“መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋልጠናል”- በጅማ ዞን የማና ወረዳና አካባቢው ነዋሪዎች

“ግንባታውን ለማጠናቀቅ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና የወሰን ማስከበር ፈታኝ ሆኗል”- በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የጅማና አካባቢው ቅርንጫፍ

ጅማ፡- ከመረዋ- ሶሞዶ ሰቃ -ሊሙ መገንጠያ የሚወስደው መንገድ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋልጠናል ሲሉ አስተያየታቸው ለኢፕድ የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታቸውን አቀረቡ።

ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና የወሰን ማስከበር ችግር ፈታኝ እንደሆነበት በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የጅማና አካባቢው ቅርንጫፍ አስታውቋል።

በጅማ ዞን የማና ወረዳ የሰሞዶ ቀበሌ ሊቀመንበር ናዚፍ አባ መጫ እንደገለጹት፣ የቀበሌው ነዋሪ ከፍተኛ የመንገድ መሰረተ ልማት ጥያቄ ያለበት በመሆኑ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታው ሲጀመር ማህበረሰቡ ካሳ ሳይከፈለው በራሱ ፍቃድ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሮ ነበር።

አሁን ላይ የመንገዱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ተገንብቶ ባለመጠናቀቁ ማህበረሰቡ ከፍተኛ ቅሬታ እያሰማ መሆኑን ጠቁመው፤ ላለፉት ሶስት ዓመታት ግንባታው ተስተጓጉሎ መቆየቱንና የካሳ ክፍያ በአግብቡ ባለመከፈሉ ማህበረሰቡ ቅሬታ እያቀረበ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በጅማ ዞን የሊሙ ኮሳ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ህንድያ አባ ፊጣ በበኩላቸው፤ የመንገድ ግንባታው በመጓተቱ ነፍስጡር እናቶች ወደ ጤና ጣቢያ ሂደው እንዳይወልዱ እንቅፋት ፈጥሯል። መንገዱ ግንባታ ሲጀመር የነበረው ደስታ አሁን ላይ ደብዝዟል። ስለዚህ ችግሩን በመረዳት በቶሎ ተገንብቶ ማህበረሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን እንዲያከናውን ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

የማና ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሰይፉ አባግዴ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህበረተሰቡን የመልማትና የማደግ ፍላጎት አይተው ያስጀመሩት መንገድ በመሆኑ ይህን ያህል ይጓተታል ብለን አልጠበቅንም ሲሉ ተናግረዋል። አሁንም ችግሩን በማየት በአፋጣኝ እንዲገነባና ማህበረሰቡ ካለበት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንዲላቀቅ የሚመለከተው አካል ምላሽ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የጅማና አካባቢው ምክትል ስራ አስኪያጅ አለማየሁ ኪሮስ (ኢ/ር)፤ ግንባታውን በተያዘው ጊዜ ለማጠናቀቅ የወሰን ማስከበር ስራና አካባቢው ላይ የሚጥለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ፈተና ሆኗል ብለዋል። ይህም ኮንትራክተሩ ስራውን በሚፈለገው መጠን እንዳያከናውን አድርጐታል። ችግሩን የመንገዶች አስተዳደር በመረዳት የግንባታ የስራ ፕሮግራሙን እንዲቀየር በማድረግ የምሽት ስራ እንዲሰራ አድርጓል ሲሉ አስረድተዋል።

የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ በ2011 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ መጀመሩን አስታውሰው፤ ውል የወሰደው ኮንትራክተር ስራ ቢጀምርም ዓመታት የመንገዱ ግንባታ ተስተጓጉሏል፤ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ባደረገው ግምገማ ኮንተራክተሩ ያለው አቅም በሚፈለገው ልክ አልነበረም ብለዋል።

የነበሩበትን ፈተናዎች በመለየት ከፍተኛ አመራሩ በወሰደው ውሳኔ ከሁለት ሶስት ዓመት በኋላ አማካሪ ድርጅት በመቀየር አሁን ላይ የተሻለ አፈጻጸም አሳይቷል ሲሉ ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት ሶስትና አራት አመት ያሳለፈው ጊዜ የነበረው ግንባታ በቀን ስራ ብቻ ነበር ያሉት አቶ አለማየሁ፣ በዚህ ዓመት ብቻ 21 በመቶ የሚሆነውን የአስፓልት ንጣፍ ግንባታ ማጠናቀቅ እንደተቻለ አመላክተዋል።

እንደ ምክትል ስራ አስኪያጁ ገለጻ፣ አጠቃላይ የመንገዱ የሲቪል ግንባታ ከዚህ በፊት ካለበት በመሻሻል 43 በመቶ ደርሷል።

በዚህ ዓመት የተያዘው እቅድ ግንባታውን 50 በመቶ ማድረስ ሲሆን፤ ቀሪውን ግንባታ በሚቀጥለው ዓመት በማጠናቅቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እቅድ ተይዞ እየተገነባ መሆኑን አስረድተዋል።

የመንገዶች አስተዳደርም ፕሮጀክቶችን በቅርበት የሚከታተልበት አሰራር በመዘርጋት በጅማ ቢሮ ከፍቶ ክትትል እያደረገ መሆኑን ምክትል ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው ዋይት ናይት የሚባል አማካሪ ድርጅት በአሾሼትድ ወይም የተባበሩት የሚባል ሀገር በቀል ድርጅት ተቀይሮ የማማከር ስራውን እያከናወነ ሲሆን ፤ ይህም በቀን ብቻ የነበረውን ግንባታ በማታ ጭምር እንዲሰራ አስችሏል ብለዋል።

የመንገዱ ግንባታ ሲጀመር ከቻይናው ሲቲጂ ግሩፕ ስራ ተቋራጭ ውል ወስዶ ግንባታ እያከናወነ ሲሆን የፕሮጀክቱ በጀት ሁለት ነጥብ ሁለት ሰባት ቢሊዮን ብር እንደነበር አንስተዋል።

ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ነዋሪዎች ቅሬታ እንዳላቸው የገለጹት ምክትል ስራ አስኪያጁ፣ ከዚህ በፊት ለፕሮጀክቱ መጓተት አንዱ ችግር የነበረው በፊት ተገምተው የቆዩ ሰነዶችን ክፍያ በመፈጸም የግንባታ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል። ካሳ ያልተከፈለበት አካባቢ ግምት እየተሰራ ወደ ዋና መስሪያ ቤት በመሄድ ክፍያ ይፈጸማል ሲሉ አስረድተዋል።

የካሳ ክፍያ ተከፍሏቸው አነሰን ብለው እንዳልተከፈላቸው ቅሬታ የሚያቀርቡ ነዋሪዎች መኖራቸውን ገልጸው፤ ነገር ግን ካሳ ክፍያ ሳይክፈል የተነሳ ህብረተሰብ የለም። ቅሬታ ካለ ግን ከአካባቢው ማህበረሰብ የተውጣጡ የቡድን አባላት ያሉት የቅሬታ ሰሚ ችግሩን አይቶ ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።

በጅማና አካባቢው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከተጀመሩ ስድስት የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል 94 ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመረዋ- ሶሞዶ ሰቃ- ሊሙ መታጠፊያ የመገነባው መንገድ አንዱ ሲሆን፤ 43 በመቶ የደረሰውን ግንባታ በ2017 ዓ.ም በሚያዝያ ወር ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው።

ሞገስ ተስፋና ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You