በኦሮሚያ 3 ሺህ 953 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ለአገልግሎት ውለዋል

አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ ሦስት ሺህ 953 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት ላይ መዋላቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በክልሉ በበጀት ዓመቱ ሦስት ሺህ 410 ትምህርት ቤቶችን ለማደስ ታቅዶ አራት ሺህ 627 ትምህርት ቤቶች ላይ የማሻሻያ ሥራዎች ተከናውኗል።

በቢሮው ምክትል ኃላፊ ደረጃ የዋና ኃላፊው አማካሪ ኤፍሬም ተሰማ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ውስጥ ብቻ አራት ሺህ 574 ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ተይዞ አራት ሺህ 612ቱ ግንባታቸው ተጀምሯል። ከዚህ ውስጥ ሦስት ሺህ 953 ያህሉም ተጠናቅቀው አገልግሎት ላይ ውለዋል ሲሉ አስረድተዋል።

በመንግሥት ደረጃ በትምህርት ላይ ያለውን ስብራት ለመጠገን የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት 15 ሺህ በላይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ተችሏል ብለዋል፡፡

የትምህርቱ ዘርፉን የማሻሻል ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሕዝቡን ያሳተፉ የተለያዩ ክንውኖች እየተደረጉ መሆናቸውን አቶ ኤፍሬም አመላክተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቤቶችን ምቹና ሳቢ ለማድረግ በተጀመረው በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ላይ አበረታች አፈፃጸም መመዝገቡን አቶ ኤፍሬም አመልክተዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመት ሦስት ሺህ 410 ትምህርት ቤቶችን ለማደስ ታቅዶ እንደነበር ጠቁመው፤ ከእቅድ በላይ አምስት ሺህ 438ቱ መጀመራቸውንና እስካሁን የአራት ሺህ 627 ትምህርት ቤቶች ዕድሳት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በክልሉ የበጎ አድራጎት ተግባራትን የሚያከናውነው ቡሳ ጎኖፋ የተሰኘው ተቋም በርካታ ተግባራትን እየከወነ መሆኑን ያመላከቱት አቶ ኤፍሬም፤ ባለፉት ሶስት ዓመታትም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ግንባታ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ጠቅሰዋል፡፡

ቡሳ ጎኖፋ ሰፊ የማህበረሰቡ ክፍል የሆነው አርሶአደሩን ጭምር በማሳተፍ የተማሪዎች ምገባ፣ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ የትምህርት ቁሳቁሶችን የማሟላትና ሌሎችንም መልካም ተግባራት በመከወን ላይ እንደሚገኝ አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል፡፡

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 / 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You