወደ ልማት ማዞሩን ያመለክታሉ:: ‹‹በሴፍትኔት ፍለጋ የምናቃጥለውን ጊዜ ወደጓሮ ልማት በማዞራችን ውጤታማ ሆነናል፤ ልጆችንም በቅርበት ተንከባክበን ለማሳደግ ችለናል፤ በሴፍትኔት በወር የምናገኘው ቢበዛ 900 ብር ነበር፤ አሁን በአንድ የሙዝ ተከል አንድ ዙር ምርት ብቻ 700 ብር እናገኛለን፤ በትንሹ 10 ሙዝ ያለው አርሶአደር ሰባት ሺ ብር ያገኛል›› በማለት ጥቅሙ ፈፅሞ ለውድድር የሚቀርብ አለመሆኑን ያብራራሉ:: አብዛኞቹ አርሶአደሮች ባመረቱት ምርት የገቢ አቅማቸው በማደጉ የሳር ጎጆዎቻቸውን ወደ ቆርቆሮ ቤት ቀይረዋል፤ የአኗኗር ዘይቤያቸውንም አሻሽለዋል ይላሉ:: በቀጣይም ሁሉንም የሲምቢጣ አርሶ አደር ከተረጂነት ለማላቀቅ ነዋሪው ርብርቡን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት::

አሁን ላይ አርሶአደር ገረመውም ሆነ ጎረቤቶቻቸው ከራሳቸው አልፈው ሸኖ ወረዳ፣ ሃላባ ዞን፣ ስልጤ ዞን፣ ሳንኩራ፣ ወራቤ፣ ቡታጅራና በሌሎችም አካባቢዎች ላይ ምርቶቻችንን ተደራሽ ያደርጋሉ:: የቀበሌዋ አርሶአደሮች በተለይም በ2016 በጀት ዓመት ጥቅል ጎመንና ቲማቲም በስፋት በማምረት አዲስ አበባ ድረስ መላክ መጀመራቸውን ይጠቅሳሉ::

የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የወረዳው ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገበና ሰማን እንደሚሉት፤ በወረዳዋ ካሉት 26 ቀበሌዎች መካከል ሰባቱ የጎርፍ ተጋላጭ ናቸው:: ሲምቢጣ ደግሞ ከሁሉም በላይ ጎርፉ የሚያጠቃው ቀበሌ ነው:: በዚህ ምክንያት አብዛኛው የቀበሌዋ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ይኖሩ ነበር:: ጎርፉን መቀነስ ያስችል ዘንድ የክልሉ መንግስት ከዞንና ወረዳ 3 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ዲጆ ወንዝ ላይ መቀለሻ ተሰርቷል:: የተራቆቱ አካባቢዎች ላይ ደግሞ የተፋሰስ ሥራ በሕዝቡ ርብርብ ተከናውኗል::

‹‹ሲምቢጣ ላይ በተለይ ክረምት ወቅት ጎርፉ ለሕይወት አደገኛ በመሆኑ ማንኛውም ሰው መግባት አይችልም ነበር፤ አይደለም መኪና በእግር መግባት የማይቻልበትም ነበር›› ሲሉ የሚያስታውሱት ኃላፊው፤ በሀገር ደረጃ የበጋ መስኖ ስንዴ ከተጀመረ ወዲህ ግን በስንዴም ሆነ በሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ከፍተኛ አምራች ቀበሌ መሆን መጀመሯን ያመለክታሉ:: በተለይ ደግሞ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሲምቢጣ ቀበሌ ትታወቅበት የነበረውን ክፉ ታሪክ መቀየሯን ያመለክታሉ:: ‹‹አምና ስምንት ሺ የሙዝ ችግኝ ከአርባ ምንጭ አምጥተን በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት ማግኘት ጀምረናል›› ይላሉ::

ይህንን ለማድረግ ግን አስቀድሞ ለአርሶአደሩ ሰፊ የግንዛቤ ማስበጫ ስራ መሰራቱን ይጠቅሳሉ፤ ‹‹ከአርሶአደሩ ጋር መግባባት ከፈጠርን በኋላ በተለይም በአጭር ጊዜ ውስጥ አርሶአደሩ ምርት የሚያገኝበትን መንገድ ለማሳየት ገበሬውን አሰልጥነናል›› ይላሉ:: በተጨማሪም የግብርና ባለሙያዎችን ቁጥር በርከት በማድረግ አርሶአደሩን መሬት ከማዘጋጀት ጀምሮ ምርቱ እስኪሰበሰብ ድረስ ከስር ከስሩ እንዲደግፉ መደረጉንም ያስረዳሉ:: ሙዝ ደግሞ በቂ ውሃና እንክብካቤ የሚፈልግ በመሆኑ ባለሙያዎቹ ያለመታከት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ይጠቁማሉ:: ‹‹ሙዙን ከአርባ ምንጭ ካመጣን በኋላ በቅድሚያ በ100 አርሶአደሮች ጓሮ ላይ ጉድጓድ አስቆፍረን ተከልን፤ እሱም በ11 ወራት ውስጥ ምርት መስጠት ጀመረ›› ሲሉም ያብራራሉ::

እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ በሲምቢጣ ቀበሌ የተጀመረው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስኬታማ ይሆን ዘንድ በቅድሚያ የልማት ቡድን የተደራጀ ሲሆን፣ ለዚህ ቡድን አባላትም ከጉድጓድ ዝግጅት ጀምሮ ባሉ ስራዎች ላይ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል:: በጎርፍ የተራቆተውን አፈር ለማልማትም ኮምፖስት በስፋት እንዲጠቀሙ ተደርጓል::

ሲምቢጣን ጨምሮ በስምንት ቀበሌዎች ላይ የመስኖ አውታሮች ግንባታ ተከናውኗል:: ከዚሁ ጎን ለጎንም የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ሲሆን፣ ይሁንና አካባቢው ከጎርፍ ባሻገር ከፍተኛ የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር ያለበት በመሆኑ ሕብረተሰቡን በማስተባበር በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መንገዱን ምቹ የማድረግ ስራ ተሰርቷል::

ሲምቢጣን ጨምሮ በስምንት ቀበሌዎች ላይ በመስኖ አውታሮቹ በመጠቀምም የስንዴ ልማት ስራ መከወኑን የሚጠቅሱት ምክትል አስተዳዳሪው፤ ከዚሁ ጎን ለጎን የክልሉ ኢኒሼቲቭ የሆነውን 30-40-30 የልማት መርሃግብር ተግባራዊ የማድረግ ስራ መሰራቱን ያስረዳሉ:: ‹‹በአሁኑ ወቅትም የተገኘውን ተሞክሮ በመቀመር በ26 ቀበሌዎች ላይ ለማዳረስ እየሰራን ነው፤ በተለይ አትክልትና ፍራፍሬ በስፋት በማልማት ለአዋሳኝ ወረዳዎችና ዞኖች ጭምር ምርቱን ማቅረብ ችለናል›› ሲሉም ያስረዳሉ::

በዋናነትም ቲማቲምና ጥቅል ጎመን በስፋት መመረቱን ጠቅሰው፤ ይሁንና የግሪሳ ወፍ በስንዴ ልማቱ ላይ ጉዳት በማድረሱ፣ ዋግም በመከሰቱ ምክንያት ከአምናው ምርት ዘንድሮ የቀነሰበት ሁኔታ መፈጠሩን አቶ ጎበና ያመለክታሉ:: ይህ በመሆኑ ምክንያት ለስንዴ የተለየው ማሳ ባዶ እንዲሆን በማለም አርሶአደሩ ፊቱን ወደ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያዞር መደረጉን ይጠቅሳሉ:: ለዚህ ደግሞ ከስድስት እስከ 20 ሜትር የሚደርሱ በርካታ ጉድጓዶችን በመቆፈር የከርሰ ምድር ውሃ በማውጣት በመስኖ እንዲለማ መደረጉን ያስረዳሉ:: ወረዳውና ዞኑ በመተባበር አርሶአደሩ አንድ ለአምስት እንዲደራጅ አድርገን፤ በኩታ ገጠም እንዲያርሱና፣ የውሃ ፓምፖችን እንዲጠቀሙ አድርገናል›› ይላሉ:: ግን ደግሞ የነዳጅ ዋጋ በመናሩ ምከንያት አርሶአደሩ የተቸገረበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህንን ችግር ለመፍታትም ከዞኑ ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ጋር በመተባበር የድጋፍ ስራ መሰራቱን ነው ያብራሩት::

እንደ ምክትል አስተዳዳሪው ገለፃ፤ እንደማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያሉ ግብዓቶችን አርሶአደሩ በወቅቱና በበቂ ሁኔታ እንዲያገኝ ርብርብ ተደርጓል:: ከዚህም ጎን ለገጎን ለከርሰ ምድር ውሃ ማውጫ የሚጠቀምበትን የነዳጅ ችግር ለመፍታት ያስችል ዘንድ የሶላር ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ማከፋፈል ተችሏል:: በአሁኑ ወቅትም የውሃ አማራጭ ባለባቸው አካባቢዎች ላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቱን የማስፋት ስራ እየተሰራ ሲሆን በተለይም የሙዝ ምርቱን ለማስፋት በሁለት ቀበሌዎች የሚኖሩ 300 አርሶአደሮችን በማደራጀት 17 ሺ ሙዝ የሚተከልበት ጉድጓድ ተዘጋጅቶ በተወሰነ ደረጃ ተከላ ተጀምሯል:: በሽታ እንዳይስፋፋ በቂ ባለሙያዎችን በመመደብ የቁጥጥር ስራ እየተሰራ ነው:: በተጓዳኝም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ከሌሎች ወረዳዎች ጋር በመቀናጀት ጭምር የሚሰሩ ይሆናሉ::

በአሁኑ ወቅት የወረዳው ምርቶች ከአካባቢው ገበያ ባሻገር እስከ ዲላና ወላይታ ሶዶ ድረስ ተፈላጊ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቁመው፤ ወረዳው የገበያ ትስስር በመፍጠር ሚናውን እየተወጣ እንደሆነም ያመለክታሉ:: በቀጣይም በሁሉም የወረዳዋ ቀበሌዎች የማስፋፋት ስራ እንደሚሰራ አመልክተው ይሁንና በመንገድ መሰረተ ልማት ችግር ምክንያት ምርት ሊባክን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ያስረዳሉ::

‹‹በእኛ አቅም 406 ሚሊዮን ብር በሚገመት ጉልበት አርሶአደሩን በማስተባበር መንገዱን ምቹ የማድረግ ስራ ሰርተናል፤ ይሁንና በርካታ ድልድዮች የሚያስፈልጉ በመሆናቸውና ይህም በእኛ አቅም የሚሰራ ባለመሆኑ ለሚመለከታቸው የዞንና የክልል አካላት ሪፖርት አድርገናል›› ሲሉ ይጠቅሳሉ:: ከጸሀይ ኃይል /ሶላር ቴክኖሎጂ/ ጋር ተያይዞ ያለውን እጥረት ለመፍታት የክልሉ መንግስት ቃል የገባላቸው መሆኑን ነው ያስገነዘቡት::

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የግብርና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ የሲምቢጣ አርሶአደሮች ከነበሩበት የተረጂነት ሁኔታና አስተሳሰብ ተላቀው ወደ አምራችነት ብሎም እስከ ማዕከላዊ ገበያ ድረስ ምርት ማቅረብ የቻሉበት መንገድ ከክልሉ አልፎ ለመላው ሀገሪቱ አርሶአደሮች ምሳሌ ያደርጋቸዋል:: ሴፍትኔት ከመጠበቅ ወጥተው ለክልሉ ገቢ ሁነኛ ምንጭ መሆን መቻላቸውም የሚያበረታታ ነው::

ይህን የምርታማነት ተሞክሮ ወደ ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ረገድ አርሶአደሮቹም ሆነ ወረዳው የሚያነሱት የሶላር ፓምፕና የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት የክልሉ መንግስት ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ያመለክታሉ:: ይሁንና በተለይ የሶላር ፓምፑ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገቡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በክልሉ አቅም ብቻ በታሰበው ልክ ተደራሽ ማድረግ አዳጋች መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት እንደሚገባም አስታውቀዋል::

ማህሌት አብዱል

 አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም

 

 

Recommended For You