“የንግድ መመሪያው በሁለቱ ሀገራት የሚደረገውን የንግድ ትብብር ለማሳደግ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል” – በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደር ጆርጅ ኦሬና

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ባለሀብቶች በተለያዩ የንግድ ዘርፎች እንዲሳተፉ ያጸደቀው መመሪያ የሁለቱን ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ለማሳደግ ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደር ጆርጅ ኦሬና ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከኬንያ አምራቾች ማህበር በጋራ ያዘጋጁት የንግድና ኢንቨስትመነት ፎረም ሰሞኑን ተካሂዷል።

አምባሳደር ጆርጅ ኦሬና በወቅቱ እንደገለጹት፤ በቅርቡ በኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ባለሀብቶች በወጪ፣ በገቢ፣ በጅምላና በችርቻሮ ንግድ እንዲሳተፉ የጸደቀው ሕግ የኢትዮጵያን እና የኬንያን የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር ለማሳደግ ትልቅ እድል ይፈጥራል፡፡

የውጭ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የሪልስቴት ገበያን ጨምሮ፤ በተለያዩ የንግድ መስኮች እንዲሳተፉ የተሰጠውን እድል እንደ በጎ ርምጃ እንደሚመለከቱት አስረድተዋል፡፡

የተደረገው ማሻሻያ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የግብይት ሂደት ለማሳደግ ጥሩ አማራጭ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ የንግዱ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ምን አይነት ዕድሎች እንዳሉ እንዲመለከትና ያንን እድል ለጋራ ጥቅም ለማዋል ያስችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች በኬንያ ያሉ የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እንዲመረምሩ ጥሪ ያቀረቡት አምባሳደሩ፤ የኬንያ ኢንቬስተሮች ደግሞ በኢትዮጵያ ያሉትን የገበያ ዕድሎች እንዲመለከቱ እንደሚያበረታቱ ጠቁመዋል። ይህም በሁለቱ ሀገራት ያለውን የገበያ አቅም በጋራ ለመጠቀም ያስችላል ብለዋል፡፡

አምባሳደር ጆርጅ ኦሬና እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ያላቸው ግንኙነት ኬንያ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከመውጣቷ አስቀድሞ ነው፡፡ ኬንያ ነጻ ሀገር ለመሆን ባደረገችው ጥረት የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

ኬንያ ነጻ ሀገር ከሆነች በኋላም ሁለቱ ሀገራት በመከላከያ፣ በንግድናኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ በፍልሰትና በተለያዩ ጉዳዮች ስምምነት ተፈራርመው በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት በየካቲት ወር የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሰባት ጉዳዮች ላይ የመግባቢያ ስምምነት ማድረጋቸውን የገለጹት አምባሳደሩ፤ በዚህም የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚያግዙ ስምምነቶች መደረጋቸውን አመላክተዋል።

ሁለቱ ሀገራት የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና አባል እንደመሆናቸው አሰራሩን በመከተል እንዴት የንግድ እንቅስቃሴያቸውን ማሳደግ እንደሚቻል፣ በሞያሌ በኩል ለሚደረገው ንግድ ማነቆ የሆነው ቢሮክራስ የመብዛት ሁኔታ ለመቀነስና ያሉትን መሰረተ ልማቶች ለማዘመን ስምምነት ተደርጓል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

እ.አ.አ. በ2012 የኢትዮጵያ እና የኬንያ መሪዎች በንግድ፣ በመሰረተ ልማት፣ በምግብ ደህንነትና በዘላቂነት አብሮ ለመኖር በሚያስችሉ አራት ጉዳዮች ላይ በተለየ መልኩ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፤ ይህን ስምምነት ለማጠናከር በተጨማሪም መግባባት ተደርሷል ብለዋል፡፡

አምባሳደሩ እንዳስታወቁት፤ የተደረጉ ስምምነቶች ሁሉ የሁለቱን ሀገራት ትብብር ከማሳደግ ባለፈ ለንግድ እንቅስቃሴ ምቹ እድል የሚፈጥሩ ናቸው።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You