ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው በፋሽስት ጣልያን የተፈጸመባትን ወረራ በመቀልበስ ድል ያደረጉበት 83ኛ ዓመት ትናንት ተከብሯል:: ዓድዋ ላይ በኢትዮጵያውያን ከደረሰባቸው ሽንፈት አልማር ያሉት ፋሽስቶች ጣልያኖች ለ40 ዓመታት ቂም አርገዘው በድጋሚ ኢትዮጵያን ቢወሩም፣ በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ለሁለተኛ ጊዜ የሽንፈትን ጽዋ በግድ እንዲጎነጩት ተደርገዋል::
ጣልያኖች በዓድዋ ጦርነት ወቅት ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቀውና የሠለጠነ ሠራዊት ይዘው ወደ ጦርነቱ በመግባት ኋላቀር መሣሪያ በታጠቁት ኢትዮጵያውያን ድል የተደረጉት:: ፋሽስት ጣልያንም ከዓድዋ ጦርነት ከ40 ዓመት በኋላ በቂም በቀል ተነሳስተው የጦር አውሮፕላኖችን ጨምሮ ዘመናዊ መሣሪያ እና በቅኝ ግዛት ከያዟቸው ሀገሮች ጭምር አያሌ ሠራዊት በመልመል ኢትዮጵያን ወረዋል::
ይህን የጣልያኖች ወረራ ለመመከት ኢትዮጵያውያን ማይጨው ላይ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል:: ይሁንና ፋሽስቶቹ በዓለም መንግሥታት የተከለከለውን የመርዝ ጋዝ ጭምር በመጠቀም ኢትዮጵያውያንን በገዛ ምድራቸው በመጨፍጨፍ ሀገሪቱን በመውረር አምስት ዓመታትን በኢትዮጵያውያን ላይ ግፍ ፈጽመዋል::
ፋሽስቶቹ የመርዝ ጋዝ በመጠቀም ብቻ አይደለም ኢትዮጵያውያንን በግፍ የጨፈጨፉት:: ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለጠላት አንበረከክም በማለታቸው በአዲስ አበባ ከተማ የካቲት 12 ቀን በኢትዮጵያውያን ላይ በፈጸሙት ጭፍጨፋ ከ30 ሺ በላይ ንጹኃን ኢትዮጵያውያን ተሰውተዋል:: ይህ በዶማና በአካፋ ጭምር የተፈጸመ ጭፍጨፋ አድማሱን ከአዲስ አበባ እስከ ደብረ ሊባኖስ በማስፋት አያሌ ንጹሃን ኢትዮጵያውያንመየግፍ ሞት እንዲሞቱ ተደርጓል:: በአምስት ዓመቱ ወረራ ፋሽቶችን አሻፈረኝ ባሉ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው ግፍ ተቆጥሮ ተሰፍሮ አያልቅም::
ኢትዮጵያውያን ግን ለዚህ የጣልያን ወረራ እና ላደረሰባቸው ግፍ አልተንበረከኩም፤ ይልቁንም ትግላቸውን አቃጣጠሉት እንጂ:: አምስት ዓመታትን በዱር በገደል ተጋድሎ አደረጉ፤ ሌሎች ደግሞ ጠላትን በመሰለል ለወገን ጦር መረጃ በማቀበል የበኩላቸውን ተወጡ፤ በዚህ ሁሉ ተጋድሏቸው ኢትዮጵያውያን ጠላትን መግቢያ መውጫ በማሳጣት ተረጋግቶ እንዳይቆይ አደረጉት::
በዚህም ቅኝ ገዥዎች በመላ ዓለም ረጅም ዓመታትን መቆየትና ያሰቡትን ማሳካት ቢችሉም በኢትዮጵያ ግን ይህን ማድረግ እንዳይችሉ ማድረግ ተችሏል:: ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ፋሽስቶች ላይ ባደረሱባቸው አሳፋሪ ሽንፈት ፋሽቶቹ ሀገሪቱን ጥለው ወጡ::
በዚህም ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ነጻነት ለመጠበቅ፣ ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር የቱንም ያህል ተደራጅቶና ታጥቆ የመጣን ኃይል ድል ከማድረግ እንደማይመለሱ በዓድዋ ላይ የሠሩትን ታሪክ በፋሽስት ጣልያን ላይም በመድገም ማንነታቸውን ለዓለም በድጋሚ ማሳየት ችለዋል::
ኢትዮጵያውያን ይህን ሁሉ ድል የተጎናጸፉት በሀገራቸው ጉዳይ የማይደራደሩ፣ በአማኑ ቀን የቱንም ያህል ልዩነት ቢኖራቸው በሀገር ጉዳይ ግን አንድ ሆነው የሚነሱ በመሆናቸው ነው:: በሀገር ጉዳይ እግሩን የሚጎትት ፣ ማቄን ጨርቄን የሚል ኢትዮጵያዊ የለም:: ሀገር በጠራችው ወሳኝ ወቅት የቤተሰብም ሆነ ሌላ የግል ጉዳዩን ከሀገራዊ ጉዳይ በጭራሽ በልጦበትም አያውቅም::
ከዚያም ወዲህ ጠላቶቻቸው በጦር ሜዳ ውሎ ያጡትን ድል በሌሎች መንገዶች ለመጎናጸፍ ሞክረዋል፤ በሀገር ውስጥ ልዩነት እንዲፈጠር ብዙ ሠርተዋል፤ ያ የፈለጉት ልዩነት ተፈጥሯል ሲሉም ሀገሪቱ ላይ በተለያዩ መንገዶች ጥቃት እንዲፈጸም ሲያደርጉ እነሱም በተለያዩ የእጅ አዙር መንገዶች ሲፈጽሙ ኖረዋል::
ይህን ዓይነት ጥቃቶች በሀገሪቱ ላይ በተደጋጋሚ ተፈጽመው በተደጋጋሚ ከሽፈዋል:: ይሁንና የፈለጉትን ግን አላሳኩም:: የኢትዮጵያውያን አንድነት በልዩነት ውስጥ ያለ እንደመሆኑ ጠላት ኢትዮጵያውያኑ ተቃቅረዋል፤ ይሄኔ ነው መውጋት ብሎ ሲነሳም አንድ ሆነው የሚያገኛቸው ለእዚህ ነው:: በዚህ ሁሉ ኢትዮጵያውያን የቱንም ያህል ልዩነት ቢኖራቸው በሀገር ጉዳይ አንድ መሆናቸውን ለጠላቶቻቸው በተጨባጭ ሲያሳዩ ኖረዋል::
የጦር ሜዳም ሆነ የእነዚህ ድሎቻቸው ምስጢር ኅብረ ብሔራዊ አንድነታቸው ነው:: ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህን አንድነታቸውን የልማታቸው ሁነኛ መሣሪያ አድርገውታል:: ለብዙ ችግር የዳረጋቸው ዋና ጠላታቸው ድህነት መሆኑን በሚገባ ተገንዝበው የጦር ሜዳ ድላቸው ምስጢር የሆነውን አንድነታቸውን አስተባብረው ድህነትን ድል ለማድረግ ዘምተውበታል::
በዓባይ ግድብ ግንባታ ላይ ያሳዩት ርብርብም ለእዚህ ዋናው ማሳያ ይሆናል:: ሀገሪቱ የዓባይ ግድብን ለመገንባት የሚረዳ ፋይናንስ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ማግኘት እንደማይቻል አስቀድማ ተገንዝባ ሕዝቧ ላይ አጥብቃ ሠርታለች:: በአንዳንድ የተፋሰሱ ሀገሮችና አጋሮቻቸው ጫና የተነሳ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድር ማግኘት እንደማይቻል ተገነዝባ ግንባታውን በኢትዮጵያውያን መዋጮ ለማካሄድ በቁርጠኝነት በመሥራቷ ግድቡን በራስ አቅም እውን ማድረግ ተችሏል::
ይህ በዓለምም በአፍሪካም ደረጃ ግዙፍ የተባለ ግድብ የኢትዮጵያውያንን የማድረግ አቅም በልማቱም መስክ ማሳየት ያስቻለ ሆኗል:: በስንዴ ልማት፣ በዲጂታላይዜሽንና በቱሪዝም መዳረሻዎች ግንባታም እየተመዘገቡ ያሉ ድሎችም የኢትዮጵያ ትንሳዔ ቅርብ መሆኑን የሚመሰክሩ ናቸው:: ቀጣይም የኢትዮጵያ አቅም የሕዝቧ አንድነት ነው:: ይህን አንድነት ይበልጥ በማጠናከር አሁንም በድህነት ላይ የተጀመረውን ርብርብ ማጠናከር ይገባል:: ግዙፍ አውሮፓዊ ሃይልን በተደጋጋሚ ድል ያደረገ አንድነት ድህነትን ለመገርሰስ የሚሳነው አይሆንም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም