በቀደምት አርበኞች ለተፈጸሙ የድል ታሪኮች ተገቢውን እውቅናና ክብር መስጠት ይገባል

አዲስ አበባ፦ በቀደምት አርበኞቻችን ለተፈጸሙ ታላላቅ የድል ታሪኮች የአሁኑ ትውልድ ተገቢውን እውቅናና ክብር መስጠት ይኖርበታል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡ 83ኛው የአርበኞች የድል በዓል “በሀገር ፍቅር አርበኝነት የተገኘ ድል” በሚል መሪ ሃሳብ በአራት ኪሎ የድል ሐውልት በተለያዩ ሁነቶች ትናንትና ተከብሯል፡፡

በክብረ በዓሉ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንዳመለከቱት፤ በቀደምት እናትና አባት አርበኞቻችን ለተፈጸሙ ታላላቅ ጀብድና የድል ታሪኮች የአሁኑ ትውልድ ተገቢውን እውቅናና ክብር መስጠት ይኖርበታል።

ጥንታዊ አርበኞች በዱር በገደል ፋሽስቱን ተዋግተው በሕይወት መስዋዕትነት የሀገራችንን ሉዓላዊነት አስከብረዋል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ አርበኞች ደማቸውን አፍሰው አጥንታቸውን ከሰክሰው ያስገኙት ድል በመሆኑ መጪው ትውልድ ታሪኩን በልኩ እንዲያውቅ ማድረግ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

አርበኞች በአንድነትና በሀገር ፍቅር ስሜት ወራሪው ኃይል ዳግም በውርደት እንዲመለስ በማድረጋቸው ውለታን የምናውቅ፣ የምናክብርና የምንዘከር ሰዎች በመሆን ድሉን ሕያው ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እንዳመለከቱት፤ የድል ታሪኩ ይበልጥ የሚጎላው ሕዝቡ የጋራ ታሪኩን በሚገባው ልክ ሲያውቅ፣ ሲስማማበትና ለታሪክ ተመራማሪዎች እንዲሁም ባለሙያዎች ተገቢው እውቅና ሲሰጥ ነው።

ታሪክን ከማክበር ባለፈ የሁሉ መሰረት የሆነውን ሰላም መገንባት መንከባከብና ሰላምን ሊያሳጡ የሚችሉ ነገሮች ሲታዩ ለመፍታት መረባረብ ሁሉም ሊተገብረው የሚገባ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል። ሰላም መተኪያ የሌለው ካመለጠ ደግሞ ለመመለስ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ሁላችን ለሰላም መፈጠር መስራት ይጠበቃል ሲሉ ፕሬዚዳንቷ መልዕክት አስተላልፈዋል ።

በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የሰላም እጦቶች እንቅልፍ ሊነሱን ይገባል ያሉት ፕሬዚዳንቷ ፤ ለሀገርና ለሕዝቦች ሰላም ሁሉም አካል ቅድሚያ መስጠት አለበት ብለዋል። የድል ታሪኩን ስናስብ ኢትዮጵያ የጦርነት ታሪክ የሚነገርባት ሀገር ብቻ ሳትሆን ሊወር የመጣን ጠላት በድል የምናሸንፍበትና እድገታችንን የምናፋጥንበት ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው፤ የድል በዓሉን ስናስብ በሀገር ፍቅር መስዋትነት የተገነባውን ሰላምና ነፃነት በመንከባከብና የተጀመሩ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል መሆን አለበት ብለዋል፡፡ ዛሬ ያገኘናት ሰላምና ክብር በአርበኞቻችን ደምና አጥንት የተገኘ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ መጪው ትውልድ የኢትዮጵያን እድገት በሚያፋጥኑ ጉዳዮች ላይ አሳታፊ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

በመከላከያ የሰው ሀብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ሃጫሉ ሸለመ በበኩላቸው፤ በዱርና በገድል የከተቱ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በጠንካራ የአንድነት መንፈስ ወራሪውን ፋታ በማሳጣት ለቆ እንዲወጣ አድርገው የተከበረችና የታፈረች ኢትዮጵያን ማስረከባቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው የግዛት አንድነትና ነፃነት የማይደራደሩ ሕዝቦች መሆናቸውን የተገኘው ድል ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ መከላከያ ሠራዊትም የጀግኖች አርበኞችን እሴት ተላብሶ ለሕዝቦች ደህንነት እየተዋደቀ ያለ ሠራዊት ነው ብለዋል።

ሠራዊቱ የሀገር ሰላም አስተማማኝ እስኪሆን ድረስ የሚከፍለውን ዋጋ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። በክብረ በዓሉ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ወይዘሮ ሳሃለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች የተገኙ ሲሆን ከንጋቱ 12 ሰዓትም ለበዓሉ ክብር 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል፡፡

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You