በዘጠኝ ወራት ከቡና ምርት 835 ሚሊዮን 230 ሺህ ዶላር ገቢ ተገኝቷል

– ከ174 ሺህ 596 ቶን በላይ ቡና ውደ ውጭ ተልኳል

አዲስ አበባ፡- በ2016 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ከቡና ምርት 835 ሚሊዮን 230 ሺህ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ በዘጠኝ ወራት ከ174 ሺህ 596 ቶን በላይ የቡና ምርት ወደ ውጭ ሀገራት መላኩም ተገልጿል፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በ2016 በጀት ዓመት ከ 174 ሺህ 596 ቶን በላይ ቡና ውደ ውጭ ተልኮ 835 ሚሊዮን 230 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡

በዘንድሮ ዓመት በዘጠኝ ወራት የተገኘው ገቢ ቀደም ባሉት ዓመታት ከተገኘው አንጻር የተሻለ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተው፤ የቡና ምርት ገቢን ለማሳደግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የማሻሻያ ስራ ተሰርቷል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በተሰሩ የሪፎም ስራዎች የቡና ምርት ገቢ ወደ ቢሊዮን ዶላር ማደጉን ጠቁመው፤ ባለፈው ዓመት ከአንድ ነጥብ 33 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ በዘንድሮ ዓመት አንድ ነጥብ 75 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ በስፋት እየተሰራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በዘንድሮ ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ መውረድ እና ከወደብ ጋር ተያይዞ በቀይ ባህር አካባቢ የተፈጠረው ችግር በቡና ግብይት ላይ ማነቆ እንደነበር አንስተዋል፡፡

ከወደብ ጋር ተያይዞ ላጋጠመው ችግር የቡና ምርት ወደተለያዩ ሀገራት በመኪና እንዲጓግዝ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል። የቡና ምርት በስፋት ሲገኝ የገበያ መውረድ ያጋጥማል፤ ስለዚህ ስፔሻሊቲ ቡና በስፋት ለመላክ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ሻፊ እንዳስታወቁት፤ በዘጠኝ ወራት ከነባር የቡና ምርት መዳረሻዎች በተጨማሪ አዳዲስ ገበያዎችን የማፈላለግ ስራ ተከናውኗል። የኢትዮጵያ ቡና የመግዛት ድርሻቸው እስከ 10 ባለው ደረጃ ያልነበሩ ሀገራት፤ ከአንድ እስከ 10 ባለው ደረጃ መቀላቀል ችለዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የተባበሩት አረብ ኤምሬት፣ ሱዳን እና ቻይና ቀደም ብሎ የኢትዮጵያን ቡና በመግዛት ከአንድ እስከ 10 ባለው ደረጃ ያልነበሩ ሀገራት ሲሆኑ፤ በዘጠኝ ወራት ቻይና ሰባተኛ፣ ሱዳን ስምንተኛ እና አረብ ኤምሬት ዘጠነኛ ደረጃ በመያዝ የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ሆነዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፤ ከዚህ በፊት የገበያ ሰንሰለት መርዘም፤ ቡና በእጅ ስለሚነካካ ገዚዎች በሚፈልጉት ደረጃ ጥራቱ የተጠበቀ ምርት ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ በመሃል ያለውን ሰንሰለት በማሳጠር የቡና አቅራቢና ሻጭ በቀጥታ እንዲገናኙ ተደርጓል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም አርሶአደሮች በማህበር ተደራጅተው በቀጥታ ቡና ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ የሪፎርም ስራ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You