ስለ ሰላም ለመናገር ሳስብ ቀድሞ ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው ‹‹ሰላም ሰላም ፤ ሰላም ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ›› የተሰኘው የታዋቂውና አንጋፋው ድምፃዊ መሐመድ አሕመድ ዘፈን ነው:: ይህ ዘፈን ልክ እንደ ሀገራችን ብሄራዊ መዝሙር ሁሉም ይወደዋል፤ ያቀነቅነዋልም:: የሀገሩን ሰላም በመሻት ጥሪ የሚያቀርብበት ነው:: ድምጻዊው የሰላም ደወልን በጋራ ያስተጋባበት ድንቅ ግጥምና ዜማ ያለው ዘፈን::
በግጥሞቹ ዘመን ተሻግረን ስለኢትዮጵያ ሰላም እንድናስብ ያደርገናል:: መልካሙን ብቻ ተናጋሪና አሳቢ እንድንሆንም ያስገድደናል::
ዜማው ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለችበት ወቅት ሁሉ ይዜማል፤ በዚህም ስለሰላም እንድናስብ፣ ስለሰላም እንድንሰራ ሲደረግ ኖሯል:: ዛሬም እንደ ሀገር የዚህ ዘፈን ጭብጥ ያስፈልገናል::
በአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ሐዲስ ላይ እንደሰፈረውም፤ ሰላም ማለት ፍፁም ጤናን፣ እረፍትን፣ እርቅን፣ ፍቅርን አንድነትን፣ ደህንነትን፣ ተድላ ደስታን፣ ሰላምታን ያቀፈ ጽንሰ ሃሳብ ነው:: ይህም የሰላም ትርጉሙ ሰፊ መሆኑን እንመለከታለን:: በብያኔው ለተመለከቱት ሁሉ ስንል ለሰላም ልንሠራ ይገባናል::
ለእኛ ለኢትዮጵያውያን በተለይ ለአሁኑ ዘመናችን ሰላም እጅግ አስፈላጊ ነው:: እንደሚታወቀው ሀገራችን የኢኮኖሚ እድገትን እውን የሚያደርጉ፣ ሰላምና መረጋጋትን የሚያጸኑ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማስፈን የሚረዱ በርካታ ተግባሮችን እያከናወነች ትገኛለች::
ሰላም የኢኮኖሚ መሠረቷ፣ የፖለቲካ ሀዲድ እና የልማቷ መሽከርከሪያ ምህዋሯ ነው:: እናም ሰላም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አጀንዳዎቿ ጉልበት ኖሯቸው የተፈለገው ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ትልቅ አቅም ነው::
ሰላም ሰው ሲገናኝም ሆነ ሲለያይ ደጋግሞ የሚያነሳው የዘወትር ጾሎቱ፣ የሕይወቱ መመሪያው ነው:: ከሰላም ውጪ ምንም ሊያስብ አይችልም፤ ሁሉም በሰላም ማእቀፍ ውስጥ ነው::
ምንም እንኳ ቃሉና መሬት ላይ ያለው ነገር የማይገናኝበት ሁኔታ ቢስተዋልም፤ ሰላም ስለጠፋ፣ ጦርነትና ግጭት ስለተመላለሰ ስለሰላም አይነሳም ማለት አይቻልም:: ያጣነውን የጎደለንን ሰላም መልሰን ለማግኘት ሰላም፣ ሰላም እንላለን::፡
የሰላም ችግር በሃሳብ ልዩነት ካለማመን ሊመነጭ ይችላል:: ጦርነትና ግጭት ብቻ ሳይሆን አሉቧልታም ሰላምን ያናጋል:: በሀገራችን ሁከት እየተንሰራፋ፣ ጦር መስበቅ እየገዘፈ፣ ሰውን ለማጥፋት፣ ሀገርን ለማመስ የቃላት ፍትጊያው እየተፋፋመ ፣ ስደት እና ጉዳት እየተበራከተ ለመምጣቱ መንስኤው አሉታዊ ሃሳብ መንሰራፋቱ እንደሆነ ማስረጃ መጠቀስ አያሻንም:: ብዙ ማስረጃዎች አሉንና::
በቅርቡ በሰላም እጦት ሳቢያ ያሳለፍናቸው ችግሮች መልሰን እንድናይ ከሚጎሰመው የጦርነት ነጋሪትና በተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሚደርሱ ጥቃቶች የምንረዳውም ይህንኑ ነው:: ካሳለፍናቸው ችግሮች መማር አልቻልንምና ዛሬም በእነዚህ አሉባልታዎች እየተናጥን እንገኛለን::
‹‹ሞኝ ከራሱ፤ ብልህ ከሰዎች ይማራል›› ነበር ተረቱ:: እኛ ግን ከራሳችንም ሆነ ከሰዎች መማር አልቻልንም:: ትናንት ባደረግናቸው ጦርነቶች ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ሕጻናት ያለአሳዳጊ አዛውንቶች ያለጧሪና ቀባሪ ቀርተዋል፤ በርካታ ዜጎች በከፋ የርሃብ አለንጋ እንዲገረፉ እና እንዲረግፉ ሆነዋል:: ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸውንም ቤት ይቁጠራቸው::
ተማሪዎችም ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ የተደረጉባቸው ሁኔታዎች ጥቂት አይደሉም፤ መምህራንና ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች በሰላም እጦት ሳቢያ ለበርካታ ወራት ያለደመወዝ የሆኑበት ሁኔታ የችግሩ ስር የሰላም እጦት ነው::
በጦርነት ሀገርም ብትሆን ዜጎቿን ተነጥቃለች፤ በብዙ ቢሊዮኖች ብር የሚገመት ሀብት እና ንብረቷን አጥታለች:: በጦርነት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የወጣው ግዙፍ ወጪ ሲታሰብ በራሱ ጦርነት ምን ያህል አስከፊ እንደሆን ያመለክታል:: በዚህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገጽታዋ በእጅጉ እንዲበላሽ ተደርጓል::
ይህን ሁሉ መከራ ባየች ሀገር ውስጥ እንዴት ዳግም ጦርነት ይካሄዳል፤ መሞከርስ ነበረበት ወይ:: ለምን ከትናንቱ ችግራችን መማር አቃተን? ‹‹ሞኝ ከራሱ፤ ብልጥ ከሰው ይማራል›› ከሆነ ተረቱ እኛ ከየትኛው ምድብ ነን? መልሱን የሥነ ልቦናም ሆኑ ሌሎች ምሁራን የሚደርሱበት አይመስለኝም:: ለመሆኑ ሀገራችን ለእኛ አትበቃም ይሆን? መልሱን በዚህ ፍትጊያ ውስጥ ላሉ ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ‹‹ወግ ጠራቂዎች›› ልተወው::
አዳም እና የሄዋንን ልጆች በጎሳ እና በብሔር እየከፋፈሉ ልዩነቶች ማስፋት፣ ነገሮችን ማወሳሰብ ምን የሚሉት ፖለቲከኝነት ነው? በትናንት ታሪካችን ቀንድ እና ጅራት እየለጠፉ መጓተት ምን የሚሉት ፖለቲካ ነው?
ለእኔ አዋቂ ፖለቲከኛ ማለት በሰላም ውስጥ የሚገኙ እድሎችን ተጠቅሞ ኢትዮጵያ እየደከመችበት ያለችውን የጸና የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት በአለት መሠረት ላይ እንዲቆም ማድረግ ነው:: ለዚህ ተግባር እውን መሆን የራስን ድርሻ መወጣትም ነው::
ሰላም ዘላቂነት ያለው የፖለቲካል ኢኮኖሚ እድገት እንዲኖር ከማስቻሉም ባሻገር እንደ ሀገር ጠንካራ ተቋማት ለመገንባት አስተዋጽኦው የጎላ ነው:: አስተማማኝ የፖለቲካል ኢኮኖሚ እድገት ሲኖር ኅብረተሰቡም ስለሰላም የሚኖረው አመለካከት የተሻለ ይሆናል:: ይህም ኅብረተሰቡ ሰላምን ለማጽናት የሚያስችል አቅም በማጎልበት ፈተናዎች ቢያጋጥሙ እንኳን ያለ ምንም ችግር መፍታት ይችላል፤ ግጭት የሚፈታበት ችሎታ መገንባት ያስችለዋል::
ከዚህ አኳያም አሁን እንደ ሀገር አለያም እንደ ዜጋ ለሰላም ማድረግ የሚገባን ሰላም የኔ ጉዳይ ነው ብሎ መስራት ነው:: ለጦርነትና ግጭት ምክንያቶች በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር እና ጊዜ ከማጥፋት ይልቅ ሰላማዊ ዓለም ለመፍጠር መትጋት ይገባናል::
የሁሉንም ኢትዮጵያዊ አመለካከት ማስተናገድ መቻል ለሰላም የሚደረገውን ሩጫ ወይም ትግል በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ ያደርጋል:: ስለሆነም ሀገርን ከችግር ለመታደግ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ አመለካከቶች ፣ ተቋማትን አሠራር እና መዋቅሮችን በመፈተሽ ሁሉን አካታች የሆነ አስታራቂ ሃሳብ ሊቀርብ የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል:: በዚህም አካታች አስተሳሰቦችን ህብረተሰቡ እንዲላበስ በማድረግ በዜጎች መካከል ከፍ ያለ መተማመንን መፍጠር ያስፈልጋል::
ለሀገር ይበጃል የተባለንም ማንኛውንም ሃሳብ አዳምጦ ተግባራዊ ማድረግም ሌላው የዘላቂ ሰላም ማምጫ መንገድ ነው:: በአንድ ሀገር ብዙ ጥፋትን ያስከተለ ጦርነት ወይም ግጭት በሀገሪቱ የተለያዩ ቡድኖች መካከል ሊቀሰቀስ ይችላል:: የጦርነቱ ጦስም በሀገሪቱና በሕዝቧ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ሊሆንም ይችላል::
ለእዚህ ጦርነት መፍትሄው እርቅ ማድረግ ከሆነ እርቅ ማድረግ ይገባል፤ እርቅ ደም ያደርቅ አይደለስ የሚባለው:: ውይይት ማድረግ ካስፈለገም መወያየት:: ጦርነቱን አቁሞ ለጦርነቱ ምክንያት የሆኑትን ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ውስጥ መግባት መቼም ቢሆን ለድርድር አይቀርብም::
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው:: ይህ ስምምነት ለሰላም የተከፈለ ትልቅ ዋጋ ነው:: ጦርነቱ በሰላም ስምምነት እንዲቆም ተደርጎ ችግሮች በሰላማዊ አማራጭ እየታዩ ናቸውና::
ለእኛ ችግር ከእኛ በላይ መፍትሄ አፍላቂ የለም:: ከራሳችን ጽንፈኛ ፖለቲከኞች በተጨማሪ በርካታ የውጭ ሃይሎች አሁንም ከጦርነት አዙሪት እንድንወጣ አይሹም:: በቃላት ጦራቸው ያልተባሉ ነገሮችን በማቀባበል ግብ ግብ ውስጥ እንድንቆይ ያደርጉናል::
ለእኛ ኢትዮጵያውያን ሰላም የመውጣት መግባታችን ዋስትና የሀገራዊ ልማታችን ስኬት ቁልፍ መሣሪያ ነው:: ለእዚህ ታላቅ መሣሪያ ዘላቂነት ከእያንዳንዱ ዜጋ አንስቶ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ ፣ ሕዝብ በሙሉ መሥራት ይኖርበታል::
ሰላም ለማምጣት ጦርነት አማራጭ ስለአለመሆኑ መንግሥት በተደጋጋሚ አስገንዝቧል:: ጦርነት የመጨረሻው አማራጭ ነው፤ እኛ ደግሞ ብዙ አይተናልና እዚያ ደረጃ ላይ መድረስ የለብንም:: የጦርነት አማራጭ አጥፊ አውዳሚ መሆኑን ተረድተናል፤ መፍትሄው አሁን የሰላም አማራጭ መሆኑን ተገንዝብን ለተግባራዊነት መሥራት ይኖርብናል::
ዘላቂ ሰላም በማስፈን ቁሳዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሥነ ልቦናዊም ሆነ ማኅበራዊ ፍላጎቶችን ማሟላት ይቻላል:: ለእዚህ ሰላም እውን መሆን በማኅበረሰቡ ውስጥ ሥር ሰዶ የሚገኘው የሰላም ወዳድነት እሴት እንዲጎለብት አጥብቆ መስራት ያስፈልጋል:: ሰላም!!
ክብረ መንግስት
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም