ውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይከሰቱ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራውን በቅንጅት መሥራት ይገባል

– በ297 ወረዳዎች የኮሌራ በሽታን መቆጣጠር ተችሏል

አዲስ አበባ፡- የክረምት ወራትን ተከትሎ ውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይከሰቱ የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራው በቅንጅት ሊሠራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ በ297 ወረዳዎች የኮሌራ በሽታን መቆጣጠር መቻሉም ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የክረምት ወራትን ተከትሎ ውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይከሰቱ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

ኮሌራ፣ ወባና ኩፍኝ በሽታዎች በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የመቆጣጠርና የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኮሌራና ሌሎች ውሃ ወለድ በሽታዎችን ከመቆጣጠር አንጻር የህክምናና ሌሎች ቁሳቁሶች ቶሎ እንዲደርሱ ክትትል የማድረግ፣ ህብረተሰቡን የማስገንዘብ እና የመጸዳጃ ቤት ሽፋንና አጠቃቀም ዝቅተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች ላይ የማሻሻል ስራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

በድርቅ ምክንያት የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ዝቅተኛ በሆነባቸው አካባቢዎችም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የንጹህ መጠጥ ወሃ አቅርቦትን የማሻሻል ስራ በመሰራቱ ኮሌራ በተከሰተባቸታ በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች መቆጣጠር የተቻለ ሲሆን፤ በምስራቅ ኦሮሚያ በሶማሌና አፋር ክልሎች የተወሰኑ ወረዳዎች ላይ ያለ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኮሌራ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በተሰራው የመከላከል ስራ በ297 ወረዳዎች ላይ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር መቻሉን ገልጸው፤ በሽታው በባህሪው ተላላፊ በመሆኑ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን በማስፋፋት እና ውሃን አክሞ በመጣጣት ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ይገባል ብለዋል፡፡

የወባ በሽታን ለመከላከል ለማህበረሰቡ ተደራሽ የተደረገውን አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀም ግንዛቤ የማስጨበጥ እና የወባ ምልክት የታየባቸውን ሰዎች በመለየት ህክምና እንዲያገኙ የማድረግ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡

ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑና ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በህበረተሰብ ተሳትፎ የማጽዳት፣ የኬሚካል ርጭት፣ ለወባ ምርመራ የሚያገለግሉ የህክምና ቁሳቁሶችን የማሰራጨት ስራ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

እንደ ዶክተር መሳይ ገለጻ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በቤኔሻንጉል እና በምእራብ አማራ፣ ክልሎች ላይ የወባ በሽታ የጨመረበት ሁኔታ በመኖሩ የመከላከል ስራው በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኩፍኝ በሽታን የመደበኛ ክትባትን ማጠናከር እና ተጨማሪ የክትባት ዘመቻ በመደረጉ ከ320 በላይ ወረዳዎች ላይ መቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል፡፡ መደበኛ ክትባትን የማጠናከርና የተማሙ ህጻናት ህክምና እንዲያገኙ በስፋት ይሰራል ብለዋል፡፡

ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን ማንቃት ወሳኝ ነው ያሉት ዶክተር መሳይ፤ የግልና የአካባቢ ንጽህናን፣ የምግብና መጠጥ ውሃ ንጽህናን መጠበቅ እንደ ኮሌራ ያሉ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጠቀሜታዉ የጎላ ነው ብለዋል።

የክረምት ወራትን ተከትሎ ውሃ ወለድ በሽታዎች እንዳይከሰቱ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You