ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ እየተመለከትን የምነገኘው የመሠረተ ልማት ሥራዎች ስሟን ከምግባሯ ጋር የሚያጣጥሙ ተግባራት እንደሆኑ እየተመለከትን ነው። የከተማ ልማት በባህሪው ብዙ ጉዳዮችን በውስጡ ይይዛል:: በተለይም ደግሞ አዲስ አበባን የመሰሉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ክዋኔዎች ማዕከል የሆኑ ከተሞች በመሠረተ ልማት እና በፅዳት ሊታሙ አይገባም።
ይህንን መነሻ በማድረግ እየተሠራ ያለው ተግባርም መልካም ጅምር መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። በእርግጥ ስር በሰደደ የመሠረተ ልማትና የመሳሰሉት ችግሮች የተተበተቡ ከተሞችን የሠለጠነ ከተማ የማድረግ ሥራ ብዙ ሥራዎችን የሚጠይቅ እንደሆነ ይታወቃል:: ይሁን እንጂ መንግሥት አሁን ከተማዋ ባለችበት መልኩ መቀጠል እንደሌለባትና አያሌ ማሻሻያዎች ማድረግ እንደሚገባ አምኖ የጀመራቸው ታላላቅ የልማት ርምጃዎች ተስፋ ሲጪዎች ናቸው።
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆንም የአፍሪካ ‹‹መዲና›› መሆኗ በራሱ ከመሠረተ ልማትና ከፅዳት አንፃር ለከተማዋ ብዙ ተግባራዊ ርምጃዎችን መውሰድ ይጠይቃል:: ከተማዋ የዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ነች። የኤምባሲዎችና የዲፕሎማቶች መናኸሪያ መሆኗ በራሱ ትኩረትን በቀላሉ እንድትስብ ያደርጋታል:: ይህ አጋጣሚ በጎ ጎን እንዳለው ሁሉ እነዚህን ተቋማትና የማህበረሰቡን የመልማት ፍላጎት የሚመጥን የከተማ አደረጃጀት ከሌላት ደግሞ በቀላሉ ገፅታዋን የሚያበላሹ አሉታዊ አጋጣሚዎች መፈጠራቸው አይቀርም። ለዚህ ነው ሰፋፊና ታላላቅ የመሠረተ ልማት ፕሪጀክቶች ትግበራ አስፈላጊ የሚሆነው።
የእነዚህ ሁሉ ዲፕሎማሲያዊ ተቋማት የስበት ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ የበርካቶች ቀዳሚ ዓይን ማረፊያም ነች። የፌዴራል መንግሥትና የከተማ አስተዳደሩም በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከተማዋን ማልማትን ቀዳሚ አጀንዳቸው ያደረጉት ከእነዚህ መሠረታዊ ምክንያቶች ተነስተው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል:: በእርግጥ አንድ ከተማ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ይሁንም አይሁንም ዘመኑ የሚጠይቀውን የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የኑሮ ዘይቤ፣ ዘመናዊነትና ደረጃውን የጠበቀ አስተዳደር ያሻዋል። በዚህ ላይ ከላይ ያነሳኋቸው ተቋማት መቀመጫ የመሆን አጋጣሚው ሲኖር ደግሞ የሚደረገው ትኩረት በእጥፍ እንዲጨምር ያደርገዋል።
ከተማዋ በዚህ ዓመት ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ ሲገነባባት የሚታየው መሠረተ ልማትና በቀጣይ እንዲኖራት የሚጠበቀው ቁመና ሲታሰቡ ሰፋ ያለ የቅርጽና የይዘት ለውጥ እንደምታደርግ የሚያሳይ ነው:: የኮሪደር ልማቱ ገና ከጅምሩ ይህንኑ እያመላከተ ይገኛል:: የመሠረተ ልማት ግንባታዎቹና የከተማዋን ውበት በመጠበቅ ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ሌሎች በርካታ ሥራዎች በእጅጉ ቀልብ ሰቅዘው የሚይዙ ናቸው:: ለዚህ ነው የልማት ሥራዎቹ ሀዲዳቸውን ሳይስቱ መስመራቸውን ጠብቀው እየሄዱ መሆናቸውን የምናውቀው።
የ‹‹ኮሪደር›› ልማቱ በሚካሄድባቸው አምስት አካባቢዎች ላይ የሚታየው ግንባታ ብዙ ለውጦችን ሊያመጣ እንደሚችል አያያዙ በራሱ ያስታወቃል:: ግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተካሄዱ ናቸው፤ ልማቱ ከተጀመረ ከ45 ቀናት ብዙም ያልዘለለ ቢሆንም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች በሚገርም ፍጥነት እየተገባደደ ይገኛል::
በከተማዋ መሠረተ ልማት ብቻ አይደለም እየተገነባ የሚገኘው፤ የከተማዋን ገጽታ ያበላሹ ያረጁ ያፈጁ፣ ለከተማዋ ውበት ምንም አይነት እሴት ያልጨመሩ ይልቁኑም ውበቷን ያደበዘዙ ግንባታዎች በቅድሚያ ለነዋሪዎች ቤትና ቦታ በመስጠት እንዲፈርሱ ተደርጓል:: በዚህም ጥቂት የማይበሉ መንደሮች ጽድተው ሌላ ታላቅ ልማት ታጭተው አልሚዎችን እየተጠባበቁ ይገኛሉ::
ሌሎች ህንጻዎች ደግሞ በኮሪዲሩ ለሚገኙ አካባቢዎች በተቀመጠው የልማት አቅጣጫ መሠረት እድሳት እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተቀምጦ እድሳቱ እየተካሄደ ይገኛል:: በጣም ጠባብ የነበሩ የእግረኛ መንገዶች ለቀቅ እንዲሉ ተደርገዋል:: በተለምዶ ከምናውቃቸው የእግረኛ መንገዶች በተጨማሪ መንገድ አጠገብ የሚገኙ ህንጻዎች የታችኛውን ወለላቸውን የተወሰነ ክፍል ለእግረኛ መንገድ እንዲለቁ ተደርጓል::
ልማቱ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገበት የሚገኝና ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠርም የቻለ ነው:: ለ24 ሰዓት ለሰባት ቀናት እየተካሄደ የሚገኝ ግዙፍ ልማት፣ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል የፈጠረ ስለመሆኑ ልማቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው ርብርብ በሚገባ ያመለክታል:: በሥራ እድል ፈጠራው እንደ ሀገር እንደ ከተማ አስተዳደርም ለመሥራት ለታቀደው ሥራ አስተዋጽኦ ያበረክታል:: አካሄዱ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የሚለውን አባባል የሚያስታውስ ነው።
በኮሪደር ልማት ግንባታዎቹ እየተከናወነ ያለው ተግባር መሠረተ ልማትን ተቀናጅቶ ከመገንባት አኳያ ያለውን ሰፊ ክፍተት አጢኖ በቀጣይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ሁኔታን ሊፈጥር ይችላል:: የመንገድ ግንባታው ሲካሄድ ለስልኩም፣ ለኤሌክትሪኩም፣ ለውሃውም፣ ለፍሳሽ ማስወገጃውም መስመር የሚያገለግሉ መሠረተ ልማቶች በመሬት ውስጥ እንዲቀበሩ ተደርጓል:: እነዚህ መሠረተ ልማት ዘርጊ አካላት በተዘጋጁላቸው መሠረተ ልማቶች ኬብሎቻቸውንና የመሳሰሉት በመዘርጋት አገልግሎት መስጠታቸውን መቀጠል ይችላሉ::
ልማቱ በራሱ ከሕዝብ ለሚነሱ ቅሬታዎች ምላሽ የሚሰጥ ነው:: በተናጠል የመሠረተ ልማት ግንባታ ወቅት የውሃ መስመር ሲሰበር፣ የኤሌክትሪክ መስመር የስልክ መስመር ሲጎዱ በደንበኞች ላይ የሚደርሰውን የአገልግሎት መቋረጥና ያንን ለማስቀጠል የሚያጋጥማቸውን የመልካም አስተዳደር ችግር ይፈታል:: እንደ ከተማ አስተዳደር የተሻለና ዘመናዊ አሠራር ለመዘርጋት ብሎም የዘመነ አገልግሎት ለመስጠት ዓይን ከፋች ፕሮጀክት እንደሚሆን እምነቴ ነው::
በፕሮጀክቱ ላይ የሚደረገው ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር 24 ሰአትና ለሰባት ቀናት የመሥራት ባህልን በሌሎች ፕሮጀክቶችም ላይ እውን ለማድረግ ፕሮጀክቱ መልካም እድል ይፈጥራል:: ፕሮጀክት ጀምሮ እንዴት መጨረስ እንደሚቻል በተጨባጭ ማሳየት ከለውጡ ወቅት አንስቶ የተጀመረ ቢሆንም፣ ይህ ፕሮጀክት በበርካታ ደጆች ፣ መሥሪያ ቤቶችና አደባባዮች የሚያልፍ እንደመሆኑ ፕሮጀክት የሚመሩ አካላት ራሳቸውን እንዲመለከቱበት መልካም እድል ይፈጥራል::
ይህች ከተማ እየተከንባለሉ የመጡትን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ስታደርግ የቆየችውን ተግባር ከቁጥቁጥ በማውጣት በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን በመሥራት ለመፍታት መሥራት ውስጥ መግባት መጀመሯን ይህ ግዙፍ የኮሪደር ልማት ያመለክታል:: ልማቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች እየተገነቡ ያሉ መሠረተ ልማቶችና ለመገንባት የታቀዱ ሥራዎች ሲታሰቡ በእርግጥም ከተማዋ ስር የሰደዱ ችግሮቿን ለመፍታት ቆርጣ ተነስታለች::
ከተማዋ ሌሎች በርካታ የሰው ተኮር፣ የመሠረተ ልማት፣ የኑሮ ውድነትን ለማርገብ የሚረዱ ሥራዎችን እያካሄደች እንደምትገኝ ይታወቃል:: ሌሎች የመልካም አስተዳደር፣ የሰላምና ጸጥታ ሥራዎችም እየተካሄዱባት ይገኛሉ::
ለኮርደር ልማቱ የተሰጠው ትኩረትና በከፍተኛ ርብርብ እየተካሄደ ያለበት ሁኔታ ሌሎች የከተማዋን መሠረታዊ ችግሮች በከፍተኛ ርብርብ ለመፍታት መሥራት እንደሚቻልም ያስገነዝባል:: በከተማዋ የሚካሄዱ ልዩ ልዩ ተግባሮች በሚገባ የሚከታተላቸው የሚቆጣጠራቸው ቢያገኙ ምን ያህል ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከዚህ የኮሪደር ልማትና ቀደም ሲል ከተካሄዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አፈጻጻም መረዳት ይቻላል::
እንደሚታወቀው እንደ ሀገር መንግሥት በሀገሪቱ ከተሞች የተንሰራፋውን የኑሮ ውድነት ለማርገብ እየሠራ ይገኛል:: የግብርና ምርቶች በሸማቾች ማኅበራት በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ ለማድረግ ማህበራቱን ከአርሶ አደሮች ማህበራት ጋር በማስተሳሰር እየተሠራ ነው:: መሠረታዊ ሸቀጦች በድጎማ እንዲቀርቡ እየተደረገ ይገኛል::
ከዚህ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ መግቢያ በሮች አካባቢ በገነባቸው የግብርና ምርቶች መሸጫ ማእከላት በኩል የግብርና ምርቶች ለሸማቹ በቀጥታ የሚደርሱበትን ሁኔታ እየፈጠረ ነው:: ይህም ምርቶቹን ከደላሎች መዳፍ ውስጥ በማስወጣት አምራችና ሸማች ብቻ እንዲገበያዩ እድል የሚፈጥር አካሄድ ነው::
በምገባ መርሃ ግብር፣ ህብረተሰቡን ባለሀብቶችን ወዘተ፣ በማስተባበር አቅመ ደካሞችን፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች ለመደገፍ እየተሠራ መሆኑ ይታወቃል:: በከተማዋ በነዋሪዎች ላይ በኪራይ ዋጋ ጭማሪ የሚደርሰውን ግፍ ለማስቀረትም ችግሩን የሚፈታ የቤት ኪራይ አስተዳደርና አዋጅ አውጥቷል፤ አዋጁ መተግበር ሲጀምር የኑሮ ውድነቱን ለማረግብ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል::
በከተማዋ ሌሎች ለኑሮ ውድነት ምክንያት የሚሆኑ ችግሮች በስፋት ይስተዋላሉ:: መጀመሪያ የመቀመጪያዬን እንዳለችው ዝንጀሮ በከተማዋ በርካታ ስር የሰደዱ ችግሮች ቢኖሩም አስተዳደሩም የፌዴራል መንግሥቱም የከተማዋ መሠረታዊ ቁልፍ መሠረታዊ ችግር የሆነውን የኑሮ ውድነት ለመፍታት አሁንም አቅማቸውን አስተባብረው ሊሠሩ ይገባል:: ይህን ለማድረግ ደግሞ በኮሪደር ልማቱ አቅማቸው የታየ እንደመሆኑ በቀጣይ ደግሞ በእዚህ ችግር ላይ ርብርብ የሚደረግበትን ሁኔታ እውን እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ::
ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት የኑሮ ውድነቱን ለመፍታት ብዙ እየተሠራ ነው:: ከችግሩ ግዝፈት አኳያ ግን ግዙፍ ሥራዎች መሥራት ይጠይቃል:: በዚህች ሀገር በዚህች ከተማ ዋጋ የሚጨምርበት ምክንያት ኢኮኖሚያዊ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል:: ለዋጋ ንረቱ እሴት የማይጨምሩ እንደ ደላላ ያሉ አካላት፣ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች በምክንያትነት ሲጠቀሱ ይሰማል:: ይሄ መታወቁ ጥሩ ነው:: እነዚህን አካላት አደብ ማስገዛት ላይ ካልተሠራ ግን እስከ አሁን እየተደረገ ባለው መንገድ ብቻ የኑሮ ውድነቱን በዘላቂነት መፍታት አይቻልም:: የችግሩ ስፋት በኮርደር ልማቱ ልክ፣ ምናልባትም ከዚያ በላይ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግን ይጠይቃል::
ችግሩን በመሠረታዊነት ለመፍታት ለኑሮ ውድነት ምክንያት የሆኑትን ችግሮች በጥናት ላይ ተመሥርቶ በመለየት መፍትሄ ማመላከትና የኮሪደር ልማቱን ያህል አቅም ፈጥሮ ለተግባራዊነቱ መሥራት ያስፈልጋል:: የከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ስር የሰደዱ ችግሮች ለመፍታት በኮሪደር ልማቱ ቆርጦ መነሳቱን እንዳሳየ ሁሉ የኑሮ ውድነትንና የመሳሰሉትን ችግሮችም በተመሳሳይ አግባብ ለመፍታት ቁርጠኛ ሆኖ ለመሥራት ከወዲሁ መዘጋጀትም ይኖርበታል::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም